ኤርምያስ 40 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤርምያስ ከጎዶልያስ ጋር እንደ ተቀመጠ 1 ወደ ባቢሎን በተማረኩት በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምርኮኞች መካከል የአዛዦች አለቃ ናቡዛርዳን በሰንሰለት አስሮ በወሰደው ጊዜ ከራማ ከለቀቀው በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2 የአዛዦችም አለቃ ኤርምያስን ወሰደው፤ እንዲህም አለው፥ “አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ክፉ ነገር በዚህ ስፍራ ላይ ተናገረ። 3 እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው አደረገ፤ እርሱን በድላችኋልና፥ ቃሉንም አልሰማችሁምና ይህ ነገር ሆነባችሁ። 4 አሁንም እነሆ በእጅህ ካለችው ሰንሰለት ዛሬ ፈታሁህ። ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ቢታይህ፥ ና፤ እኔም በመልካም አይሃለሁ፤ ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን መምጣት መልካም መስሎ ባይታይህ ግን፥ ተቀመጥ፤ ተመልከት፥ እነሆ፥ ሀገሪቱ ሁሉ በፊትህ ናት፤ ትሄድ ዘንድ መልካም መስሎ በሚታይህና ደስ በሚያሰኝህም ስፍራ ተቀመጥ።” 5 እርሱም ገና ሳይመለስ፥ “የባቢሎን ንጉሥ በይሁዳ ከተሞች ላይ ወደ ሾመው ወደ ሳፋን ልጅ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ተመለስ፤ ከእርሱም ጋር በሕዝቡ መካከል በይሁዳ ምድር ተቀመጥ፤ ወይም ትሄድ ዘንድ ለዐይንህ ደስ ወደሚያሰኝህ ስፍራ ሂድ” አለው። የአዛዦችም አለቃ ስንቅና ስጦታ ሰጥቶ አሰናበተው። 6 ኤርምያስም የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ወደ አለበት ወደ መሴፋ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር በሀገሩ ውስጥ በቀሩት ሕዝብ መካከል ተቀመጠ። ጎዶልያስ የይሁዳ ገዥ ሆኖ መሾሙ 7 በየሜዳው የነበሩት የጭፍራ አለቆችና ሰዎቻቸው ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሀገሩ ላይ እንደ ሾመ፥ ወንዶችንና ሴቶችን ልጆችንም፥ ወደ ባቢሎን ያልተማረኩትንም የምድርን ድሆች እንዳስጠበቀ በሰሙ ጊዜ፥ 8 የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃርሔም ልጆች ዮሐናንና ዮናታን፥ የተንሁሜትም ልጅ ሠራያ፥ የነጦፋዊውም የዮፌ ልጆች፥ የመከጢ ልጅ አዛንያም ከሰዎቻቸው ጋር ወደ ጎዶልያስ ወደ መሴፋ መጡ። 9 የሳፋንም ልጅ የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ለእነርሱና ለሰዎቻቸው እንዲህ ብሎ ማለ፥ “ለከለዳውያን ትገዙ ዘንድ አትፍሩ፤ በምድር ተቀመጡ፤ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፤ መልካምም ይሆንላችኋል። 10 እነሆ እኔም ወደ እኛ በሚመጡት ከለዳውያን ፊት እቆም ዘንድ በመሴፋ እኖራለሁ፤ እናንተ ግን ወይኑንና ፍሬውን፥ ዘይቱንም አከማቹ፤ በየዕቃችሁም ውስጥ ክተቱ፤ በያዛችኋቸውም ከተሞቻችሁ ተቀመጡ።” 11 በሞዓብና በአሞንም ልጆች መካከል፥ በኤዶምያስም፥ በምድርም ሁሉ ላይ የነበሩ አይሁድ ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ የይሁዳን ቅሬታ እንዳስቀረ፥ የሳፋንንም ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በላያቸው እንደ ሾመው ሰሙ። 12 አይሁድም ሁሉ ከተሰደዱበት ስፍራ ሁሉ ተመለሱ፤ ወደ ይሁዳም ሀገር ጎዶልያስ ወዳለበት ወደ መሴፋ መጡ፤ ወይንንና የበጋን ፍሬ፥ ዘይትንም እጅግ ብዙ አከማቹ። የጎዶልያስ መገደል 13 የቃርሔም ልጅ ዮሐናን፥ በየሜዳውም የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ ወደ ጎዶልያስ ወደ መሴፋ መጥተው፦ 14 “የአሞን ልጆች ንጉሥ በኣሊስ ይገድልህ ዘንድ የናታንያን ልጅ እስማኤልን እንደ ላከ ታውቃለህን?” አሉት። የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን አላመናቸውም። 15 የቃርሔም ልጅ ዮሐናን፥ “እባክህ፥ ልሂድ፤ ማንም ሳያውቅ የናታንያን ልጅ እስማኤልን ልግደለው፤ ወደ አንተ የተሰበሰቡ አይሁድ ሁሉ እንዲበተኑ፥ የይሁዳም ቅሬታ እንዲጠፋ ነፍስህን ስለ ምን ይገድላል?” ብሎ በመሴፋ በቈይታ ለጎዶልያስ ተናገረ። 16 የአኪቃም ልጅ ጎዶልያስ ግን የቃርሔን ልጅ ዮሐናንን፥ “በእስማኤል ላይ ሐሰት ተናግረሃልና ይህን ነገር አታድርግ” አለው። |