ዘኍል 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሕዝቡ ዐመፅ 1 ማኅበሩም ሁሉ ድምፃቸውን አንስተው ጮኹ፤ ሕዝቡም ሌሊቱን ሁሉ አለቀሱ። 2 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ፤ ማኅበሩም ሁሉ፥ “በዚህ ምድረ በዳ ከምንሞት በግብፅ ምድር ሳለን ብንሞት በተሻለን ነበር። 3 እግዚአብሔርም በጦርነት እንሞት ዘንድ ወደዚች ምድር ለምን ያገባናል? ሴቶቻችንና ልጆቻችን ለንጥቂያ ይሆናሉ፤ አሁንም ወደ ግብፅ መመለስ አይሻለንምን?” አሉአቸው። 4 እርስ በርሳቸውም፥ “ኑ፥ አለቃ ሾመን ወደ ግብፅ እንመለስ” ተባባሉ። 5 ሙሴና አሮንም በእስራኤል ልጆች ጉባኤ ፊት በግንባራቸው ወደቁ። 6 ምድሪቱን ከሰለሉት ጋር የነበሩት የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ 7 ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ “የሰለልናት ምድር እጅግ በጣም መልካም ናት። 8 እግዚአብሔርስ ከመረጠን ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ወደዚች ምድር ያገባናል፤ እርስዋንም ይሰጠናል። 9 ነገር ግን እናንተ በእግዚአብሔር ላይ አታምፁ፤ እኛ እናጠፋቸዋለንና የምድሪቱን ሰዎች አትፍሩ፤ ጊዜአቸው አልፎባቸዋል፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ጋር ነው፤ አትፍሩአቸው” ብለው ተናገሩአቸው። 10 ማኅበሩ ሁሉ ግን “በድንጋይ እንውገራቸው” አሉ። የእግዚአብሔርም ክብር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በምስክሩ ድንኳን ተገለጠ። ሙሴ ስለ ሕዝቡ እንደ ጸለየ 11 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እኒህ ሕዝብ እስከ መቼ ያስቈጡኛል? በፊታቸውስ ባደረግሁት ተአምራት ሁሉ እስከ መቼ አያምኑብኝም? 12 በሞት እቀጣቸዋለሁ፤ አጠፋቸዋለሁም፤ አንተንና የአባትህን ቤት ግን ለታላቅና ከዚህ ለሚበዛ ሕዝብ አደርግሃለሁ” አለው። 13 ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፥ “ግብፃውያን ይሰማሉ፤ እኒህን ሕዝብ ከእነርሱ በኀይልህ አውጥተኻቸዋልና፤ 14 የዚያች ምድር ሰዎች፥ አንተ እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብህ መካከል እንደ ሆንህ ሰምተዋል፤ አንተም፥ አቤቱ፥ ዐይን በዐይን እንደሚተያይ ተገልጠህላቸዋል። ደመናህም በላያቸው ቆመች። በቀንም በደመና ዐምድ ፥ በሌሊትም በእሳት ዐምድ በፊታቸው ትሄዳለህ። 15 እኒህን ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ብትገድል ስምህን የሰሙ አሕዛብ፦ 16 እግዚአብሔር ‘እነዚህን ሕዝብ ወደ ማለላቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና በምድረ በዳ ገደላቸው’ ብለው ይናገራሉ። 17 አሁንም አቤቱ፥ ኀይልህ ይገለጥ፤ እንዲህ ብለህ እንደ ተናገርህ፦ 18 እግዚአብሔር መዓቱ የራቀ ምሕረቱ የበዛ ጻድቅ፥ አበሳን፥ መተላለፍንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፥ ኀጢአተኞችንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኀጢአት እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው። 19 እነዚህን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ካወጣህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይቅር እንዳልሃቸው፥ እንደ ምሕረትህ ብዛት የእነዚህን ሕዝብ ኀጢአት ይቅር በል።” 20 እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “እንደ ቃልህ ይቅር አልሁ፤ 21 ነገር ግን እኔ ሕያው ነኝ፤ ስሜም ሕያው ነው፤ በእውነት የእግዚአብሔር ክብር ምድርን ሁሉ ይሞላል። 