ዘፍጥረት 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ ባረከ 1 እንዲህም ሆነ፦ ይስሐቅ ፈጽሞ ከአረጀ በኋላ ዐይኖቹ ፈዝዘው አያይም ነበር። ታላቁን ልጁን ዔሳውንም ጠርቶ፥ “ልጄ ሆይ፥” አለው፤ እርሱም፥ “እነሆ አለሁ” አለው። 2 እርሱም አለው፥ “እነሆ እኔ አረጀሁ፤ የምሞትበትን ቀን አላውቅም። 3 አሁንም ማደኛህን የፍላጻህን አፎትና ቀስትህን ውሰድ፤ ወደ ምድረ በዳም ውጣ፤ አደንም አድንልኝ፤ 4 ሳልሞትም ነፍሴ እንድትባርክህ እኔ እንደምወደው መብል አዘጋጅተህ እበላ ዘንድ አምጣልኝ።” 5 ርብቃም ይስሐቅ ለልጁ ለዔሳው እንደዚህ ሲነግር ትሰማ ነበር። ዔሳውም ለአባቱ አደን ሊያድን ወደ ምድረ በዳ ሄደ። 6 ርብቃም ታናሹ ልጅዋን ያዕቆብን እንዲህ አለችው፦ 7 “እነሆ፥ አባትህ ለወንድምህ ለዔሳው፦ እንዲህ ሲለው ሰማሁ፤ ‘ሂድና ከአደንኸው መብል አዘጋጅተህ አምጣልኝ፤ ሳልሞትም በልች በእግዚአብሔር ፊት ልባርክህ።’ 8 አሁንም ልጄ ሆይ፥ እኔ እንደማዝዝህ ስማኝ፤ 9 ወደ በጎቻችን ሄደህ ሁለት መልካም ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እነርሱንም ለአባትህ እንደሚወደው መብል አደርጋቸዋለሁ፤ 10 ለአባትህም ሳይሞት እንዲባርክህ፥ ይበላ ዘንድ ትወስድለታለህ።” 11 ያዕቆብም እናቱን ርብቃን፥ “እነሆ ዔሳው ወንድሜ ጠጕራም ሰው ነው፥ እኔ ግን ለስላሳ ነኝ፤ 12 ምናልባት አባቴ ቢዳስሰኝ በፊቱ እንደምንቀው እሆናለሁ፤ መርገምን በላዬ አመጣለሁ፤ በረከትንም አይደለም።” 13 እናቱም አለችው፥ “ልጄ ሆይ፥ መርገምህ በእኔ ላይ ይሁን፥ ቃሌን ብቻ ስማኝ፤ ሂድና ያልሁህን አምጣልኝ።” 14 ሄዶም አመጣ፤ ለእናቱም ሰጣት፤ እናቱም መብልን አባቱ እንደሚወድደው አደረገች። 15 ርብቃም ከእርስዋ ዘንድ በቤት የነበረውን የታላቁን ልጅዋን የዔሳውን መልካሙን ልብስ አመጣች፤ ለታናሹ ልጅዋ ለያዕቆብም አለበሰችው፤ 16 የጠቦቶችንም ለምድ በእጆቹና በለስላሳው አንገቱ ላይ አደረገች፤ 17 ያን የሠራችውን መብልና እንጀራውን ለልጅዋ ለያዕቆብ በእጁ ሰጠችው። 18 ወደ አባቱም አግብቶ፥ “አባቴ ሆይ፥” አለው፦ እርሱም፥ “እነሆኝ፤ ልጄ ሆይ፥ አንተ ማን ነህ?” አለ። 19 ያዕቆብም አባቱን አለው፥ “የበኵር ልጅህ እኔ ዔሳው ነኝ፤ እንዳዘዝኸኝ አደረግሁ፤ ነፍስህ ትባርከኝ ዘንድ ቀና ብለህ ተቀመጥ፤ ካደንሁትም ብላ።” 20 ይስሐቅም ልጁን፥ “ልጄ ሆይ፥ ፈጥነህ ያገኘኸው ይህ ምንድን ነው?” አለው። እርሱም፥ “አምላክህ እግዚአብሔር በፊቴ የሰጠኝ ነው” አለ። 21 ይስሐቅም ያዕቆብን፥ “ልጄ ሆይ፥ አንተ ልጄ ዔሳው እንደ ሆንህ ወይም እንዳልሆንህ ቅረበኝና ልዳስስህ” አለው። 22 ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ ቀረበ፤ ዳሰሰውም፤ እንዲህም አለው፥ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፥ እጆች ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለው። 23 እርሱም አላወቀውም ነበር፤ እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ነበሩና፤ ይስሐቅም ባረከው ። 24 አለውም፥ “አንተ ልጄ ዔሳው ነህን?” እርሱም፥ “እኔ ነኝ” አለ። 25 እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ ከአደንኸው እንድበላና ነፍሴ እንድትባርክህ አምጣልኝ” አለው። አቀረበለትም፤ በላም፤ ወይንም አመጣለት፤ እርሱም ጠጣ። 