ዘፍጥረት 32 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ያዕቆብ ላባን ለመገናኘት እንደ ተዘጋጀ 1 ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፤ በዐይኖቹም የእግዚአብሔርን ሠራዊት ከትመው አየ፤ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት። 2 ያዕቆብም በአያቸው ጊዜ፥ “እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው” አለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም “ተዓይን” ብሎ ጠራው። 3 ያዕቆብም ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ወደ ሴይር ምድር ወደ ኤዶም ሀገር በፊቱ መልእክተኞችን ላከ፤ 4 እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “ለጌታዬ ለዔሳው፦ ባሪያህ ያዕቆብ እንዲህ አለ ብላችሁ ንገሩት፦ በላባ ዘንድ በስደት ተቀመጥሁ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ቈየሁ፤ 5 ላሞችንም፥ ግመሎችንም፥ አህዮችንም፥ በጎችንም፥ ወንዶች አገልጋዮችንም፥ ሴቶች አገልጋዮችንም አገኘሁ፤ አሁንም በፊትህ ሞገስን አገኝ ዘንድ ለጌታዬ ለዔሳው ለመንገር ላክሁ።” 6 የላካቸው መልእክተኞችም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት፥ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ።” 7 ያዕቆብም እጅግ ፈራ፤ የሚያደርገውንም አጣ። ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች ላሞችንም፥ ግመሎችንም፥ በጎችንም ሁለት ወገን አድርጎ ከፈላቸው፤ 8 ያዕቆብም እንዲህ አለ፥ “ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደ ሆነ የቀረው ወገን ይድናል።” 9 ያዕቆብም አለ፥ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴ የይስሐቅ አምላክ ሆይ፥ ‘ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፤ በጎነትንም አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፥ 10 ለባሪያህ በአደረግኸው በምሕረትህና በእውነትህም ሁሉ በጎውን አድርግልኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፥ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ። 11 አቤቱ ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናትን ከልጆችዋ ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና። 12 አንተም፦ ‘በርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ ብለህ ነበር።’ ” 13 በዚያችም ሌሊት በዚያው አደረ። ለወንድሙ ለዔሳውም የሚወስደውን እጅ መንሻ አወጣ፤ 14 ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሃያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሃያ የበግ አውራዎችን፥ 15 ሃምሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ ዐሥር በሬ፥ ሃያ እንስት አህያ፥ ዐሥርም የአህያ ውርንጫዎች፤ 16 መንጎቹንም ለየብቻ ከፍሎ ለብላቴኖቹ ሰጣቸው፤ ብላቴኖቹንም፥ “በፊቴ እለፉ፤ መንጋውን ከመንጋው አርቁ” አላቸው። 17 የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው፥ “ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደ ሆነ፦ ‘አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለሀ? በፊትህ ያለው ይህስ መንጋ የማን ነው?’ ብሎ የጠየቀህም እንደሆነ፥ 18 በዚያ ጊዜ አንተ፦ ‘ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የላከው የአገልጋይህ የያዕቆብ ነው፤ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ተከትሎናል’ በለው።” 19 እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን፥ በፊቱ የሚሄዱትንና መንጋውን የሚነዱትን ሁሉ እንዲሁ ብሎ አዘዘ፦“ ወንድሜ ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት፤ 20 እንዲህም በሉ፦ እነሆ አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው። በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይራራልኛል፤ ፊቱንም አያለሁ ብሎአልና።” 21 እጅ መንሻውን ከእርሱ አስቀድሞ ላከ፤ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት በሰፈር አደረ። የያዕቆብ ትግል 22 በዚያችም ሌሊት ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ዕቁባቶቹን ዐሥራ አንዱንም ልጆቹን ይዞ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ። 23 ወሰዳቸውም፤ ወንዙንም አሻገራቸው፤ ገንዘቡንም ሁሉ አሻገረ። 24 ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር። 25 እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ያዘው፤ የያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ። 26 እንዲህም አለው፥ “ሊነጋ ጎሕ ቀድዶአልና ልቀቀኝ።” እርሱም “ከአልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው። 27 እንዲህም አለው፥ “ስምህ ማን ነው?” እርሱም፥ “ያዕቆብ ነኝ” አለው። 28 አለውም፥ “ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር ታግለህ በርትተሃልና።” 29 ያዕቆብም፥ “ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው። እርሱም፥ “ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? ድንቅ ነውና” አለው። 30 በዚያም ስፍራ ባረከው። ያዕቆብም፥ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፤ ሰውነቴም ዳነች” ሲል የዚያን ቦታ ስም “ራእየ እግዚአብሔር” ብሎ ጠራው። 31 ራእየ እግዚአብሔርንም በተወ ጊዜ ፀሐይ ወጣችበት። እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። 32 ስለዚህም የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ የወርችን ሹልዳ አይበሉም፤ የያዕቆብን ጭን ይዞ የወርቹን ሹልዳ አደንዝዞአልና። |