ዘፍጥረት 36 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዔሳው ትውልድ ( 1ዜ.መ. 1፥34-37 ) 1 ኤዶም የተባለው የዔሳው ትውልድ እንዲህ ነው። 2 ዔሳው ከከነዓን ልጆች ሚስቶችን አገባ፤ የኬጤያዊውን የዔሎን ልጅ ሐዳሶን፥ የኤውያዊው የሴቤሶ ልጅ ሐና የወለዳትን ኤሌባማን፥ 3 የይስማኤልን ልጅ የናቡአት እኅት ቤሴሞትን። 4 ሐዳሶ ለእርሱ ኤልፋዝን ወለደች፤ ቤሴሞትም ራጉኤልን ወለደች፤ 5 ኤሌባማም ዮሔልን፥ ይጉሜልን፥ ቆሬንም ወለደች። በከነዓን ምድር የተወለዱለት የዔሳው ልጆች እነዚህ ናቸው። 6 ዔሳውም ሚስቶቹን፥ ወንዶች ልጆቹንና ሴቶች ልጆቹን፥ ቤተ ሰቡንም ሁሉ፥ እንስሶቹንም ሁሉ፥ በከነዓንም ሀገር ያገኘውን ገንዘቡን ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ፊት ከከነዓን ሀገር ሄደ። 7 ከብታቸው ስለበዛ በአንድነት ይቀመጡ ዘንድ አልቻሉም፤ በእንግድነት የተቀመጡባትም ምድር ከከብታቸው ብዛት የተነሣ ልትበቃቸው አልቻለችም። 8 ዔሳውም በሴይር ተራራ ተቀመጠ፤ ዔሳውም ኤዶም ነው። 9 በሴይር ተራራ የሚኖሩ የኤዶማውያን አባት የዔሳው ትውልድም እንዲህ ነው። 10 የዔሳው ልጆች ስም ይህ ነው፤ የዔሳው ሚስት የሐዳሶ ልጅ ኤልፋዝ፤ የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጅ ራጉኤል። 11 የዔሳው ልጅ የኤልፋዝ ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ቴማን፥ ኤሞር፥ ሳፍር፥ ጎቶን፥ ቄኔዝ። 12 ቴምናሕም ለዔሳው ልጅ ለኤልፋዝ ዕቅብት ነበረች፤ አማሌቅንም ለኤልፋዝ ወለደችለት፤ የዔሳውም ሚስት የሐዳሶ ልጆች እነዚህ ናቸው። 13 የዔሳው ልጅ የራጉኤል ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ናሖት፥ ዛራ፥ ሲም፥ ሞዛህ፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጆች ናቸው። 14 የሴቤጎን ልጅ የሐና ልጅ የዔሳው ሚስት የኤሌባማ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ለዔሳውም ዮሔልን፥ ዩጉሜልን፥ ቆሬን ወለደች። 15 የዔሳው ልጆች መሳፍንት እነዚህ ናቸው፤ የዔሳው የበኵር ልጅ የኤልፋዝ ልጆች፤ ቴማን መስፍን፥ ኦሜር መስፍን፥ ሳፍር መስፍን፥ ቄኔዝ መስፍን፥ 16 ቆሬ መስፍን፥ ጎቶን መስፍን፥ አማሌቅ መስፍን፤ በኤዶም ምድር የኤልፋዝ መሳፍንት እነዚህ ናቸው፤ እነዚህ የሓዳሶ ልጆች ናቸው ። 17 የዔሳው ልጅ የራጉኤል ልጆች መሳፍንት እነዚህ ናቸው፤ ናሖት መስፍን፥ ዛራ መስፍን፥ ሲን መስፍን፥ ሞዛህ መስፍን፤ በኤዶም ምድር የራጉኤል ልጆች መሳፍንት እነዚህ ናቸው፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጆች ናቸው። 18 የዔሳው ሚስት የኤሌባማ ልጆች መሳፍንት እነዚህ ናቸው፤ ዮሔል መስፍን፥ ይጉሜል መስፍን፥ ቆሬ መስፍን፤ የዔሳው ሚስት የሐና ልጅ የኤሌባማ ልጆች መሳፍንት እነዚህ ናቸው። 19 የዔሳው ልጆችና መስፍኖቻቸው እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም የኤዶም ልጆች ናቸው። የሴይር ዘሮች ( 1ዜ.