Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዳንኤል 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ዳንኤል ስለ ሕዝቡ መጸለዩ

1 ትውልዱ ሜዶናዊ የሆነው የአርጤክስስ ልጅ ዳርዮስ በባቢሎን ነገሠ።

2 በነገሠም በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል ቅዱሳት መጻሕፍትን እየተመለከትኩ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ በነገረው መሠረት ኢየሩሳሌም ፍርስራሽ ሆና የምትቈይባት ዘመን ሰባ ዓመት መሆኑን ዐወቅሁ።

3 ማቅ ለብሼና ዐመድ ላይ ተቀምጬ በመጾም ጸሎቴንና ልመናዬን ለማቅረብ ፊቴን ወደ ጌታ እግዚአብሔር መለስኩ።

4 ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር በመናዘዝ እንዲህ ስል ጸለይኩ፦ “ለሚወዱህና ትእዛዞችህን ለሚጠብቁ ቃል ኪዳንህንና ዘለዓለማዊ ፍቅርህን የምትጠብቅ ታላቅና መፈራት የሚገባህ አንተ ጌታ እግዚአብሔር ነህ።

5 “እኛ ግን ክፉዎችና ዐመፀኞች ሆነን ኃጢአት በመሥራት በድለናል፤ ሕግህንና ትእዛዞችህን ከመፈጸም ቸል ብለናል።

6 ለንጉሦቻችን፥ ለገዢዎቻችን፥ ለቀደሙት አባቶቻችንና በምድሪቱ ለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ በስምህ የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አላዳመጥንም።

7 ጌታ ሆይ! አንተ እውነተኛ ነህ፤ ነገር ግን ለአንተ ታማኞች ባለመሆናችን፥ እኛ በምድር ሁሉ ላይ የበተንከን በቅርብና በሩቅ ያለን የይሁዳ ሕዝብ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና መላዋ የእስራኤል ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ኀፍረት ደርሶብናል።

8 ጌታ ሆይ! እኛ ሁላችን አንተን ስለ በደልን እኛ፥ ንጉሦቻችን፥ ገዢዎቻችንና የቀድሞ አባቶቻችን ኀፍረት ደርሶብናል።

9 ጌታ አምላካችን ሆይ፥ ምንም እኛ በአንተ ላይ ብናምፅ አንተ መሐሪና ይቅር ባይ ነህ።

10 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! ሕጎችህን በመጠበቅ ታዛዦች ሆነን አልተገኘንም፤ በአገልጋዮችህ በነቢያት አማካይነት የሰጠኸንን ትእዛዞች አልጠበቅንም።

11 እስራኤላውያን ሁሉ ሕግህን ተላለፉ፤ የተናገርከውን ሁሉ ማዳመጥ እምቢ አሉ፤ አንተን ስለ በደልን በአገልጋይህ በሙሴ በኩል የተሰጠውን ሕግ በመሐላ የተገለጠውን ርግማን ሁሉ በእኛ ላይ አመጣህብን።

12 በእኛና በመሪዎቻችን ላይ ታላቅ መከራ እንደምታመጣብን የተናገርከው ሁሉ እንዲፈጸምብን አደረግህ፤ ስለዚህም በምድር ላይ ካሉ አገሮች ሁሉ የኢየሩሳሌምን ያኽል ቅጣት የደረሰበት ከቶ የለም።

13 በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት ይህን ሁሉ መከራ በእኛ ላይ አመጣህ፤ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፥ ይህም ሁሉ ሆኖ ከኃጢአታችን በመመለስና እውነትን በመከተል የአንተን ምሕረት ለማግኘት ወደ አንተ አልጸለይንም።

14 አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ! አንተ በሥራህ ሁሉ እውነተኛ ነህ፤ እኛ ግን ስለ አልታዘዝንህ ይህን ሁሉ መከራ አመጣህብን።

15 “እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! ከዚህ በፊት በብርቱ ኀይልህ ሕዝብህን ከግብጽ በማውጣት ስምህ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲታወቅ አድርገሃል፥ እኛ ግን ኃጢአተኞችና በደለኞች ሆንን።

16 ጌታ ሆይ! ስለ ፈጸምካቸው የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ ብለህ ከተቀደሰችው ተራራህ ከኢየሩሳሌም ቊጣህንና መዓትህን እንድታነሣ እንለምንሃለን፤ በኃጢአታችንና በአባቶቻችንም በደል ምክንያት ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በጐረቤቶቻችን ሁሉ መካከል ተዋርደዋል።

