1 ሳሙኤል 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት ጎልያድን እንደ ገደለ 1 ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን ለጦርነት ሰበሰቡ፤ ራሳቸውም በይሁዳ በሰኮት ተሰበሰቡ፤ በሰኮትና በዓዜቃ መካከል በኤፌርሜም ሰፈሩ። 2 ሳኦልና የእስራኤል ሰዎችም ተሰበሰቡ፤ በኤላ ሸለቆም ሰፈሩ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጉ ተሰለፉ። 3 ፍልስጥኤማውያንም በአንድ ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ እስራኤልም በሌላው ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበረ። 4 ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር የጌት ሰው ጎልያድ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ ከስንዝር የሆነ፥ ኀይለኛ ሰው መጣ። 5 በራሱም የናስ ቍር ደፍቶ ነበር፤ ጥሩርም ለብሶ ነበር፤ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስና ብረት ነበረ። 6 በእግሮቹም ላይ የናስ ገምባሌ ነበረ፤ የናስም ጭሬ በትከሻው ላይ ነበረ። 7 የጦሩም የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ ነበረ፤ የጦሩም ሚዛን ስድስት መቶ ሰቅል ብረት ነበረ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። 8 እርሱም ቆሞ ወደ እስራኤል ጭፍሮች ጮኸ፥ “ከእኛ ጋር ትዋጉ ዘንድ ለምን ወጣችሁ? እኔ ፍልስጥኤማዊ አይደለሁምን? እናንተስ የሳኦል አገልጋዮች ዕብራውያን አይደላችሁምን? ከእናንተ አንድ ሰው ምረጡ፤ ወደ እኔም ይውረድ፤ 9 ከእኔም ጋር ሊዋጋ ቢችል ቢገድለኝም፥ ባሪያዎች እንሆናችኋለን፤ እኔ ግን ባሸንፈው፥ ብገድለውም፥ እናንተ ባሪያዎች ትሆኑናላችሁ፤ ለእኛም ትገዛላችሁ” አለ። 10 ፍልስጥኤማዊውም፥ “ዛሬ የእስራኤልን ጭፍሮች ተገዳደርኋቸው፤ አንድ ሰው ስጡኝ ሁለታችንም ለብቻችን እንዋጋ አልኋቸው” አለ። 11 ሳኦልና እስራኤልም ሁሉ ይህን የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም። 12 ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፤ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፤ ስምንት ልጆችም ነበሩት፤ እሴይም በሳኦል ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር። 13 የእሴይም ሦስቱ ታላላቆች ልጆቹ ሳኦልን ተከትለው ወደ ሰልፉ ሄደው ነበር፤ ወደ ሰልፉም የሄዱት የሦስቱ ልጆች ስም ይህ ነበረ፤ ታላቁ ኤልያብ፥ ሁለተኛውም አሚናዳብ፥ ሦስተኛውም ሣማዕ ነበረ። 14 ዳዊትም የሁሉ ታናሽ ነበረ፤ ሦስቱም ታላላቆቹ ሳኦልን ተከትለው ነበር። 15 ዳዊትም የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር። 16 ፍልስጥኤማዊውም ጥዋትና ማታ እየመጣ አርባ ቀን ይቆም ነበር። 17 እሴይም ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፥ “ከዚህ በሶ አንድ የኢፍ መስፈሪያ እነዚህንም ዐሥር እንጀራዎች ለወንድሞችህ ውሰድ፤ ወደ ሰፈሩም ፈጥነህ ሂድና ለወንድሞችህ ስጣቸው፤ 18 ይህንም ዐሥሩን አይብ ወደ ሻለቃው ውሰደው፤ የወንድሞችህንም ደኅንነት ጠይቅ፤ ወሬአቸውንም አምጣልኝ።” 19 ሳኦልና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ በኤላ ሸለቆ ነበሩ። 20 ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፤ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፤ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፤ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ፥ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ። 21 የእስራኤልና የፍልስጥኤማውያን ሠራዊትም ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበር። 22 ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፤ ወደሚዋጉበትም ሮጦ ሄደ፤ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ። 23 እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለ ያ አርበኛ ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፤ ቀድሞ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፤ ዳዊትም ሰማ። 24 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዬውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከፊቱ ሸሹ። 25 የእስራኤልም ሰዎች፥ “ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፤ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፤ ልጁንም ይድርለታል፤ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል” አሉ። 26 ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች፦ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው በውኑ ይህ ይደረግለታል? የሕያው አምላክን ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው?” ብሎ ተናገራቸው። 27 ሕዝቡም፥ “ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል” ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት። 28 ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ ኤልያብም በዳዊት ላይ እጅግ ተቈጣ፥ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኵራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል” አለው። 29 ዳዊትም፥ “እኔ ምን አደረግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን?” አለ። 30 ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፤ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፤ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት። 