26 አባቱ ይስሐቅም፥ “ልጄ ሆይ፥ ወደ እኔ ቅረብ፤ ሳመኝም” አለው። 27 ወደ እርሱም ቀረበ፤ ሳመውም፤ የልብሱንም ሽታ አሸተተ፤ ባረከውም፤ እንዲህም አለ፥ “የልጄ ሽታ እግዚአብሔር እንደ ባረከው የእርሻ ሽታ ነው፤ 28 እግዚአብሔርም ከሰማይ ጠል፥ ከምድርም ስብ፥ የእህልንም፥ የወይንንም፥ የዘይትንም ብዛት ይስጥህ፤ 29 አሕዛብ ይገዙልህ፤ አለቆችም ይስገዱልህ፤ ለወንድምህ ጌታ ሁን፤ የአባትህም ልጆች ይስገዱልህ፤ የሚረግምህ እርሱ ርጉም ይሁን፤ የሚባርክህም ቡሩክ ይሁን።” ዔሳው ከይስሐቅ በረከትን መለመኑ 30 ይስሐቅም ያዕቆብን ባርኮ ከፈጸመ በኋላ፥ ያዕቆብ ከአባቱ ከይስሐቅ ፊት ወጣ፥ ወንድሙ ዔሳውም ከአደኑ መጣ፤ 31 እርሱም ደግሞ መብል አዘጋጀ፥ ለአባቱም አመጣ፤ አባቱንም፥ “አባቴ ተነሥ፤ ነፍስህም ትባርከኝ ዘንድ ልጅህ ከአደነው ብላ” አለው። 32 አባቱ ይስሐቅም፥ “አንተ ማን ነህ?” አለው። እርሱም፥ “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው። 33 ይስሐቅም እጅግ ደነገጠ፤ እንዲህም አለ፥ “ያደነውን አደን ወደ እኔ ያመጣው ማን ነው? አንተ ሳትመጣም ከሁሉ በላሁ፤ ባረክሁትም፤ እርሱም የተባረከ ነው።” 34 ዔሳውም የአባቱን ቃል በሰማ ጊዜ ታላቅ፥ እጅግም መራራ ጩኸት ጮኸ፤ አባቱንም፥ “አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ” አለው። 35 ይስሐቅም ዔሳውን አለው፥ “ወንድምህ በተንኰል መጥቶ በረከትህን ወሰደብህ።” 36 ዔሳውም አለ፥ “በእውነት ስሙ ያዕቆብ ተባለ፤ ሁለት ጊዜ አሰናክሎኛልና፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደ፤ አሁንም እነሆ በረከቴን ወሰደ።” ዔሳውም አባቱን አለው፥ “ደግሞም አባቴ ሆይ፥ ለእኔ በረከትን አላስቀረህልኝምን?” 37 ይስሐቅም መለሰ ዔሳውንም አለው፥ “እነሆ ጌታህ አደረግሁት፤ ወንድሞቹንም ሁሉ ለእርሱ ተገዦች አደረግኋቸው፤ እህሉን፥ ወይኑንና ዘይቱንም አበዛሁለት፤ ለአንተ ግን፥ ልጄ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ?” 38 ዔሳውም አባቱን ይስሐቅን አለው፥ “አባቴ ሆይ፥ በረከትህ አንዲት ብቻ ናትን? አባቴ ሆይ፥ እኔንም ደግሞ ባርከኝ።” ዔሳውም ጮሆ አለቀሰ። 39 አባቱ ይስሐቅም መለሰ፤ አለውም፥ “እነሆ መኖሪያህ ከላይ ከሰማይ ጠል፥ ከምድርም ስብ ይሁን፤ 40 በሰይፍህም ትኖራለህ፤ ለወንድምህም ትገዛለህ፤ ነገር ግን ቀንበሩን ከአንገትህ ልትጥል ብትወድድ ከእርሱ ጋር ተስማማ።” 41 ዔሳውም አባቱ ስለ ባረከው በያዕቆብ ቂም ያዘበት፤ ዔሳውም በልቡ አለ፥ “ለአባቴ የልቅሶ ቀን ትቅረብ፤ ወንድሜን ያዕቆብን እገድለዋለሁ።” 42 ለርብቃም ታላቁ ልጅዋ ዔሳው ያለው ተነገራት፤ ታናሹን ልጅዋን ያዕቆብንም ልካ ጠራችው፤ አለችውም፥ “እነሆ ወንድምህ ዔሳው ያድድንሃል፤ ሊገድልህም ይፈልጋል። 43 አሁንም ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ስማ፤ ተነሣና በሶርያ ወንዞች መካከል ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ፤ 44 በእርሱም ዘንድ ጥቂት ቀን ተቀመጥ። የወንድምህ ቍጣ ከአንተ እስኪበርድ ድረስ፥ 45 ያደረግህበትንም እስኪረሳው ድረስ፤ በአንድ ቀን ሁለታችሁን እንዳላጣ፥ ከዚያም ልኬ አመጣሃለሁ።” ይስሐቅ ያዕቆብን ወደ ላባ መላኩ 46 ርብቃም ይስሐቅን አለችው፥ “ከኬጢ ሴቶች ልጆች የተነሣ ሕይወቴን ጠላሁት፤ ያዕቆብ ከዚህ ሀገር ሴቶች ልጆች ሚስትን የሚያገባ ከሆነ በሕይወት መኖር ለእኔ ምኔ ነው?” |