ዘዳግም 31:17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) በዚያም ቀን ቍጣዬ ይነድድባቸዋል፤ እተዋቸውማለሁ፤ ፊቴንም ከእነርሱ እመልሳለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም መብል ይሆናሉ፤ በዚያም ቀን፦ በእውነት አምላካችን እግዚአብሔር ትቶናልና፥ በእኛም መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በዚያች ቀን እቈጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፣ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፣ አምላካችን ከእኛ ጋራ ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በዚያች ቀን እቀጣቸዋለሁ፤ እተዋቸዋለሁም፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይጠፋሉ። ብዙ ጥፋትና የከፋ ችግር ይደርስባቸዋል፤ በዚያችም ቀን፥ ‘ይህ ጥፋት የደረሰብን፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባለመሆኑ አይደለምን?’ ይላሉ። አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህም በሚሆንበት ጊዜ እኔ በእነርሱ ላይ ተቈጥቼ እለያቸዋለሁ፤ ፊቴን ከእነርሱ እሰውራለሁ፤ እነርሱም ይደመሰሳሉ፤ በእነርሱም ላይ ብዙ አሠቃቂ መቅሠፍት ይመጣባቸዋል፤ በዚያን ጊዜ፥ ‘ይህ ችግር የመጣብን አምላካችን በመካከላችን ስለሌለ አይደለምን?’ ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በዚያም ቀን ቁጣዬ ይነድድባቸዋል፥ እተዋቸውማለሁ፥ ፊቴንም እሰውርባቸዋለሁ፥ ለአሕዛብ መብል ይሆናሉ፤ በዚያም ቀን፦ በእውነት እግዚአብሔር በእኛ መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል። |
“አባቶቻችን በእርስዋ የተጻፈውን ሁሉ ይሠሩ ዘንድ የዚህችን መጽሐፍ ቃል ስላልሰሙ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ እኔና ስለ ሕዝቡ ስለ ይሁዳም ሁሉ ስለዚችም ስለተገኘችው መጽሐፍ ቃል ሁሉ እግዚአብሔርን ጠይቁ።
“አንተም ልጄ ሰሎሞን ሆይ፥ እግዚአብሔር ልብን ሁሉ ይመረምራልና፥ የነፍስንም አሳብ ሁሉ ያውቃልና የአባቶችህን አምላክ ዕወቅ፤ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም ተገዛለት፤ ብትፈልገው ታገኘዋለህ፤ ብትተወው ግን ለዘለዓለም ይተውሃል።
እርሱም ንጉሡን አሳን፥ የይሁዳንና የብንያምን ሕዝብ ሁሉ ሊገናኝ ወጣ፤ እንዲህም አለ፥ “አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ብትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል።
ኤዶምያስ ግን በይሁዳ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፀ፤ በዚያም ዘመን ልብና ደግሞ በእርሱ ላይ ዐመፀ፤ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ትቶ ነበርና።
የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በኢዮአዳ ልጅ በአዛርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆመና፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? መልካምም አይሆንላችሁም፤ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል” አላቸው።
“አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኀያል ጽኑዕና የተፈራኸው አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ በእኛና በነገሥታቶቻችን፥ በአለቆቻችንም፥ በካህናቶቻችንም፥ በነቢያቶቻችንም፥ በአባቶቻችንም፥ በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ።
ጥበብን አጽኑአት፤ እግዚአብሔር እንዳይቈጣ፥ እናንተም ከጽድቅ መንገድ እንዳትጠፉ፥ ቍጣው ፈጥና በነደደች ጊዜ፥ በእርሱ የታመኑ ሁሉ ብፁዓን ናቸው።
