ዘፍጥረት 33 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ያዕቆብ ዔሳውን እንደ ተገናኘው 1 ያዕቆብም ዐይኑን አነሣ፤ እነሆም፥ ዔሳውን ሲመጣ አየው፤ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ ልጆቹንም ከፍሎ ወደ ልያና ወደ ራሔል ወደ ሁለቱም ዕቁባቶቹ አደረጋቸው፤ 2 ዕቁባቶቹንና ልጆቻቸውንም በፊት አደረገ፤ ልያንና ልጆችዋን በኋላ፥ ራሔልንና ዮሴፍንም ከሁሉ በኋላ አደረገ። 3 እርሱም በፊታቸው አለፈ፤ ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳውም እስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ። 4 ዔሳውም ሊገናኘው ሮጠ፤ አንገቱንም አቅፎ ሳመው፤ ሁለቱም በአንድነት አለቀሱ። 5 ዔሳውም ዐይኑን አነሣና ሴቶችንና ልጆችን አየ፤ እንዲህም አለ፥ “እነዚህ ምኖችህ ናቸው?” እርሱም፥ “እግዚአብሔር ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለ። 6 ዕቁባቶቹም ከልጆቻቸው ጋር ቀርበው ሰገዱ፤ 7 ደግሞም ልያና ልጆችዋ ቀርበው ሰገዱለት፤ ከዚያም በኋላ ዮሴፍና ራሔል ቀርበው ሰገዱ። 8 ዔሳውም፥ “ያገኘሁት ይህ ሠራዊት ሁሉ ምንህ ነው?” አለ። እርሱም፥ “በጌታዬ ፊት ሞገስን አገኝ ዘንድ ያደረግሁልህ ነው” አለ። 9 ዔሳውም፥ “ለእኔ ብዙ አለኝ፤ ወንድሜ ሆይ፥ የአንተ ለአንተ ይሁን” አለ። 10 ያዕቆብም አለ፥ “እንደዚህ አይደለም፤ ነገር ግን በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅ መንሻዬን ከእጄ ተቀበለኝ፤ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያይ ፊትህን አይቻለሁና፥ በቸርነትም ተቀብለኸኛልና። 11 ከወደድኸኝስ ይህችን ያመጣሁልህን በረከቴን ተቀበል፤ እግዚአብሔር ራርቶልኛልና፥ ለእኔም ብዙ አለኝና።” እስኪቀበለውም ድረስ ግድ አለው፤ ተቀበለውም። 12 እርሱም፥ “ተነሣና ወደ ፊት እንሂድ” አለው። 13 እርሱም አለው፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ፤ ሰዎችም በአንድ ወይም በሁለት ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደ ሆነ ከብቶቹ ሁሉ ይሞታሉ። 14 ጌታዬ ከአገልጋዩ ፊት ቀድሞ ይለፍ፤ እኛም እንደ ቻልን እንሄዳለን፤ በጎዳናም እንውላለን፤ ወደ ጌታችን ወደ ሴይር እስክንደርስም በሕፃናቱ ርምጃ መጠን እንሄዳለን” አለው። 15 ዔሳውም፥ “ከእኔ ጋር ካሉ ሰዎች ከፍዬ ልተውልህን?” አለ። እርሱም፥ “ይህ ለምንድን ነው? በጌታዬ ዘንድ ሞገስን ማግኘቴ ይበቃኛል” አለ። 16 ዔሳውም በዚያ ቀን ወደ ሴይር ተመለሰ። 17 ያዕቆብ ግን በሰፈሩ አደረ፤ በዚያም ለእርሱ ቤትን ሠራ፤ ለከብቶቹም ዳሶችን አደረገ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ማኅደር ብሎ ጠራው። 18 ያዕቆብም ከሁለቱ ወንዞች መካከል በተመለሰ ጊዜ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሰቂሞን ከተማ ወደ ሴሎም መጣ፤ በከተማዪቱም ፊት ለፊት ሰፈረ። 19 ድንኳኑን ተክሎበት የነበረውንም የእርሻ ክፍል ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች ገዛው። 20 በዚያም መሠውያዉን አቆመ፤ የእስራኤልንም አምላክ ጠራ። |