ኢሳይያስ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢሳይያስ ልጅ ለሕዝቡ የምርኮ ምልክት እንደ ሆነ 1 እግዚአብሔርም አለኝ፥ “ታላቅ አዲስ ሰሌዳ ወስደህ፦ ‘ቸኩለህ ማርክ፤ ፈጥነህም በዝብዝ’ ብለህ በሰው ብርዕ ጻፍበት። 2 የታመኑትን ሰዎች ካህኑን ኦርያንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርግልኝ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ አድሮባቸዋልና፤” 3 ወደ ነቢዪቱም ቀረብሁ፤ እርስዋም ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች። እግዚአብሔርም አለኝ፥ “ስሙን ‘ቸኩለህ ማርክ፤ ፈጥነህም በዝብዝ’ ብለህ ጥራው። 4 ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና።” 5 እግዚአብሔርም ደግሞ ተናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፦ 6 “እኒህ ሕዝብ በቀስታ በሚሄደው በሰሊሆም ውኃ ቍርጥ ምክርን መከሩ፤ ረአሶንንና የሮሜልዩን ልጅ ያነግሡላቸው ዘንድ ይወዳሉና። 7 ስለዚህ፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውኃ፥ የአሦርን ንጉሥና ክብሩን ሁሉ ያመጣባቸዋል፤ ወንዙም ሞልቶ ይወጣል፤ በዳሮቻቸውም ሁሉ ላይ ይፈስሳል፤ 8 ከይሁዳ ወንድ ሰውን ሁሉ ያጠፋል፤ ኀያላኑንም ይጨርሳል፤ ሰፈሩም በሰፊው ምድርና በሀገሮቻቸው ሁሉ ይሞላል፤” እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና። 9 አሕዛብ ሆይ፥ ዕወቁና ደንግጡ፤ እስከ ምድር ዳርቻም ስሙ፤ ኀያላን! ድል ሁኑ፤ ዳግመኛም ብትበረቱ እንደ ገና ድል ትሆናላችሁ። 10 ምክርን ብትመክሩም እግዚአብሔር ምክራችሁን ይለውጣል፤ የተናገራችሁትም ነገር አይሆንላችሁም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና። 11 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ እንዲህ ተናገረኝ፤ በዚህም ሕዝብ መንገድ እንዳልሄድ አስጠነቀቀኝ፤ 12 እንዲህም አለኝ፥ “ይህ ሕዝብ፦ ከባድ ነው የሚለውን ሁሉ፦ ከባድ ነው አትበሉ፤ መፈራታቸውንም አትፍሩ፤ አትደንግጡም። 13 ነገር ግን የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፤ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁም እርሱ ይሁን። 14 ብታምንበት ይቀድስሃል፤ እንደ ድንጋይ ዕንቅፋትም አያደናቅፍህም፤ እንደሚያድጥ ዓለትም አይሆንብህም፤ ሁለቱ የያዕቆብ ቤቶች ግን በኢየሩሳሌም በወጥመድና በአሽክላ ተይዘው ይኖራሉ። 15 ስለዚህም ከእነርሱ ብዙዎች በእርሱ ይሰናከላሉ፤ ይወድቁማል፤ ይሰበሩማል፤ ይጠመዱማል፤ ይያዙማል።” 16 እንዳይማሩአት ሕግን የሚያጠፉአት ሰዎች ያንጊዜ ይገለጣሉ። 17 ከያዕቆብም ቤት ፊቱን የመለሰውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፥ እተማመንበትማለሁ። 18 እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን። 19 እነርሱም፥ “ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ” ባሉአችሁ ጊዜ፥ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን? 20 ነገሩ እንዲህ አይደለም ይሉ ዘንድ፥ ለእርሱም ግብር እንዳይሰጡ ሕግን ለርዳታ ሰጥቶአልና። 21 በዚህም በርግጥ ጽኑ ረኃብ ይመጣባችኋል፤ በተራባችሁም ጊዜ ትጨነቃላችሁ፤ በአለቆችና በመኳንንቱም ላይ ክፉ ትናገራላችሁ፤ ወደ ላይ ወደ ሰማይ ትመለከታላችሁ። 22 ወደ ታችም ወደ ምድር ትመለከታላችሁ፤ ድቅድቅ ጨለማንም ታያላችሁ፤ ታላቅ መከራንም ትቀበላላችሁ፤ ትጨነቃላችሁ፤ ትቸገራላችሁም፤ በፊታችሁም ጨለማ ይሆናል፤ አታዩምም፤ በመከራም ያለ ጊዜው እስኪደርስ አይድንም። |