መ. 1፥38-42 ) 20 በዚያች ሀገር የተቀመጡ የሖሪያዊው የሴይር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሉጣን፥ ሦባን፥ ሳባቅ፥ አናም፥ 21 ዲሶን፥ ኤሶር፥ ዲሳን፤ እነዚህ በኤዶም ምድር የሖሪያዊው የሴይር ልጆች መሳፍንት ናቸው። 22 የሉጣን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ሖሪ፥ ሃማን ናቸው፤ የሉጣንም እኅት ትምናዕ ናት። 23 የሦባን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ዓልዋን፥ ማኔሐት፥ ኤቤል፥ ሳፋር፥ አውናም። 24 የሳባቅ ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ኢኣ፥ ዓናን፤ ይህም ዓናን በምድረ በዳ የአባቱን የሳባቅን አህዮች ሲጠብቅ ፍል ውኃዎችን ያገኘ ነው። 25 የዓናን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ዲሶን፤ የዓናን ሴት ልጅ ኤሌባማ። 26 የዲሶንም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሕምዳን፥ አስባን፥ ቤዖር፥ ይትራን፥ ክራን። 27 የኤሶር ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ከልሐን፥ ዛኦን፥ ዓቃን። 28 የሪሶን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ዑሳ፥ አራን። 29 የሖሪ መሳፍንት እነዚህ ናቸው፤ ሉጣን መስፍን፥ ሦባን መስፍን፥ ሳባቅ መስፍን፥ ዓናን መስፍን፥ 30 ዲሶን መስፍን፥ ኤሶር መስፍን፥ ሪሶን መስፍን፤ በሴይር ምድር በየሹመታቸው መሳፍንት የሆኑ የሖሪ መሳፍንት እነዚህ ናቸው። የኤዶም ነገሥታት ( 1ዜ.መ. 1፥43-54 ) 31 በእስራኤል ልጆች ላይ ንጉሥ ከመንገሡ በፊት በኤዶም ሀገር የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው። 32 በኤዶምም የቤዖር ልጅ ባላቅ ነገሠ፤ የከተማዋም ስም ዴናባ ናት። 33 ባላቅም ሞተ፤ በእርሱ ፈንታም የባሶራው የዛራ ልጅ ኢዮባብ ነገሠ። 34 ኢዮባብም ሞተ፤ በእርሱም ፈንታ የቴማኒው ሀገር ሑሳም ነገሠ። 35 ሑሳምም ሞተ፤ በእርሱም ፈንታ የምድያምን ሰዎች በሞዓብ ሜዳ የገደለ የቤዳድ ልጅ አዳድ ነገሠ፤ የከተማዋም ስም ዓዊት ተባለ። 36 ዓዳድም ሞተ፤ በእርሱም ፈንታ የምስሬቃው ሠምላ ነገሠ። 37 ሠምላም ሞተ፤ በእርሱም ፈንታ በወንዝ አጠገብ ካለችው ከርኆቦት ሳኦል ነገሠ። 38 ሳኦልም ሞተ፤ በእርሱም ፈንታ የዓክቦር ልጅ በአልሐናን ነገሠ። 39 የአክቦር ልጅ በአልሐናንም ሞተ፤ በእርሱም ፈንታ አዳር ነገሠ፤ የከተማውም ስም ፎጎር ነው፤ ሚስቱም የሜዛአብ ልጅ መጥሬድ የወለደቻት ምኤጠብኤል ትባላለች። 40 የዔሳውም የመሳፍንቱ ስም በየነገዳቸው፥ በየስፍራቸው፥ በያገራቸውና በየሕዝባቸው ይህ ነው፤ ትምናዕ መስፍን፥ ዓልዋ መስፍን፥ ኤቴት መስፍን፥ 41 ኤሌባማ መስፍን፥ ኤላ መስፍን፥ ፊኖን መስፍን፥ 42 ቄኔዝ መስፍን፥ ቴማን መስፍን፥ ሜብሳር መስፍን፥ 43 መግዴኤል መስፍን፥ ኤራም መስፍን፤ እነዚህ በግዛታቸው ምድር በየመኖሪያቸው የኤዶም መሳፍንት ናቸው። የኤዶማውያንም አባት ይህ ዔሳው ነው። |