17 አምላክ ሆይ! ጸሎቴንና ልመናዬን ስማ፤ ስለ ስምህ ስትል ለፈረሰው ቤተ መቅደስህ ራራ።

18 አምላክ ሆይ! እባክህ አድምጠኝ፤ የእኛን ችግርና በስምህ የምትጠራውን ከተማ ጥፋት ተመልከት፤ ወደ አንተ የምንጸልየው የአንተን ምሕረት በመተማመን እንጂ በእኛ መልካም ሥራ በመመካት አይደለም።

19 እግዚአብሔር ሆይ! ስማን! እግዚአብሔር ሆይ! ይቅር በለን! እባክህ አድምጠን! ሥራህንም ግለጥ! አምላክ ሆይ! አትዘግይ፤ ይህች ከተማና ይህ ሕዝብ በስምህ የተጠሩ ናቸው።”


ገብርኤል የትንቢቱን ትርጒም መግለጡ

20 የራሴንና የወገኖቼን የእስራኤላውያንን ኃጢአት እየተናዘዝኩ፥ ስለ ቅዱስ ተራራው በአምላኬ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎቴን ቀጠልኩ።

21 በዚህም ጸሎት ላይ ሳለሁ በመጀመሪያው ራእይ ያየሁት ገብርኤል እኔ ወዳለሁበት ስፍራ በፍጥነት እየበረረ መጣ፤ ጊዜውም የሠርክ መሥዋዕት የሚቀርብበት ወቅት ነበር።

22 እርሱም እንዲህ ሲል አስረዳኝ፦ “ዳንኤል ሆይ! እኔ ወደዚህ የመጣሁት የትንቢቱን ምሥጢር እንድታውቅ ጥበብንና ማስተዋልን ልሰጥህ ነው፤

23 ገና መጸለይ ስትጀምር እግዚአብሔር ልመናህን ሰምቶአል፤ አንተ በእርሱ ዘንድ የተወደድክ ስለ ሆነ የጸሎትህን መልስ ልነግርህ መጥቼአለሁ፤ እንግዲህ የምነግርህን አዳምጠህ የራእዩን ትርጒም ተረዳ።

24 “ሰባት ጊዜ ሰባ ሳምንት የተባለው እግዚአብሔር ሕዝብህንና የተቀደሰ ከተማህን ከኃጢአትና ከክፋት ነጻ ለማውጣት ውሳኔ ያደረገበት ጊዜ ነው፤ በዚያን ጊዜ በደል ይሰረያል፤ ዘለዓለማዊ ፍትሕ ይሰፍናል፤ ራእይና ትንቢት ይፈጸማል፤ ቤተ መቅደሱም ይታደሳል።

25 ይህን ልብ ብለህ አስተውል፤ ኢየሩሳሌም እንድትታደስ ትእዛዝ ከወጣበት ጊዜ አንሥቶ መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ሰባት ሳምንቶች ያልፋሉ፤ እንዲሁም ለሥልሳ ሁለት ሳምንት በችግር ጊዜ ኢየሩሳሌም፥ መንገዶችዋና የመከላከያ ጒድጓድዋ ይገነባሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የመከራ ዘመን ይሆናል።

26 ከስድሳ ሁለት ሳምንት በኋላ መሲሑ ያለ ፍትሕ ይገደላል፤ የሚገደለውም ለራሱ አይደለም፤ የሚመጣው መሪ ወታደሮች ቤተ መቅደሱንና ከተማይቱን ይደመስሳሉ፤ መጨረሻውም እንደ ጐርፍ ይመጣል፤ ውድመት ስለ ታወጀ ጦርነት እስከ መጨረሻ ይቀጥላል።

27 ያም መሪ ለአንድ ሳምንት ከብዙ ሕዝቦች ጋር የጠበቀ ቃል ኪዳን ያደርጋል፤ በሳምንቱም እኩሌታ መሥዋዕቱንና ቊርባኑን ያስቀራል፤ በእነርሱም ፈንታ ጥፋት የሚያስከትለው ርኲሰት እንዲተካ ያደርጋል። ይህም የሚሆነው በዚያ አጥፊ መሪ ላይ የታወጀው ቅጣት እስኪፈጸም ድረስ ነው።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos