ሆሴዕ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር ፍርድ በእስራኤል ጣዖት ላይ 1 እስራኤል ፍሬው የበዛለት የለመለመ ወይን ነው፤ እንደ ፍሬው ብዛት መሠዊያዉን አብዝቶአል፤ እንደ ምድሩም ማማር መጠን ሐውልቶችን ሠርተዋል። 2 ልባቸው ተከፈለ፤ አሁንም ይጠፋሉ፤ እርሱ መሠዊያቸውን ያፈርሳል፤ ሐውልቶቻቸውንም ያጠፋል። 3 አሁንም፥ “ንጉሥ የለንም፤ እግዚአብሔርን አልፈራንምና፤ ንጉሥስ ምን ያደርግልናል?” ይላሉ። 4 የማይረባውን የሐሰት ቃል ይናገራሉ፤ ቃል ኪዳንም ያደርጋሉ፤ ስለዚህ መርዛም ሣር በእርሻ ትልም ላይ እንደሚበቅል ፍርድ ይበቅልባቸዋል። 5 የሰማርያ ሰዎች በቤትአዌን እንቦሳ አጠገብ ይኖራሉ፤ ሕዝቡ ያለቅሱለታል፤ ክብሩም ከእርሱ ዘንድ ወጥቶአልና እንዳዘኑበት እንዲሁ በክብሩ ደስ ይላቸዋል። 6 ለንጉሡ ለኢያሪም እጅ መንሻ ይሆን ዘንድ አስረው ወደ አሦር ይወስዱታል፤ ኤፍሬምን እፍረት ይይዘዋል፤ እስራኤልም በምክሩ ያፍራል። 7 ሰማርያ ንጉሥዋን እንደ ጥራጊ በውኃ ላይ ጣለችው። 8 የእስራኤል ኀጢአት የሆኑት የአዎን የኮረብታው መስገጃዎች ይፈርሳሉ፤ እሾህና አሜከላም በመሠዊያዎቻቸው ላይ ይበቅላሉ፤ ተራሮችንም፥ “ክደኑን፤ ኮረብቶችንም፦ ውደቁብን” ይሉአቸዋል። 9 እስራኤል ከጊብዓ ዘመን ጀምሮ ኀጢአትን ሠርቶአል፤ በዚያም ጸንተዋል፤ በጊብዓ ላይ ጦር አይደርስባቸውምን? መጥቶም የዐመፅ ልጆችን ገሠጻቸው፤ 10 ስለ ሁለቱም ኀጢአቶቻቸው በገሠጻቸው ጊዜ አሕዛብ በላያቸው ይሰበሰቡባቸዋል። 11 ኤፍሬምም ቀንበርን እንደ ለመደች ጊደር ነው፤ እኔ ግን በአንገቱ ውበት እጫንበታለሁ፤ በኤፍሬም ላይ እጠምድበታለሁ፤ ይሁዳንም እለጕመዋለሁ፤ ያዕቆብም ለራሱ መንግሥትን ያስተካክላል። 12 ለእናንተ ጽድቅን ዝሩ፤ የሕይወት ፍሬን ሰብስቡ፤ የጥበብንም ብርሃን ለራሳችሁ አብሩ፤ የጽድቃችሁ መከር እስኪደርስ እግዚአብሔርን ፈልጉት። 13 ዐመፅን ለምን ተከላችሁ? ኀጢአትንስ ለምን አጨዳችሁ፤ የሐሰትንም ፍሬ በልታችኋል፤ በሠረገሎችህና በሠራዊትህ ብዛት ታምነሃል። 14 በሕዝብህም መካከል ጥፋት ይነሣል፤ እናትም በልጆችዋ ላይ በተጣለች ጊዜ የሰልማን አለቃ ቤትአርብኤልን በጦርነት ቀን እንዳፈረሰ፥ አምባዎችህ ሁሉ ይፈርሳሉ። 15 የእስራኤል ቤት ሆይ! ከኀጢአታችሁ ክፋት የተነሣ እንዲሁ አደርግባችኋለሁ፤ በነጋም ጊዜ የእስራኤልን ንጉሥ ይጥሉታል። |