1 ነገሥት 22 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ነቢዩ ሚክያስ ንጉሥ አክዓብን እንዳስጠነቀቀው ( 2ዜ.መ. 18፥2-27 ) 1 በሰማርያም ሦስት ዓመት ተቀመጠ፤ በሶርያና በእስራኤልም መካከል ጦርነት አልነበረም። 2 ከዚህም በኋላ በሦስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወረደ። 3 የእስራኤልም ንጉሥ አገልጋዮቹን፥ “ሬማት ዘገለዓድ የእኛ እንደ ሆነች፥ እኛም ከሶርያ ንጉሥ እጅ ሳንወስዳት ዝም እንዳልን ታውቃላችሁን?” አላቸው። 4 የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፥ “በሬማት ዘገለዓድ እንዋጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ትዘምታለህን?” አለው። ኢዮሣፍጥም ለእስራእል ንጉሥ፥ “እኔ እንደ አንተ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ፥ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” አለው። 5 የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፥ “ወደ እግዚአብሔር ዛሬ ጠይቁልን” አለው። 6 የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ የሚያህሉትን ሰዎች ሰበሰበ፤ የእስራኤል ንጉሥም፥ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፥ “እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። 7 ኢዮሳፍጥም፥ “የእስራኤልን ንጉሥ የእግዚአብሔርን ቃል እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔር ነቢይ በዚህ አይገኝምን?” አለው። 8 የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት የይምላ ልጅ ሚክያስ የሚባል አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ክፉ እንጂ መልካም አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ” አለው። የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም፥ “ንጉሥ እንዲህ አይበል” አለ። 9 የእስራኤልም ንጉሥ አንዱን ጃንደረባ ጠርቶ፥ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ ጥራው” አለው። 10 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥም ከጦር መሣሪያቸው ጋር በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ተናገሩ። 11 የከሓና ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ትወጋቸዋለህ” አለ። 12 ነቢያትም ሁሉ እንዲህ ብለው ትንቢት ተናገሩ፥ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ዝመት፤ እግዚአብሔርም ይረዳሃል። ሶርያውያንንና ንጉሣቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል።” 13 ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ፥ “እነሆ፥ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ” አለው። 14 ሚክያስም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር የሚነግረኝን እርሱን እናገራለሁ” አለ። 15 ወደ ንጉሡም ደረሰ። ንጉሡም፥ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር?” አለው። እርሱም፥ “ውጣና ተከናወን፤ እግዚአብሔርም በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታል” ብሎ መለሰለት። 16 ንጉሡም፥ “በእግዚአብሔር ስም እውነት ትነግረኝ ዘንድ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። 17 እርሱም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም አለ፦ እግዚአብሔር የእነዚህ አምላክ አይደለምን? እያንዳንዱ በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ።” 18 የእስራኤልም ንጉሥ የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥን፥ “ክፉ እንጂ መልካም እንደማይናገርልኝ አላልሁምን?” አለው። 19 ሚክያስም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔርን ቃል የሰማሁት እኔ አይደለሁምን? እንዲህ አይደለም፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። 20 እግዚአብሔርም፦ ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ አክዓብን የሚያሳስት ማን ነው? አለ። አንዱም እንዲህ ያለ ነገር፥ ሌላውም እንዲያ ያለ ነገር ተናገረ። 21 መንፈስም ወጣ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ፦ እኔ አስተዋለሁ አለ። 22 እግዚአብሔርም፦ በምን ታስተዋለህ? አለው፤ እርሱም ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም፦ ማሳሳትስ ታሳስተዋለህ፤ ይሆንልሃልም፤ ውጣ፤ እንዲሁም አድርግ አለ። 23 አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በላይህ ክፉ ተናግሮብሃል።” 24 የከሓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም ጕንጩን በጥፊ መታውና፥ “ምን ዓይነት የእግዚአብሔር መንፈስ ነው የተናገረህ?” አለው። 