ሕዝቡን የያዕቆብን ቤት ትቶአልና፤ ምድራቸው እንደ ቀድሞው እንደ ፍልስጥኤማውያን ምድር በሟርት ተሞልቶአልና፤ እንደ ባዕድ ልጆችም ሆነዋልና፤ ብዙ እንግዶች ልጆችም ተወልደውላቸዋልና።
ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ታላቅ ቍጣን ተቈጣ፤ እጁንም በላያቸው ዘርግቶ መትቶአቸዋል፤ ተራሮችም ተንቀጠቀጡ፤ ሬሳቸውም በመንገድ መካከል እንደ ጕድፍ ሆኖአል። በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
አቤቱ፥ ከመንገድህ ለምን አሳትኸን? እንዳንፈራህም ልባችንን ለምን አጸናህብን? ስለ ባሪያዎችህ ስለ ርስትህ ነገዶች ተመለስ፤
ስምህንም የሚጠራ፥ አንተንም የሚያስብ የለም፤ ፊትህንም ከእኛ መልሰሃል፤ ለኀጢአታችንም አሳልፈህ ሰጥተኸናል።
ይህ ሕዝብ ወይም ነቢይ ወይም ካህን፥ “የእግዚአብሔር ሸክም ምንድር ነው?” ብሎ ቢጠይቅህ፥ አንተ፥ “ሸክሙ እናንተ ናችሁ፤ እጥላችሁማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር” ትላቸዋለህ።
ስለዚህ፥ እነሆ- ፈጽሜ እረሳችኋለሁ እናንተንም፥ ለእናንተና ለአባቶቻችሁም የሰጠኋትን ከተማ ከፊቴ አንሥቼ እጥላለሁ።
የከለዳውያን ተዋጊዎች ለመዋጋት መጥተዋል፤ ነገር ግን በቍጣዬና በመዓቴ በገደልኋቸው ሰዎች ሬሳዎች እሞላታለሁ፥ ስለ ክፋታቸው ሁሉ ፊቴን ከዚህች ከተማ እመልሳለሁ።
እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ልመናቸው በእግዚአብሔር ፊት ትደርስ ይሆናል፤ ሁሉም ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል።”
የአዛዦችም አለቃ ኤርምያስን ወሰደው፤ እንዲህም አለው፥ “አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር በዚህ ስፍራ ላይ ተናገረ።
እነሆ እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርስዋ ዘንድ የለምን? የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ ሀገር ተሰማ። በተቀረፁ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድን ነው?
ፊቴንም ከእነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አልመልስም፤ መዓቴን በእስራኤል ቤት ላይ አፍስሻለሁና፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የማይረባውን የሐሰት ቃል ይናገራሉ፤ ቃል ኪዳንም ያደርጋሉ፤ ስለዚህ መርዛም ሣር በእርሻ ትልም ላይ እንደሚበቅል ፍርድ ይበቅልባቸዋል።
የእግዚአብሔር ቍጣ፥ ቅንአቱም በዚያ ሰው ላይ ይነድዳል እንጂ እግዚአብሔር ይቅርታ አያደርግለትም፤ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈው ርግማን ሁሉ በላዩ ይኖራል፤ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል።
ፈጽመህ እንደምትጠፋ እኔ ዛሬ እነግርሃለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ዘመንህ አይረዝምም።
በፊትህ ሕይወትንና ሞትን፥ በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤
ከፊታቸው አትደንግጥ፤ አምላክህ እግዚአብሔር፥ ከአንተ ጋር ነውና፥ እርሱም አምላክህ እግዚአብሔር ታላቅና ጽኑዕ ነውና።
የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ በዓሊምንና አስታሮትን፥ የሶርያንም አማልክት፥ የሲዶናንም አማልክት፥ የሞዓብንም አማልክት፥ የአሞንንም ልጆች አማልክት፥ የፍልስጥኤማውያንንም አማልክት አመለኩ፤ እግዚአብሔርንም ተዉ፤ አላመለኩትምም።
ጌዴዎንም፥ “ጌታዬ ሆይ! እሺ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ፦ እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራት ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያም እጅም አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው።