ዘፍጥረት 25:23 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔርም አላት፥ “ሁለት ሕዝቦች በማኅፀንሽ አሉ፤ ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይወለዳሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል።” አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔርም እንዲህ አላት፤ “ሁለት ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል” አላት። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ጌታም እንዲህ አላት፥ “ሁለት ሕዝቦች በማሕፀንሽ አሉ፤ ሁለቱም ወገኖች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤ አንዱም ከሌላው ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እግዚአብሔርም፥ “በማሕፀንሽ ያሉት ሁለት ሕዝቦች ናቸው፤ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ሁለት ወገኖች ትወልጃለሽ፤ አንዱም ከሌላው የበረታ ይሆናል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔርም አላት፦ ሁለት ወገኖች በማኅፀንሽ ናቸው ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ፤ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል፤ ታላቁም ለታናሹ ይገዛል። |
እኅታቸው ርብቃንም መረቁአትና፥ “አንቺ እኅታችን፥ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ ዘርሽም የጠላት ሀገሮችን ይውረስ” አሉአት።
ብላቴኖቹም አደጉ፤ ጐለመሱም፤ ዔሳውም አደን የሚያውቅ የበረሃ ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት ሰው ነበረ፤ በቤትም ይቀመጥ ነበር።
አሕዛብ ይገዙልህ፤ አለቆችም ይስገዱልህ፤ ለወንድምህ ጌታ ሁን፤ የአባትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን፤ የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን።”
ይስሐቅም እጅግ ደነገጠ፤ እንዲህም አለ፥ “ያደነውን አደን ወደ እኔ ያመጣው ማን ነው? አንተ ሳትመጣም ከሁሉ በላሁ፤ ባረክሁትም፤ እርሱም የተባረከ ነው።”
ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው፥ “እነሆ ጌታህ አደረግሁት፤ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች አደረግኋቸው፤ እህሉን፥ ወይኑንና ዘይቱንም አበዛሁለት፤ ለአንተ ግን፥ ልጄ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ?”
በሰይፍህም ትኖራለህ፤ ለወንድምህም ትገዛለህ፤ ነገር ግን ቀንበሩን ከአንገትህ ልትጥል ብትወድድ ከእርሱ ጋር ተስማማ።”
የላካቸው መልእክተኞችም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት፥ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ።”
አባቱም እንቢ አለ፤ እንዲህ ሲል፥ “አውቃለሁ ልጄ ሆይ፥ አውቃለሁ፤ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፤ ዘሩም ብዙ ሕዝብ ይሆናል።”
መላዋን ኤዶምያስን ይጠብቁ ዘንድ በኤዶምያስ ሁሉ ጭፍሮችን አኖረ፤ ኤዶማውያንም ሁሉ ለንጉሥ ዳዊት ገባሮች ሆኑ፤ እግዚአብሔርም ዳዊትን በሚሄድበት ቦታ ሁሉ ጠበቀው።
በዚያም ሸለቆ ምሽግ ሠርቶ ጭፍሮችን አኖረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ። እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ሁሉ ያድነው ነበር።
ሙሴም ከቃዴስ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ መልእክተኞችን እንዲህ ብሎ ላከ፥ “ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል፦ ያገኘንን መከራ ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤
ሕዝቡንም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፦ በሴይር ላይ በተቀመጡት በወንድሞቻችሁ በዔሳው ልጆች ሀገር ታልፋላችሁ፤ እነርሱ ይፈሩአችኋል፤ እንግዲህ እጅግ ተጠንቀቁ።
በሴይርም ከተቀመጡት ከወንድሞቻችን ከዔሳው ልጆች በዓረባ መንገድ ከኤሎንና ከጋስዮን-ጋብር አለፍን። ተመልሰንም በሞዓብ ምድረ በዳ መንገድ አለፍን።