25 ሚክያስም፥ “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ ውስጠኛው እልፍኝህ በሄድህ ጊዜ ታያለህ” አለ። 26 የእስራኤልም ንጉሥ፥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማዪቱም ሹም ወደ አሞን ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ፦ 27 ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉአቸው” አለ። 28 ሚክያስም፥ “በሰላም ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም” አለ። ደግሞም አሕዛብ ሁሉ ሆይ! ስሙኝ” አለ። የንጉሥ አክዓብ ሞት ( 2ዜ.መ. 18፥28-34 ) 29 የእስራኤልም ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ዘመቱ። 30 የእስራኤልም ንጉሥ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን የእኔን ልብስ ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ወደ ሰልፍ ገባ። 31 የሶርያም ንጉሥ ሠላሳ ሁለቱን የሰረገሎች አለቆች፥ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፥ ታናሽ ቢሆን ወይም ታላቅ ከማናቸውም ጋር አትዋጉ” ብሎ አዝዞ ነበር። 32 የሰረገሎች አለቆችም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፥ “በእውነት የእስራኤልን ንጉሥ ይመስላል፤” አሉ ይዋጉትም ዘንድ ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥም ጮኸ። 33 የሰረገሎች አለቆችም የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። 34 አንድ ሰውም ቀስቱን ድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በሳንባውና በደረቱ መካከል ወጋው፤ ሰረገለኛውንም፥ “መልሰህ ንዳ፤ ተወግቻለሁና ከሰልፍ ውስጥ አውጣኝ” አለው። 35 በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ ንጉሡም ከጥዋት እስከ ማታ በሶርያውያን ፊት በሰረገላው ላይ ተደግፎ ነበር፤ የቍስሉም ደም በሰረገላው ውስጥ ፈሰሰ፤ ማታም ሞተ። 36 ፀሐይም በገባች ጊዜ አዋጅ ነጋሪው ወጥቶ፥ “ንጉሡ ሞቶአልና እያንዳንዱ ወደ ከተማው፥ እያንዳንዱም ወደ ሀገሩ ይሂድ” ብሎ አዋጅ ነገረ። 37 ወደ ሰማርያም መጡ፤ ንጉሡንም በሰማርያ ቀበሩት፤ 38 ሰረገላውንም በሰማርያ ምንጭ አጠቡት። እግዚአብሔርም በነቢዩ አድሮ እንደ ተናገረ ውሾችና ጅቦች ደሙን ላሱት። አመንዝሮች ሴቶችም በደሙ ታጠቡበት። 39 የቀረውም የአክዓብ ነገር፥ ያደረገውም ነገር ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የሠራው ቤት፥ የሠራቸውም ከተሞች ሁሉ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 40 አክዓብም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ አካዝያስ ነገሠ። ስለ ይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ( 2ዜ.መ. 20፥31—21፥1 ) 41 የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። 42 ኢዮሣፍጥም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ አምስት ዓመት ጎበዝ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ አምስት ዓመት ነገሠ። እናቱም ዓዙባ የተባለች የሴሜይ ልጅ ነበረች። 43 በአባቱም በአሳ መንገድ ሁሉ ሄደ፤ ከእርሱም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቅን አደረገ፤ ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉትን መስገጃዎችን አላራቀም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 44 ኢዮሣፍጥም ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ታረቀ። 45 የቀረውም የኢዮሣፍጥ ነገር፥ ኀይሉም፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። 46 ከአባቱም ከአሳ ዘመን የቀረውን ርኩስ ሥራ ከምድር አጠፋ። 47 በኤዶምያስም ንጉሥ አልነበረም፤ ሹሙም እንደ ንጉሥ ነበረ። 48 ኢዮሣፍጥም ወደ ኦፌር ሄደው ወርቅ ያመጡ ዘንድ በተርሴስ መርከብን ሠራ፤ ነገር ግን መርከቢቱ በጋሴዎንጋቤር ተሰብራለችና አልሄደችም። 49 የአክዓብም ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን፥ “አገልጋዮችህ ከአገልጋዮቼ ጋር በመርከብ ይሂዱ” አለው፤ ኢዮሣፍጥ ግን አልወደደም። 50 ኢዮሣፍጥም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በእርሱም ፋንታ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። 51 በይሁዳም ንጉሥ በኢዮሣፍጥ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመተ መንግሥት የአክዓብ ልጅ አካዝያስ በእስራኤል ላይ በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። 52 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በአባቱ በአክዓብ፥ በእናቱም በኤልዛቤል መንገድ፥ እስራኤልንም ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ ሄደ። 53 በዓሊምንም አመለከ፤ ሰገደላቸውም፤ ከእርሱም አስቀድሞ አባቶቹ እንዳደረጉት ሁሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣው። |