31 ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፤ ለሳኦልም ነገሩት፤ ወደ እርሱም ወሰደው። 32 ዳዊትም ሳኦልን፥ “ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፤ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ” አለው። 33 ሳኦልም ዳዊትን፥ “አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው። 34 ዳዊትም ሳኦልን አለው፥ “እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፤ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። 35 በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር። ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር። 36 እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ ገደልሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። እንግዲህ እገድለው ዘንድ፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሄድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቈላፍ ምንድን ነው?” 37 ዳዊትም፥ “ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል” አለ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው። 38 ሳኦልም ለዳዊት ጥሩር አለበሰው፤ በራሱም ላይ የናስ ቍር ደፋለት። 39 ዳዊትንም ሰይፉን በልብሱ ላይ አስታጠቀው፤ ዳዊትም አንድና ሁለት ጊዜ ሲራመድ ደከመ። ዳዊትም ሳኦልን፥ “አለመድሁምና በዚህ መሄድ አልችልም” አለው። ከላዩም አወለቁለት። 40 ዳዊትም በትሩን በእጁ ያዘ፤ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፤ በእረኛ ኮሮጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፤ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ። 41 ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። 42 ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፤ ቀይ ብላቴና፥ መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። 43 ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትርና ድንጋይ ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው። ዳዊትም፥ “የለም ከውሻ ትከፋለህ” አለው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን በአምላኮቹ ረገመው። 44 ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “ወደ እኔ ና፤ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣቸዋለሁ” አለው። 45 ዳዊትም ፍልስጥኤማዊዉን አለው፥ “አንተ ሰይፍና ጦር፥ ጋሻም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። 46 እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፤ ራስህንም ከአንተ እቈርጠዋለሁ፤ ሬሳህንና የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ምድር ሁሉ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር እንዳለ ያውቃሉ፤ 47 ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደለ ያውቃል። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እግዚአብሔርም እናንተን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” 48 ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊዉን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ። 49 ዳዊትም እጁን ወደ ኮሮጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፤ ወነጨፈውም፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩን መታው፤ ድንጋዩም ጥሩሩን ዘልቆ በግንባሩ ተቀረቀረ፤ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ። 50 ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ ፤ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም። 51 ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፤ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፤ ገደለውም፤ ራሱንም ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ። 52 የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎችም ተነሥተው እልል አሉ፤ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጌትና እስከ አስቀሎና በር ድረስ አሳደዱአቸው። የፍልስጥኤማውያንም በድኖቻቸው እስከ ጌትና እስከ አቃሮን በሮች ድረስ በመንገድ ላይ ወደቁ። 53 የእስራኤልም ሰዎች ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመልሰው ሰፈራቸውን በዘበዙ። 54 ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ጋሻና ጦሩን ግን በድንኳኑ ውስጥ አኖረው። 55 ሳኦልም ዳዊትን ፍልስጥኤማዊውን ሊዋጋ ሲወጣ ባየ ጊዜ ለሠራዊቱ አለቃ ለአቤኔር፥ “አቤኔር ሆይ፥ ይህ ብላቴና የማን ልጅ ነው?” አለው። አቤኔርም፥ “ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ አላውቅም” አለ። 56 ንጉሡም፥ “ይህ ብላቴና የማን ልጅ እንደ ሆነ አንተ ጠይቅና ዕወቅ” አለው። 57 ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ አቤኔር ወሰደው፤ ወደ ሳኦልም ፊት አመጣው፤ የፍልስጥኤማዊውንም ራስ በእጁ ይዞ ነበር። 58 ሳኦልም፥ “አንተ ብላቴና የማን ልጅ ነህ?” አለው ዳዊትም፥ “እኔ የቤተ ልሔሙ የባሪያህ የእሴይ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ። |