ኢሳይያስ 1:4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እናንተ ኃጢአተኞች በደልን የተሸከማችሁ ወገኖች! የክፉ አድራጊዎችም ትውልድ! ሕይወታችሁ የተበላሸ፥ እግዚአብሔርን የተዋችሁና የእስራኤልን ቅዱስ የናቃችሁ በእርሱም ላይ ጀርባችሁን ያዞራችሁ ናችሁ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፣ በደል የሞላበት ወገን፣ የክፉ አድራጊ ዘር፣ ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል፤ የእስራኤልን ቅዱስ አቃልለዋል፤ ጀርባቸውንም በርሱ ላይ አዙረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) እናንተ ኀጢአተኛ ሕዝብ፤ በደል የሞላበት ወገን፤ የክፉ አድራጊ ዘር፤ ምግባረ ብልሹ ልጆች ወዮላችሁ! ጌታን ትተዋል፤ የእስራኤልን ቅዱስ አቃለዋል፤ ጀርባቸውንም በእርሱ ላይ አዙረዋል። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ኀጢአተኛ ወገንና ዐመፅ የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ በደለኞች ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ተዋችሁት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ አስቈጣችሁት። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ኃጢአተኛ ወገንና በደል የተሞላበት ሕዝብ፥ የክፉዎች ዘር፥ ርኵሰትን የምታደርጉ ልጆች ሆይ፥ ወዮላችሁ! እግዚአብሔርን ትተዋል የእስራኤልንም ቅዱስ አቃልለዋል ወደ ኋላቸውም እየሄዱ ተለይተዋል። |
ኢዮአታም አባቱ እንዳደረገው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር ሠራ፤ አባቱ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ዕጣን በማጠን ያደረገውን ኃጢአትም አልሠራም፤ ሕዝቡ ግን ኃጢአት መሥራቱን ቀጥሎ ነበር።
እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው ዐመፀኞችና እምቢተኞች አይሆኑም፤ እነዚያ እግዚአብሔርን በማመን የጸኑ አልነበሩም፤ ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው አልኖሩም።
መሪዎችሽ ዐመፀኞችና የሌቦች ግብረ አበሮች ሆኑ፤ እያንዳንዱ ሁልጊዜ ገጸ በረከትና ጉቦ ይቀበላል፤ አባትና እናት የሞቱባቸውን ልጆች መብት አይጠብቁም፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸውንም ሴቶች አቤቱታ አይሰሙም።
ሀብታቸውን ዘርፈውና መዝብረው ሕዝቡን እንደ መንገድ ላይ ጭቃ እንዲረግጡ በከሐዲውና ቊጣዬንም ባነሣሣው ሕዝብ ላይ አሦራውያንን አስነሥቼ እልካቸዋለሁ።”
አንተ አገርህን አጥፍተህ፥ የገዛ ሕዝብህን ፈጅተሃል፤ ስለዚህም አንተ እንደ ሌሎች መንግሥታት መቃብር የማግኘት ዕድል አይኖርህም፤ ከክፉ ቤተሰብ መካከል የሚተርፍ ዘር አይኖርም።
ኢየሩሳሌም ተሰናክላ በመንገዳገድ ላይ ናት፤ ይሁዳም ልትወድቅ ተቃርባለች፤ ምክንያቱም የሚናገሩትም ሆነ የሚሠሩት ሁሉ እግዚአብሔርን በመፈታተን ስለ ሆነ ክብሩን አቃለዋል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዐመፀኞች ለሆኑ ልጆች ወዮላቸው! እኔ ባላወጣሁላቸው ዕቅድ መመራት ይፈልጋሉ፤ ከእኔም ፈቃድ ውጪ የቃል ኪዳን ውል በመፈጸም በኃጢአት ላይ ኃጢአት ይጨምራሉ።
የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በመመለስና በማረፍ ደኅንነትን ታገኛላችሁ፤ ጸጥ በማለትና በመታመን ኀይል ታገኛላችሁ፤ እናንተ ግን እምቢ አላችሁ።
ዐይንህን በትዕቢት አቅንተህ፥ ድምፅህን ከፍ አድርገህ በመጮኽ የተዳፈርከውና የተሳደብከው ማንን ይመስልሃል? የእስራኤልን ቅዱስ አይደለምን?’
