ዘፍጥረት 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሌሎች የአብርሃም ዘሮች ( 1ዜ.መ. 1፥32-33 ) 1 አብርሃም ቀጡራ የምትባል ሌላ ሚስት አገባ፤ 2 እርስዋም ዚምራንን፥ ዮቅሻንን፥ መዳንን፥ ምድያምን፥ ዩሽባቅንና ሹሐን ወለደችለት። 3 ዮቅሻንም ሳባንና ደዳንን ወለደ፤ የደዳንም ዘሮች አሹራውያን፥ ሌጡሻውያንና ሌኡማውያን ናቸው። 4 የምድያምም ልጆች ዔፋ፥ ዔፈር፥ ሐኖክ፥ አቢዳዕና ኤልዳዓ ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የቀጡራ ዘሮች ናቸው። 5 አብርሃም ያለውን ሀብት ሁሉ ለይስሐቅ አወረሰው፤ 6 ከሌሎች ሴቶች ለተወለዱትም ልጆች ገና በሕይወት ሳለ ስጦታ ሰጣቸው፤ ከዚህ በኋላ እነዚህ ሌሎች ልጆች ከይስሐቅ ርቀው ወደ ምሥራቅ አገር እንዲሄዱ አደረጋቸው። የአብርሃም መሞት 7 የአብርሃም ዕድሜ በአጠቃላይ መቶ ሰባ አምስት ዓመት ነበር፤ 8 በዚህም ዐይነት አብርሃም በቂ ዕድሜ አግኝቶ ካረጀ በኋላ ሞተ፤ 9 ልጆቹ ይስሐቅና እስማኤል ማክፌላ በተባለ ዋሻ ቀበሩት፤ ይህም ዋሻ ከመምሬ በስተምሥራቅ በሒታዊው በጾሐር ልጅ በዔፍሮን እርሻ ውስጥ የሚገኘው ነው፤ 10 እርሱም አብርሃም ከሒታውያን ላይ የገዛው የመቃብር ቦታ ነው፤ በዚህ ዐይነት አብርሃም ሚስቱ ሣራ በተቀበረችበት ዋሻ ተቀበረ። 11 አብርሃም ከሞተ በኋላ ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር ባረከው፤ ይስሐቅም “ብኤርላሐይ ሮኢ ወይም የሚያየኝ ሕያው አምላክ” ተብሎ በሚጠራው ኲሬ አጠገብ ይኖር ነበር። የእስማኤል ዘሮች ( 1ዜ.መ. 1፥28-31 ) 12 የሣራ አገልጋይ ግብጻዊትዋ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል፥ 13 ከዚህ በታች በዕድሜአቸው ቅደም ተከተል ተራ የተዘረዘሩትን ልጆች ወለደ፤ እነርሱም፦ ነባዮት፥ ቄዳር፥ አድብኤል፥ ሚብሣም፥ 14 ሚሽማዕ፥ ዱማ፥ ማሣ፥ 15 ሐዳድ፥ ቴማ፥ ይጡር፥ ናፊሽ እና ቄድማ ናቸው። 16 እነዚህ የእስማኤል ልጆች ለዐሥራ ሁለት ነገዶች ቅድመ አያቶች ነበሩ፤ ስማቸውም በኖሩባቸው ከተሞችና ስፍራዎች ሲጠራ ይኖራል። 17 እስማኤል መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ሲሆነው ሞተ፤ 18 የእስማኤል ዘሮች ከግብጽ በስተምሥራቅ ወደ አሦር በምትወስደው መንገድ በሐዊላና በሹር መካከል ይኖሩ ነበር፤ የኖሩትም ከሌሎቹ የአብርሃም ዘሮች ጋር በጥላቻ ተራርቀው ነበር። የዔሳውና የያዕቆብ መወለድ 19 የአብርሃም ልጅ የይስሐቅ ታሪክ ይህ ነው፤ አብርሃም ይስሐቅን ወለደ። 20 ይስሐቅ የባቱኤልን ልጅ ርብቃን ሲያገባ አርባ ዓመት ሆኖት ነበር፤ የርብቃ አባት ባቱኤልና ወንድምዋ ላባ በመስጴጦምያ የሚኖሩ ሶርያውያን ነበሩ፤ 21 ርብቃ መኻን ስለ ነበረች ይስሐቅ ስለ እርስዋ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ስለ ሰማ ርብቃ ፀነሰች፤ 22 የተፀነሱትም መንትያዎች ስለ ነበሩ እርስ በርሳቸው በማሕፀንዋ ውስጥ ይገፋፉ ነበር፤ እርስዋም “ይህን ዐይነት ነገር ለምን ደረሰብኝ?” በማለት ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ ተነሣሣች። 23 እግዚአብሔርም፥ “በማሕፀንሽ ያሉት ሁለት ሕዝቦች ናቸው፤ እርስ በርሳቸው የማይስማሙ ሁለት ወገኖች ትወልጃለሽ፤ አንዱም ከሌላው የበረታ ይሆናል፤ ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት። 24 የመውለጃዋም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደች። 25 የመጀመሪያው ልጅ መልኩ ቀይ፥ ሰውነቱ ጠጒራም ነበር፤ ስለዚህ ዔሳው ተባለ። 26 ሁለተኛው ልጅ ሲወለድ የዔሳውን ተረከዝ ይዞ በመውጣቱ ያዕቆብ ተባለ፤ ልጆቹ በተወለዱ ጊዜ ይስሐቅ ሥልሳ ዓመት ሆኖት ነበር። ዔሳው ብኲርናውን መሸጡ 27 ሁለቱም ልጆች አደጉ፤ ዔሳው በዱር መዋል የሚወድ ብልኅ አዳኝ ሆነ፤ ያዕቆብ ግን በቤት መዋል የሚወድ ጭምት ሰው ነበር። 28 ዔሳው እያደነ ሥጋ ያበላው ስለ ነበረ ይስሐቅ ዔሳውን ይወድ ነበር። ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወድ ነበር። 29 ከዕለታት አንድ ቀን ያዕቆብ ቀይ የምስር ወጥ በመሥራት ላይ እንዳለ ዔሳው ከአደን መጣ፤ በጣም እርቦት ነበር፤ 30 ስለዚህም ያዕቆብን “ከዚህ ከቀይ ወጥ ስጠኝ” አለው። ኤዶም የተባለውም በዚህ ምክንያት ነበር። 31 ያዕቆብም “መጀመሪያ ብኲርናህን ሽጥልኝ” አለው። 32 ዔሳውም “እኔ በራብ መሞቴ ነው፤ ታዲያ ብኲርና ምን ያደርግልኛል?” አለው። 33 ያዕቆብም “እንግዲያውስ ብኲርናህን እንደምትሸጥልኝ መጀመሪያ ማልልኝ” አለው። ስለዚህ ዔሳው ምሎ ብኲርናውን ለያዕቆብ ሸጠ። 34 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ የምስሩን ወጥ በእንጀራ አድርጎ ሰጠው፤ ዔሳውም ከበላና ከጠጣ በኋላ ተነሥቶ ሄደ፤ በዚህ ዐይነት ዔሳው ብኲርናውን በመናቅ አቃለላት። |