ዘዳግም 30 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ወደ እግዚአብሔር በመመለስ የሚገኝ በረከት 1 “እንዲህም ይሆናል፤ እኔ በፊትህ ያኖርሁት ይህ ነገር ሁሉ፥ በረከቱና መርገሙ በወረደብህ ጊዜ፥ አምላክህ እግዚአብሔር በሚበትንህ በዚያ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ሆነህ በልብህ ዐስበው፤ 2 ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔርም ተመለስ፤ እኔም ዛሬ እንደማዝዝህ ሁሉ አንተና ልጆችህ በፍጹም ልብና በፍጹም ነፍስ ቃሉን ስማ፤ 3 እግዚአብሔርም ኀጢአትህን ይቅር ይልሃል ይራራልህማል፤ እግዚአብሔርም አንተን ከበተነበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መልሶ ይሰበስብሃል። 4 መበተንህም እስከ ሰማይ ዳርቻ ቢሆን አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፤ ከዚያም ያመጣሃል። 5 አባቶችህም ወደ ወረሱአት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር ይወስድሃል፤ ትወርሳትማለህ፤ መልካምም ነገር ያደርግልሃል፤ ከአባቶችህም ይልቅ ያበዛሃል። 6 በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርንም በፍጹም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ እግዚአብሔር ልብህን፥ የዘርህንም ልብ ያጠራዋል። 7 አምላክህም እግዚአብሔር ይህችን መርገም ሁሉ በጠላቶችህና በሚጠሉህ በሚያሳድዱህም ላይ ያመጣታል። 8 አንተም ተመልሰህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ትሰማለህ፤ ዛሬም እኔ የማዝዝህን ትእዛዙን ሁሉ ታደርጋለህ። 9 እግዚአብሔርም በአባቶችህ ደስ እንዳለው በመልካሙ ነገር ሁሉ እንደ ገና በአንተ ደስ ይለዋልና አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ፥ በሆድህም ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ በከብትህም ብዛት እጅግ ይባርክሃል። 10 በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙን፥ ሥርዐቱንና ፍርዱን ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ በፍጹም ልብህ፥ በፍጹምም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ብትመለስ ይባርክሃል። ሕይወትና ሞት 11 “እኔ ዛሬ የማዝዝህ ይህች ትእዛዝ ከባድ አይደለችም፤ ከአንተም የራቀች አይደለችም። 12 ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ወደ ሰማይ ወጥቶ እርስዋን የሚያመጣልን ማንነው? እንዳትል በሰማይ አይደለችም። 13 ሰምተን እናደርጋት ዘንድ ስለ እኛ ባሕሩን ተሻግሮ እርስዋን የሚያመጣልን ማን ነው? እንዳትል ከባሕሩ ማዶ አይደለችም። 14 ታደርገው ዘንድ ቃሉ በአፍህና በልብህ፥ በእጅህም ውስጥ ለአንተ እጅግ ቅርብ ነው። 15 “እነሆ፥ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና ሞትን፥ መልካምነትንና ክፉነትን አኑሬአለሁ። 16 ዛሬ እኔ የማዝዝህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ብትሰማ፥ አምላክህን እግዚአብሔርንም ብትወድድ፥ በመንገዶቹም ሁሉ ብትሄድ፥ ሥርዐቱንና ፍርዱንም ብትጠብቅ በሕይወት ትኖራለህ፤ በቍጥርም ትበዛለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔርም ልትወርሳት በምትሄድባት በምድሪቱ ሁሉ ይባርክሃል። 17 ልብህ ግን ቢስት፥ አንተም ባትሰማ፥ ብትታለልም፥ ለሌሎች አማልክትም ብትሰግድ፥ ብታመልካቸውም፥ 18 ፈጽመህ እንደምትጠፋ እኔ ዛሬ እነግርሃለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ዘመንህ አይረዝምም። 19 በፊትህ ሕይወትንና ሞትን፥ በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ፤ 20 እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ፥ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ውደደው፤ ቃሉን ስማው፤ አጥናውም።” |