ወደ ሰማይ ትበትናቸዋለህ፤ ነፋስም ጠራርጎ ይወስዳቸዋል፤ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፤ በእኔ በእስራኤል ቅዱስም ትመካለህ።
ይህን የማደርገው የእኔ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገና እኔም የእስራኤል ቅዱስ እንደ ፈጠርኩት ሁሉም አይተው ያውቁ ዘንድ፥ አስተውለውም ይረዱ ዘንድ ነው።”
“እኛ በዐይናችን እናያት ዘንድ እግዚአብሔር ሊያደርግ ያቀደውን በፍጥነት ያድርግ፤ እናውቃትም ዘንድ የእስራኤል ቅዱስ ያቀዳት ምክር ትፈጸም” ለሚሉ ሁሉ ወዮላቸው!
የእስራኤል ቅዱስ የሠራዊት አምላክ ያዘዘውን ሕግና ያስተማረውን ሥርዓት ስለ አቃለሉ ገለባና ድርቆሽ በእሳት ጋይቶ እንደሚጠፋ የእነርሱም ሥር መሠረት በስብሶ ይጠፋል፤ አበባቸውም ደርቆ እንደ ትቢያ ይበናል።
ክፉ በሆነው ስግብግብነታቸው ምክንያት በእነርሱ ላይ ተቈጥቼ ነበር፤ እንዲሁም እነርሱን ቀጥቼ ተለይቼአቸው ነበር፤ እነርሱም ወደ ራሳቸው መንገድ ተመለሱ።
ሆኖም ዕለት በዕለት ይሹኛል፤ መንገዶቼንም ማወቅ ደስ ይላቸዋል፤ ጽድቅን እንደሚያዘወትሩና የእኔን የአምላካቸውን ትእዛዝ እንዳልተወ ሕዝብ ከእኔ ትክክለኛውን ፍርድ ይለምናሉ፤ ወደ እኔ ወደ አምላክም በመቅረብ ይደሰታሉ።”
“እኔን እግዚአብሔርን ትታችሁ የተቀደሰ ተራራዬን በመርሳት ‘መልካም አጋጣሚ’ ለተባለ ጣዖትም ማእድ ታዘጋጃላችሁ፤ ‘ዕድል ፈንታ’ ለተባለ ጣዖትም ዋንጫችሁን በተደባለቀ የወይን ጠጅ ትሞላላችሁ።
ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ወጣቶቻቸውን ይቀጣል፤ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶችና አሳዳጊ ለሌላቸው ለሙት ልጆቻቸው አይራራም፤ ሁሉም እያንዳንዱ ከሐዲና ክፉ አድራጊ ሆኖአል፤ ከእያንዳንዱም ሰው አንደበት የሚነገረው ቃል ተንኰል የሞላበት ነው፤ ይህም ሁሉ ሆኖ የእግዚአብሔር ቊጣ ገና አልበረደም፤ ስለዚህ እነርሱን ለመቅጣት እጁ እንደ ተቃጣ ነው።
ሕዝቤ ሁለት ኃጢአት ሠርተዋል፤ ይኸውም የሕይወት ውሃ ምንጭ የሆንኩትን እኔን ትተውኛል፤ ውሃ መቋጠር የማይችሉ የተሸነቈሩ ጒድጓዶችን ለራሳቸው ቆፍረዋል።”
እነሆ የራስሽ ክፋት ይቀጣሻል፤ ክሕደትሽ ይፈርድብሻል፤ እኔን አምላክሽን እግዚአብሔርን መተውሽና ለእኔም የምታሳዪውን ክብር ማስቀረትሽ ምን ያኽል ከባድና መራራ በደል እንደ ሆነ ትረጂአለሽ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ጌታ የሠራዊት አምላክ ነኝ።”
እናንተ በዚህ ዘመን ያላችሁ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እኔ እግዚአብሔር የምላችሁን አድምጡ፤ እኔ ለእናንተ እንደ በረሓ፥ ወይም በድቅድቅ ጨለማ እንደ ተሞላ ምድር ሆንኩባችሁን? ታዲያ ‘እኛ የፈለግነውን እናደርጋለን እንጂ ከቶ ወደ አንተ አንመለስም’ የምትሉን ለምንድን ነው?
