መዝሙር 58 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ክፉ ሰዎችን እንዲቀጣ የቀረበ ጸሎት 1 እናንተ ገዢዎች! በትክክል ትናገራላችሁን? በሰዎችስ መካከል ያለ አድልዎ ትፈርዳላችሁን? 2 አይደለም! በልባችሁ ክፉ ነገርን ታቅዳላችሁ፤ በምድር ላይ የምትፈጽሙትም ሁሉ የዐመፅ ሥራ ነው። 3 ክፉዎች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ በድለዋል፥ ሐሰትንም ተናግረዋል። 4 እነርሱ እንደ እባብ መርዘኞች ናቸው፤ እንደ ደንቆሮ እፉኝትም ጆሮአቸውን ይደፍናሉ። 5 እፉኝት ጆሮውን የሚደፍነው የእባብ አፍዛዦችን ድምፅ፥ ወይም የአስማተኞችን ድግምት ላለመስማት ነው። 6 አምላክ ሆይ! የእነዚህን እንደ አንበሳ አስፈሪ የሆኑ ሰዎች ጥርስ ስበር፤ መንጋጋቸውንም አውልቅ። 7 ፈስሶ እንደሚያልቅ ውሃ ይጥፉ፤ በመንገድ ላይ እንደ በቀለ ሣር ተረጋግጠው ይርገፉ፤ 8 እየሄደ ሟምቶ እንደሚያልቅ ቀንድ አውጣና ሞቶ እንደ ተወለደና ብርሃንን ከቶ እንዳላየ ጭንጋፍ ይሁኑ። 9 እሾኽ በእሳት ላይ ተደርጎ ከመሞቁ በፊት ፈጥነህ ጠራርገህ አጥፋቸው። 10 ኃጢአተኞችን ሲበቀልላቸው በማየታቸው ጻድቃን ደስ ይላቸዋል፤ በክፉዎችም ደም እግሮቻቸውን ይታጠባሉ። 11 በዚያን ጊዜ ሰዎች “ጻድቃን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ አገኙ፤ በዓለም ላይ የሚፈርድ አምላክ በእርግጥ አለ” ይላሉ። |