ዘዳግም 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በሞአብ ምድረ በዳ የተሰጠ ቃል ኪዳን 1 እግዚአብሔር በኮሬብ ካደረገው ቃል ኪዳን ሌላ በሞዓብ ምድር ከእስራኤል ልጆች ጋር ያደርገው ዘንድ ሙሴን ያዘዘው የቃል ኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው። 2 ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ሁሉ ጠርቶ አላቸው፥ “እግዚአብሔር በፊታችሁ በግብፅ ምድር፥ በፈርዖንና በሹሞቹ ሁሉ፥ በምድሩም ሁሉ ያደረገውን ሁሉ፥ 3 ዐይኖቻችሁም ያዩአቸውን ታላላቆች ፈተናዎችን፥ ታላላቆች ተአምራትንና ድንቆችን አይታችኋል። 4 እግዚአብሔር ግን ታስተውሉ ዘንድ ልብን፥ ታዩም ዘንድ ዐይንን፥ ትሰሙም ዘንድ ጆሮዎችን እስከ ዛሬ ድረስ አልሰጣችሁም። 5 አርባ ዓመት በምድረ በዳ መራችሁ፤ ልብሳችሁም አላረጀባችሁም፤ ጫማችሁም በእግራችሁ ላይ አልተቀደደም። 6 አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እዚህ ቦታ እስክትደርሱ ድረስ እንጀራ አልበላችሁም፤ የወይን ጠጅና የሚያሰክረውን መጠጥም አልጠጣችሁም። 7 የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን፥ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ሊወጉን ወጡብን፤ እኛም መታናቸው፤ 8 ምድራቸውንም ወስደን ለሮቤልና ለጋድ፥ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠናቸው። 9 የምታደርጉት ሁሉ ይከናወንላችሁ ዘንድ የዚህን ቃል ኪዳን ቃሎች ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ። 10 ሁላችሁ፥ የነገዶቻችሁ አለቆች ሽማግሌዎቻችሁም፥ ሹሞቻችሁም፥ ጻፎቻችሁም፥ የእስራኤል ወንድ ሁሉ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቆማችኋል። 11 ሴቶቻችሁም፥ ልጆቻችሁም ከእንጨት ለቃሚያችሁ እስከ ውኃ ቀጃችሁ በሰፈራችሁ ያለ መጻተኛ፤ 12 ይኸውም አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ዛሬ በሚያደርገው ቃል ኪዳንና አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር በተማማለው መሐላ ትገባ ዘንድ ነው። 13 ዛሬ ለእርሱ ሕዝብ ያደርግህ ዘንድ፥ እርሱም ለአንተ እንደ ተናገረ ለአባቶችህም ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንደ ማለ አምላክ ይሆንልህ ዘንድ ነው። 14 “እኔም ይህን ቃል ኪዳንና ይህን መሐላ የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤ 15 ነገር ግን ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ከእኛ ጋር በዚህ ከሚቆም ሰው ጋር፥ ዛሬም ከእኛ ጋር በዚህ ከሌለ ሰው ጋር ነው እንጂ፤ 16 ነገር ግን እኛ በግብፅ ምድር እንደ ተቀመጥን በመካከላቸውም ባለፋችሁባቸው አሕዛብ መካከል እንዳለፍን ዐውቃችኋልና፥ 17 ርኩስነታቸውንም፥ በእነርሱም ዘንድ የነበሩትን የእንጨትና የድንጋይ፥ የብርና የወርቅም ጣዖቶቻቸውን አይታችኋልና፥ 18 ሄዶ የእነዚያን አሕዛብ አማልክት ያመልክ ዘንድ ከአምላካችሁ ከእግዚአብሔር ልቡን ዛሬ የሚያስት ወንድ ወይም ሴት ወይም ወገን ወይም ነገድ አይኑርባችሁ፤ ሐሞትና እሬትም የሚያበቅል ሥር አይሁንባችሁ። 19 “የዚህንም ርግማን ቃሎች በሰማችሁ ጊዜ በልቡ ‘ይህን በልቤ ስንፍና በማድረግ ሄጃለሁና ይቅር ይለኛል’ የሚል ቢኖር የበደለኛ ፍዳ ካልበደለ ጋር እንዳይተካከል፥ 20 የእግዚአብሔር ቍጣ፥ ቅንአቱም በዚያ ሰው ላይ ይነድዳል እንጂ እግዚአብሔር ይቅርታ አያደርግለትም፤ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈው ርግማን ሁሉ በላዩ ይኖራል፤ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል። 21 እግዚአብሔርም በዚህ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው እንደ ቃል ኪዳኑ ርግማን ሁሉ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል። 22 “ከዚያም በኋላ የሚነሣ ትውልድ፥ ከእናንተም በኋላ የሚሆኑ ልጆቻችሁ ከሩቅ ሀገርም የሚመጣ እንግዳ፥ የዚችን ሀገር መቅሠፍት፥ እግዚአብሔርም በላይዋ የላከውን ሥቃይዋን፥ 23 ምድርም በሁለንተናዋ ዲንና ጨው፥ መቃጠልም እንደ ሆነባት፥ እንዳይዘራባትም፥ እንዳታበቅልም፥ ማናቸውም ሣርና ልምላሜም እንዳይወጣባት፥ እግዚአብሔር በቍጣውና በመዓቱ እንደ ገለበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ፥ እንደ አዳማና እንደ ሲባዮ እንደ ሆነች ባዩ ጊዜ፥ 24 አሕዛብ ሁሉ እግዚአብሔር በዚህች ምድር ስለ ምን እንደዚህ አደረገ? ይህስ የቍጣው ታላቅ መቅሠፍት ምንድን ነው? ይላሉ። 25 ሰዎችም እንዲህ ይላሉ፦ የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻቸው ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ስለተዉ፥ 26 ሄደውም የማያውቋቸውንና የማይጠቅሟቸውን ሌሎችን አማልክት ስላመለኩና ስለ ሰገዱላቸው፥ 27 ስለዚህ በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን መርገም ሁሉ ያመጣባት ዘንድ የእግዚአብሔር ቍጣ በዚህች ምድር ነደደ፤ 28 ዛሬም እንዳሉ እግዚአብሔር በቍጣና በመቅሠፍት፥ በታላቅም መዓት ከምድራቸው ነቀላቸው፤ ወደ ሌላም ምድር ጣላቸው። 29 “ምስጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛና ለልጆቻችን ለዘለዓለም ነው። |