እነሆ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የቀድሞ አባቶቻችሁ ከኔ ርቀው የሄዱት በኔ ላይ ምን ጥፋት አግኝተው ነው? እነርሱም ከንቱ የሆኑትን ጣዖቶች በማምለካቸው ራሳቸውን ከንቱዎች አደረጉ።
የእስራኤልና የይሁዳ ሕዝብ፥ የእነርሱ ነገሥታት፥ ባለሥልጣኖቻቸው፥ የእነርሱ ካህናትና ነቢያት በሚያደርጉአቸው ክፉ ነገሮች ሁሉ ቊጣዬን አነሣሥተዋል።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ቀስት መደገን የሚችሉትን ቀስተኞች በባቢሎን ላይ ይዘምቱ ዘንድ ጥሩአቸው፤ ከተማይቱን ይክበቡ፤ ማንም እንዳያመልጥ ተጠባበቁ፤ የክፉ ሥራዋንም ዋጋ ክፈሉአት፤ በሌሎች ላይ የፈጸመችውንም ግፍ በእርስዋም ላይ ፈጽሙባት፤ እርስዋ በእስራኤል ቅዱስ በእኔ ላይ ተዳፍራለች፤
ምድራቸው በእኔ በእስራኤል ቅዱስ ዘንድ በበደል የተሞላች ብትሆንም እንኳ እኔ የሠራዊት ጌታ አምላካቸው እስራኤልንና ይሁዳን አልረሳኋቸውም።
አመንዝራ ሴት ገንዘብ ይከፈላት ነበር፤ አንቺ ግን ገንዘብ በመቀበል ፈንታ ለወዳጆችሽ ስጦታ ታበረክቺአለሽ፤ ከየአቅጣጫው መጥተው ከአንቺ ጋር ያመነዝሩ ዘንድ መደለያ ገንዘብ ሰጠሽ።
በእርግጥም አንቺ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ እናትሽ ባልዋንና ልጆችዋን ጠልታ ነበር፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንደ ጠሉ እንደ እኅቶችሽ ነሽ፤ አንቺና እኅቶችሽ ሒታዊ እናትና አሞራዊ አባት ነበራችሁ።
እስራኤላውያን ሁሉ ሕግህን ተላለፉ፤ የተናገርከውን ሁሉ ማዳመጥ እምቢ አሉ፤ አንተን ስለ በደልን በአገልጋይህ በሙሴ በኩል የተሰጠውን ሕግ በመሐላ የተገለጠውን ርግማን ሁሉ በእኛ ላይ አመጣህብን።
አሁን ደግሞ እናንተ በአባቶቻችሁ ስፍራ ተተክታችኋል፤ የእግዚአብሔርንም ቊጣ በእስራኤል ላይ ለማምጣት የተዘጋጀ አዲስ ኃጢአተኛ ትውልድ ሆናችኋል።
ነገር ግን፥ ዮሐንስ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ለመጠመቅ ወደ እርሱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእባብ ልጆች! ከሚመጣው ቊጣ እንድታመልጡ ማን አስጠነቀቃችሁ?
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አንተ በቅርብ ጊዜ እንደ ቀድሞ አባቶችህ ትሞታለህ፤ ከዚያ በኋላ ይህ ሕዝብ ከእርሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳል። እኔንም በመተው በሚወርሰው ምድር የሚገኙትን ጣዖቶች ያመልካል።
አሁን ስለ እናንተ በምቀበለው መከራ ደስ ይለኛል፤ አካሉ ስለ ሆነችው ስለ ቤተ ክርስቲያንም ከክርስቶስ መከራ ከመካፈል የጐደለብኝን በሥጋዬ አሟላለሁ።
ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን “አንተን አምላካችንን ትተን በዓል ተብለው የሚጠሩትን ባዕዳን አማልክት በመከተላችን በአንተ ላይ በደል ሠርተናል” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።