መዝሙር 90 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዳዊት የምስጋና መዝሙር። 1 በልዑል ረድኤት የሚያድር፥ በሰማይ አምላክ ጥላ ውስጥ የሚቀመጥ፥ 2 እግዚአብሔርን፥ “አንተ መጠጊያዬና አምባዬ ነህ፤ አምላኬና ረዳቴ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ” ይለዋል። 3 እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ፥ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድነኛልና። 4 በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። 5 ከሌሊት ግርማ፥ በመዓልት ከሚበርር ፍላጻ፥ 6 በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ሥራ፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። 7 በአጠገብህ ሺህ፥ በቀኝህም ዐሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርቡም። 8 በዐይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ፍዳ ታያለህ። 9 አቤቱ፥ አንተ ተስፋዬ ነህና፤ ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። 10 ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። 11 በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ 12 እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል። 13 በተኵላና በእባብ ላይ ትጫናለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ። 14 በእኔ ተማምኖአልና አድነዋለሁ ስሜንም አውቆአልና እጋርደዋለሁ። 15 ይጠራኛል እመልስለትማለሁ፥ በመከራውም ጊዜ ከእርሱ ጋር እሆናለሁ፤ አድነዋለሁ አከብረውማለሁ። 16 ረዥም ዕድሜን አጠግበዋለሁ፥ ማዳኔንም አሳየዋለሁ። |