ዘፍጥረት 48 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ያዕቆብ ኤፍሬምንና ምናሴን መባረኩ 1 ከዚህም ነገር በኋላ እንዲህ ሆነ፤ “እነሆ፥ አባታችን ደከመ” ብለው ለዮሴፍ ነገሩት፤ እርሱም ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። 2 ለያዕቆብም፥ “እነሆ፥ ልጅህ ዮሴፍ መጥቶልሃል” ብለው ነገሩት፤ እስራኤልም ተጠነካከረ፤ በአልጋውም ላይ ተቀመጠ። 3 ያዕቆብ ዮሴፍን አለው፥ “አምላኬ በከነዓን ምድር በሎዛ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም። 4 እንዲህም አለኝ፦ እነሆ፥ አበዛሃለሁ፤ አባዛሃለሁም፤ ለብዙም ሕዝብ ጉባኤ አደርግሃለሁ፤ ይህችንም ምድር ለአንተ፥ ከአንተም በኋላ ለዘለዓለም ርስት ለዘርህ እሰጣታለሁ። 5 አሁንም እኔ ወደ አንተ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የተወለዱልህ ሁለቱ ልጆችህ ለእኔ ይሁኑ፤ ኤፍሬምና ምናሴ ለእኔ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ናቸው። 6 ከእነርሱም በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ለአንተ ይሁኑ፤ በርስታቸው በወንድሞቻቸው ስም ይጠሩ። 7 እኔም ከሶርያ መስጴጦምያ በመጣሁ ጊዜ፥ ወደ ኤፍራታ ለመግባት ጥቂት ቀርቶኝ በፈረስ መጋለቢያው መንገድ ሳለሁ፥ ራሔል በከነዓን ምድር ሞተችብኝ፤ በዚያም በኤፍራታ ወደ ፈረስ መጋለቢያ በሚወስደው መንገድ ላይ ቀበርኋት፤ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት።” 8 እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ለይቶ፥ “እነዚህ ምኖችህ ናቸው?” አለው። 9 ዮሴፍም ለአባቱ ፥ “እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው። ያዕቆብም፥ “እባርካቸው ዘንድ ወደ እኔ አቅርብልኝ” አለው። 10 የእስራኤልም ዐይኖች ከሽምግልና የተነሣ ከብደው ነበር፤ ማየትም አይችልም ነበር፤ ወደ እርሱም አቀረባቸው፤ ሳማቸውም፤ አቀፋቸውም። 11 እስራኤልም ዮሴፍን፥ “ከፊትህ አልተለየሁም፤ እነሆም፥ እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ” አለው። 12 ዮሴፍም ከጕልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፤ ወደ ምድርም በግንባሩ ሰገደ። 13 ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፤ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አቆማቸው፤ ወደ አባቱም አቀረባቸው። 14 እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፤ እርሱም ታናሽ ነበረ፤ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፤ እጆቹንም አስተላለፈ። 15 ያዕቆብም ባረካቸው፤ እንዲህም አለ፥ “አባቶች አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ ደስ ያሰኙት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥ 16 ከከፉ ነገር ሁሉ የአዳነኝ መልአክ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም፥ የአባቶች የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድር ላይ ይብዙ፤ የብዙ ብዙም ይሁኑ፤” 17 ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ በአየ ጊዜ ከባድ ነገር ሆነበት፤ ዮሴፍም የአባቱን እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው። 18 ዮሴፍም አባቱን፥ “አባቴ ሆይ፥ እንዲህ አይደለም፤ በኵሩ ይህ ነውና ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ” አለው። 19 አባቱም እንቢ አለ፤ እንዲህ ሲል፥ “አውቃለሁ ልጄ ሆይ፥ አውቃለሁ፤ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፤ ዘሩም ብዙ ሕዝብ ይሆናል።” 20 በዚያም ቀን እንዲህ ብሎ ባረካቸው፥ “በእናንተ እስራኤል እንዲህ ተብሎ ይባረካል፦ እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ይባርክህ።” ኤፍሬምንም ከምናሴ ፊት አደረገው። 21 እስራኤልም ዮሴፍን፥ “እነሆ፥ እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ወደ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፤ 22 እኔም ከአሞራውያን እጅ በሰይፌና በቀስቴ የወሰድሁትን ምርኮ ለአንተ ከወንድሞችህ የተሻለውን እሰጥሃለሁ” አለው። |