ኤርምያስ 36 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ባሮክ የተጠቀለለውን ብራና በቤተ መቅደስ እንዳነበበውና ንጉሡ እንዳቃጠለው 1 እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመተ መንግሥት ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 2 “አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት። 3 ምናልባት የይሁዳ ቤት ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ፥ እኔም በደላቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ፥ እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል።” 4 ኤርምያስም የኔርዩን ልጅ ባሮክን ጠራ፤ ባሮክም እግዚአብሔር ለእርሱ የተናገረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ በመጽሐፉ ክርታስ ጻፈ። 5 ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ ሲል አዘዘው፥ “እኔ እስረኛ ነኝ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤትም እገባ ዘንድ አልችልም። 6 አንተ ግን ገብተህ ከአፌ የጻፍኸውን የእግዚአብሔርን ቃል በጾም ቀን በእግዚአብሔር ቤት በሕዝቡ ጆሮ በክርታሱ አንብብ፤ ደግሞም ከከተሞቻቸው በሚወጡ በይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጆሮ አንብበው። 7 እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ልመናቸው በእግዚአብሔር ፊት ትደርስ ይሆናል፤ ሁሉም ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል።” 8 የኔርዩም ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ቤት የእግዚአብሔርን ቃል በመጽሐፉ አነበበ። 9 እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት በዘጠነኛው ወር በኢየሩሳሌም የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፥ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለመጾም ዐዋጅ ነገሩ። 10 ባሮክም የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሔር ቤት በላይኛው አደባባይ በእግዚአብሔር ቤት በአዲሱ በር መግቢያ ባለው በጸሓፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ክፍል በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ በመጽሐፉ አንበበ። 11 የሳፋንም ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመጽሐፉ ሰማ። 12 ወደ ንጉሡም ቤት ወደ ጸሓፊው ክፍል ወረደ፤ እነሆም አለቆቹ ሁሉ፥ ጸሓፊው ኤሊሳማ፥ የሸማያ ልጅ ድላያ፥ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፥ የሳፋን ልጅ ገማርያ፥ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ፥ አለቆቹም ሁሉ በዚያ ተቀምጠው ነበር። 13 ሚክያስም ባሮክ በሕዝቡ ጆሮ በመጽሐፉ በአነበበ ጊዜ የሰማውን ቃል ሁሉ ነገራቸው። 14 አለቆቹም ሁሉ፥ “በሕዝቡ ጆሮ ያነበብኸውን ክርታስ በእጅህ ይዘህ ና” ብለው የኩሲ ልጅ የሰሌምያ ልጅ የናታንያ ልጅ ይሁዳን ወደ ኔርዩ ልጅ ወደ ባሮክ ላኩ። የኔርዩም ልጅ ባሮክ ክርታሱን በእጁ ይዞ ወደ እነርሱ ወረደ። 15 እነርሱም፥ “እስኪ ተቀመጥ፤ በጆሮአችንም አንብብ” አሉት። ባሮክም በጆሮአቸው አነበበው። 16 እንዲህም ሆነ፦ ቃሉን ሁሉ በሰሙ ጊዜ ፈርተው እርስ በርሳቸው ተመካከሩ፤ ባሮክንም፥ “ይህን ቃል ሁሉ በርግጥ ለንጉሡ እንናገራለን” አሉት። 17 ባሮክንም፥ “ይህን ቃል ሁሉ እንዴት እንደ ጻፍኸው ንገረን” ብለው ጠየቁት። 18 ባሮክም፥ “ኤርምያስ ይህን ቃል ከአፉ ይነግረኝ ነበር፤ እኔም በመጽሐፉ ላይ እጽፍ ነበር” ብሎ መለሰላቸው። 19 አለቆቹም ባሮክን፥ “አንተና ኤርምያስ ሂዱ፤ ተሸሸጉ፤ ወዴትም እንደ ሆናችሁ ማንም አይወቅ” አሉት። 20 ወደ ንጉሡም ወደ አደባባይ ገቡ፥ ክርታሱንም በጸሓፊው በኤሊሳማ ክፍል አኑረውት ነበር፤ ቃሉንም ሁሉ ለንጉሡ ተናገሩ። 21 ንጉሡም ክርታሱን ያመጣ ዘንድ ይሁዳን ላከ፤ እርሱም ከጸሓፊው ከኤሊሳማ ክፍል ወሰደው፤ ይሁዳም በንጉሡና በንጉሡ አጠገብ በቆሙት አለቆች ሁሉ ጆሮ አነበበው። 22 ንጉሡም በዘጠነኛው ወር በክረምት በሚቀመጥበት ቤት ተቀምጦ ነበር፤ በፊቱም እሳት ይነድድ ነበር። 23 ይሁዳም ሦስትና አራት ዐምድ ያህል በአነበበ ቍጥር፥ ንጉሡ በብርዕ መቍረጫ ቀደደው፤ ክርታሱንም በምድጃ ውስጥ በአለው እሳት ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወደ አለው እሳት ጣለው። 24 ንጉሡም፥ ይህንም ቃል ሁሉ የሰሙ አገልጋዮቹ ሁሉ አልደነገጡም፤ ልብሳቸውንም አልቀደዱም። 25 ነገር ግን ኤልናታንና ጎዶልያ፥ ገማርያም ክርታሱን እንዳያቃጥል ንጉሡን ለመኑት፤ እርሱ ግን አልሰማቸውም። 26 ንጉሡም ጸሓፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን ይይዙ ዘንድ የንጉሡን ልጅ ይረሕምኤልንና የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያን የዓብድኤልንም ልጅ ሰሌምያን አዘዘ፤ እግዚአብሔር ግን ሰወራቸው። የተቃጠለው መጽሐፍ እንደ ገና እንደ ተጻፈ 27 ንጉሡም፥ ባሮክ ከኤርምያስ አፍ የጻፈው ቃል ያለበትን ክርታስ ካቃጠለ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 28 “ዳግመኛም ሌላ ክርታስ ውሰድ፤ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአቄም በአቃጠለው ክርታስ ላይ የነበረውን የቀድሞውን ቃል ሁሉ ጻፍበት። 29 የይሁዳንም ንጉሥ ኢዮአቄምን እንዲህ በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ፦ የባቢሎን ንጉሥ በርግጥ ይመጣል፤ ይችንም ሀገር ያፈርሳታል፤ ሰውና እንስሳም ያልቃሉ ብለህ ለምን ጻፍህበት? ብለህ ይህን ክርታስ አቃጥለሃል። 30 ስለዚህም ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ልጅ አይኖርለትም፥ ሬሳውም በቀን ለትኩሳት፥ በሌሊትም ለውርጭ ይጣላል። 31 ስለ ኀጢአታቸውም እርሱንና ዘሩን አገልጋዮቹንም በመዓት እጐበኛለሁ፤ እነርሱም አልሰሙምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይና በኢየሩሳሌም በሚቀመጡ በይሁዳም ሰዎች ላይ አመጣለሁ።” 32 ኤርምያስም ሌላ ክርታስ ወሰደ፤ ለኔርዩም ልጅ ለጸሓፊው ለባሮክ ሰጠው፤ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የመጽሐፉን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ጻፈበት፤ ደግሞም እንደ ቀድሞው ያለ ቃል ብዙ ቃል ተጨመረበት። |