ዘኍል 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጌታ ለሕዝቡ ከዐለት ውኃ እንደ አፈለቀ ( ዘፀ. 17፥1-7 ) 1 የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በመጀመሪያው ወር ወደ ጺን ምድረ በዳ መጡ፤ ሕዝቡም በቃዴስ ተቀመጡ፤ ማርያምም በዚያ ሞተች፤ ተቀበረችም። 2 ለማኅበሩም ውኃ አልነበረም፤ ሕዝቡም በሙሴና በአሮን ላይ ተሰበሰቡ። 3 ሙሴንም ተጣሉት፤ እንዲህም ብለው ተናገሩት፥ “ወንድሞቻችን በእግዚአብሔር ፊት በሞቱ ጊዜ እኛም ምነው በሞትን ኖሮ፤ 4 እኛ፥ ከብቶቻችንም በዚያ እንሞት ዘንድ የእግዚአብሔርን ማኅበር ወደዚህ ምድረ በዳ ለምን አወጣችሁ? 5 ዘር ወደማይዘራበት፥ በለስና ወይንም፥ ሮማንም፥ የሚጠጣም ውኃ ወደሌለበት ወደዚህ ክፉ ስፍራ ታመጡን ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን?” 6 ሙሴና አሮንም ከማኅበሩ ፊት ወደ ምስክሩ ድንኳን ዳጃፍ ሄደው በግንባራቸው ወደቁ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠላቸው። 7 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 8 “ይህችን በትርህን ውሰድ፤ አንተና ወንድምህ አሮንም ማኅበሩን ሰብስቡ፤ ዐለቷንም በፊታቸው እዘዟት፤ ውኃ ትሰጣለች፤ ከድንጋይዋም ውኃ ታወጡላቸዋላችሁ፤ እንዲሁም ማኅበሩን፥ ከብቶቻቸውንም ታጠጡላቸዋላችሁ።” 9 ሙሴም እግዚአብሔር እንደ አዘዘው በእግዚአብሔር ፊት የነበረችውን በትሩን ወሰደ። 10 ሙሴና አሮንም ማኅበሩን በዐለቷ ፊት ሰብስበው፥ “እናንተ ዓመፀኞች፥ እንግዲህ ስሙ፤ በውኑ ከዚህች ዐለት ውኃን እናወጣላችሁ ነበር?” አሏቸው። 11 ሙሴም እጁን ዘርግቶ ዐለቷን ሁለት ጊዜ በበትሩ መታት፤ ብዙም ውኃ ወጣ፤ ማኅበሩም፥ ከብቶቻቸውም ጠጡ። 12 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን፥ “በእስራኤል ልጆች ፊት ትቀድሱኝ ዘንድ በእኔ አላመናችሁምና ስለዚህ ወደ ሰጠኋችሁ ምድር ይህን ማኅበር ይዛችሁ አትገቡም” አላቸው። 13 የእስራኤል ልጆች ተከራክረውበታልና ይህ ውኃ የክርክር ውኃ ተባለ። እርሱም ቅዱስ መሆኑ የተገለጠበት ይህ የክርክር ውኃ ነው። የኤዶም ንጉሥ እስራኤላውያን በሀገሩ እንዳያልፉ ስለ መከልከሉ 14 ሙሴም ከቃዴስ ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ መልእክተኞችን እንዲህ ብሎ ላከ፥ “ወንድምህ እስራኤል እንዲህ ይላል፦ ያገኘንን መከራ ሁሉ አንተ ታውቃለህ፤ 15 አባቶቻችን ወደ ግብፅ ወረዱ፤ በግብፅም እጅግ ዘመን ተቀመጥን፤ ግብፃውያንም እኛንና አባቶቻችንን በደሉ። 16 ወደ እግዚአብሔርም ጮኽን፤ እግዚአብሔርም ድምፃችንን ሰማ፤ መልአክንም ልኮ ከግብፅ አወጣን፤ እነሆም፥ በምድርህ ዳርቻ ባለችው ከተማ በቃዴስ ተቀምጠናል። 17 እባክህ፥ በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻም ወደ ወይንም አንገባም፤ ከጕድጓዶችም ውኃን አንጠጣም፤ በንጉሡ ጎዳና እንሄዳለን፤ ዳርቻህንም እስክናልፍ ድረስ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አንልም።” 18 የኤዶምያስም ንጉሥ “በእኔ በኩል አታልፍም፤ ይህ ካልሆነ ግን እንዋጋለን፤ በጦርም እቀበልህ ዘንድ እወጣለሁ” አለው። 19 የእስራኤልም ልጆች፥ “በተራራው በኩል እናልፋለን፤ እኛም ከብቶቻችንም ከውኃህ ብንጠጣ ዋጋውን እንከፍላለን፤ ይህ ምንም አይደለም፤ በተራራው እንለፍ” አሉት። 20 እርሱም፥ “በእኔ በኩል አታልፍም” አለ። የኤዶምያስም ንጉሥ በብዙ ሠራዊት በጽኑ እጅ ሊገጥመው ወጣ። 21 የኤዶምያስም ንጉሥ እስራኤል በዳርቻው እንዲያልፍ አልፈቀደም፤ ስለዚህ እስራኤል ከእርሱ ተመለሰ። የአሮን ሞት 22 ከቃዴስም ተጓዙ፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በሖር ተራራ ሰፈሩ። 23 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 24 “አሮን ወደ ወገኑ ይጨመር፤ በክርክር ውኃ ዘንድ ስለ አሳዘናችሁኝ ለእስራኤል ልጆች ወደ ሰጠኋት ምድር አትገቡም። 25 አሮንንና ልጁን አልዓዛርን ይዘህ በማኅበሩ ሁሉ ፊት ወደ ሖር ተራራ ላይ አምጣቸው፤ 26 ከአሮንም ልብሱን አውጣ፤ ልጁንም አልዓዛርን አልብሰው፤ አሮንም ወደ ወገኑ ይጨመር፤ በዚያም ይሙት።” 27 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘ አደረገ፤ በማኅበሩም ሁሉ ፊት እያዩ ወደ ሖር ተራራ አወጣቸው። 28 ሙሴም የአሮንን ልብስ አወጣ፤ ልጁንም አልዓዛርን አለበሰው፤ አሮንም በዚያ በተራራው ራስ ላይ ሞተ፤ ሙሴና አልዓዛርም ከተራራው ራስ ላይ ወረዱ። 29 ማኅበሩም ሁሉ አሮን እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ፥ የእስራኤል ቤት ሁሉ ለአሮን ሠላሳ ቀን አለቀሱ። |