22 በግብፅ ምድርና በምድረ በዳ ያደረግሁትን ተአምራቴንና ክብሬን ያዩ እነዚህ ሰዎች ሁሉ ዐሥር ጊዜ ስለ ተፈታተኑኝ፥ ቃሌንም ስላልሰሙ፥ 23 በእውነት ለአባቶቻቸው የማልሁላቸውን ምድር አያዩም፤ ከእኔ ጋር በዚህ ላሉ መልካምንና ክፉን ለይተው ለማያውቁ ልጆቻቸው፥ የሚያውቀው ለሌለ ለታናሹ ሁሉ ያችን ሀገር እሰጣታለሁ፤ ለጥፋት ያነሳሱኝ ሁሉ አያዩአትም። 24 ወዳጄ ካሌብ ግን ሌላ መንፈስ በእርሱ ላይ ስለ ሆነና ስለ ተከተለኝ እርሱ ወደ ገባባት ምድር አገባዋለሁ፤ ዘሩም ይወርሳታል። 25 ዐማሌቅና ከነዓናዊውም በሸለቆ ውስጥ ተቀምጠዋል፤ እናንተ ግን ነገ ተመልሳችሁ በኤርትራ ባሕር መንገድ ወደ ምድረ በዳ ሂዱ።” የዐመፁት ሕዝብ እንደ ተቀጡ 26 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 27 “የሚያጕረመርሙብኝን እኒህን ክፉ ማኅበር እስከ መቼ እታገሣቸዋለሁ? ስለ እናንተ በእኔ ላይ የሚያጕረመርሙትን የእስራኤል ልጆች ማጕረምረምን ሰማሁ። 28 እንዲህ በላቸው፦ እኔ ሕያው ነኝና በጆሮዬ እንደ ተናገራችሁት እንዲሁ በእውነት አደርግባችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 29 በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ፤ የተቈጠራችሁ ሁሉ፥ እንደ ቍጥራችሁ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ፥ እናንተ ያጕረመረማችሁብኝ፥ 30 ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር በእርስዋ አስቀምጣችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቼ ወደ ማልሁላችሁ ምድር በእውነት እናንተ አትገቡም። 31 ንጥቂያ ይሆናሉ ያላችኋቸውን ልጆቻችሁን እነርሱን አገባቸዋለሁ፤ እናንተም የናቃችኋትን ምድር ይወርሷታል። 32 የእናንተ ግን በድኖቻችሁ በዚህ ምድረ በዳ ይወድቃሉ። 33 ልጆቻችሁም በምድረ በዳ አርባ ዓመት ይቅበዘበዛሉ፤ በድኖቻችሁም በምድረ በዳ እስኪጠፉ ድረስ ግልሙትናችሁን ይሸከማሉ። 34 ምድሪቱን እንደ ሰለሉባቸው እንደ እነዚያ አርባ ቀኖች ቍጥር ስለ ኀጢአታችሁ ሁሉ አርባው ቀን አርባ ዓመት፥ አንዱ ቀንም አንድ ዓመት ይሁንባችሁ፤ እንግዲህ የቍጣዬን መቅሠፍት ታውቃላችሁ። 35 እኔ እግዚአብሔር፦ በእኔ ላይ በተሰበሰበ በዚህ ክፉ ማኅበር ሁሉ ላይ እንዲህ አደርጋለሁ ብዬ ተናገርሁ፤ በዚህ ምድረ በዳ ያልቃሉ፤ በዚያም ይሞታሉ።” 36 ምድሪቱንም ሊሰልሉ ሙሴ ልኮአቸው የተመለሱት ሰዎች ስለ እርስዋ በማኅበሩ ሁሉ ፊት አጕረመረሙ። 37 ስለዚያችም ምድር ክፉን ነገር ተናገሩ፤ ስለዚያችም ምድር ክፉ የተናገሩ እነዚያ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት በመቅሠፍት ሞቱ፤ ምድሪቱ ግን መልካም ነበረች። 38 ነገር ግን ምድሪቱን ሊሰልሉ ከሄዱ ሰዎች የነዌ ልጅ ኢያሱና የዮፎኒ ልጅ ካሌብ በሕይወት ኖሩ። ምድሪቱን ለመያዝ የመጀመሪያ ሙከራ ( ዘዳ. 1፥4-46 ) 39 ሙሴም ይህን ነገር ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ነገረ። ሕዝቡም እጅግ አዘኑ፤ 40 በነጋውም ማልደው ተነሡ፤ ወደ ተራራውም ራስ ወጥተው፥ “እነሆ፥ እኛ ከዚህ አለን፤ በድለናልና እግዚአብሔር ወዳለው ስፍራ እንወጣለን” አሉ። 41 ሙሴም አለ፥ “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? ይህ ለእናንተ መልካም አይደለም። 42 እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይደለምና በጠላቶቻችሁ ፊት እንዳትወድቁ አትውጡ። 43 ዐማሌቃዊና ከነዓናዊ በፊታችሁ ናቸውና በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ እግዚአብሔርን ከመከተል ተመልሳችኋልና እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር አይሆንም።” 44 እነርሱ ግን ተደፋፍረው ወደ ተራራው ራስ ወጡ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦትና ሙሴ ከሰፈሩ አልተንቀሳቀሱም። 45 በዚያም ተራራ ላይ የተቀመጡ ዐማሌቃዊና ከነዓናዊ ወረዱ፤ መትተዋቸውም እስከ ኤርማ ድረስ አሳደዱአቸው። ወደ ከተማም ተመለሱ። |