ኢሳይያስ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምወደፊት የሚነሣው የሰላም ንጉሥ 1 እነዚያ የተሠቃዩት ግን ዳግመኛ ችግር አይደርስባቸውም። በቀድሞ ዘመን የዛብሎንና የንፍታሌም ምድር ተዋርዳ ትኖር ነበር፤ በኋለኛው ዘመን ግን ከሜዲቴራኒያን ባሕር ምሥራቅ ጀምሮ እስከ ዮርዳኖስ ማዶ ያለው በተለይም አሕዛብ ሰፍረውበት የነበረው የገሊላ ምድር ክብርን ይጐናጸፋል። 2 በጨለማ ይኖር የነበረ ሕዝብ እነሆ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገር ውስጥ ለሚኖሩትም ሁሉ ብርሃን ወጣላቸው። 3 አምላክ ሆይ! ሕዝብህን አበዛህ፤ በደስታም እንዲሞሉ አደረግሃቸው፤ ሰዎች መከር በሚሰበስቡበት፥ ወይም ምርኮ በሚካፈሉበት ጊዜ ደስ እንደሚላቸው ሕዝብህም አንተ ባደረግኸው ነገር ደስ ይላቸዋል። 4 በቀድሞ ዘመን ምድያማውያንን ድል እንዳደረግህ ሁሉ፥ አሁንም በሕዝብህ ላይ የተጫነውን የአገዛዝ ቀንበርና በትከሻቸው ላይ የተቃጣውን በትር ሰባበርክ፤ ሕዝብህን በማስጨነቅ ይገዛ የነበረውን ድል አደረግህ። 5 የወራሪ ጦረኞች ጫማና በደም የተለወሰ ልብሳቸው ሁሉ በእሳት ይጋያል። እንደ ማገዶ ሆኖ ይቃጠላል። 6 እነሆ ሕፃን ተወልዶልናል! ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል! እርሱም መሪ ይሆናል፤ ስሙም “ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘለዓለም አባት፥ የሰላም አለቃ” ይባላል። 7 ለንጉሣዊ ሥልጣኑ ወሰን የለውም፤ መንግሥቱም ዘለዓለማዊ ሰላም የሰፈነበት ይሆናል፤ ከአሁን ጀምሮ እስከ ዘለዓለም፥ እውነትና ፍትሕ የሰፈነበት መንግሥት በዳዊት ዙፋን ላይ ተመሥርቶ እንዲጸና ያደርገዋል፤ የሠራዊት አምላክ ቅናት ይህን ለማድረግ ወስኖአል። እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ የሚቀጣ መሆኑ 8 ጌታ የያዕቆብ ዘሮች በሆኑ በእስራኤል ሕዝብ ላይ የፍርድ ቃሉን ላከ፤ ፍርዱም ተግባራዊ ይሆናል። 9 የእስራኤል ሕዝብና በሰማርያ ከተማም የሚኖሩ ሁሉ ይህን ያደረገ እግዚአብሔር መሆኑን ያውቃሉ፤ ሆኖም፥ ትዕቢተኞችና እልኸኞች ሆነው እንዲህ ይላሉ፦ 10 “ከጡብ የተሠሩ ግንቦች ፈርሰዋል፤ እኛ ግን እንደገና በጥርብ ድንጋይ እንገነባቸዋለን፤ ከሾላ ግንድ የተሠሩ ምሰሶዎች ተሰብረዋል፤ እኛ ግን በምርጥ የሊባኖስ ዛፍ እንተካቸዋለን።” 11 ስለዚህ እግዚአብሔር ተቀናቃኞችን በእነርሱ ላይ ያስነሣባቸዋል፤ ጠላቶቻቸውንም በእነርሱ ላይ ያነሣሣባቸዋል። 12 እርሱ ከምሥራቅ ሶርያውያንን፥ ከምዕራብ ፍልስጥኤማውያንን ልኮ እስራኤልን እንዲወሩ አደረገ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ቊጣው አልበረደም፤ ስለዚህ እጁ እነርሱን ለመቅጣት እንደ ተቃጣ ነው። 13 ሕዝቡ ግን ወደ ቀጣቸው አምላክ አልተመለሱም፤ ወይም የሠራዊት አምላክን የሚሹ ሆነው አልተገኙም። 14 ስለዚህ እግዚአብሔር በአንድ ቀን እንደ ራስና እንደ ጅራት እንደ ዘንባባውና እንደ ቅርንጫፉ የሚቈጠሩትን ከእስራኤል ይቈርጣል። 15 ራስ የተባሉት ሽማግሌዎችና የተከበሩ አለቆች ናቸው፤ ጅራት የተባሉትም ሐሰትን የሚያስተምሩ ነቢያት ናቸው። 16 ይህን ሕዝብ የሚመሩት ሁሉ አሳስተውታል፤ ሕዝቡም ከመንገድ ወጥቶ ባዝኖአል። 17 ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ወጣቶቻቸውን ይቀጣል፤ ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶችና አሳዳጊ ለሌላቸው ለሙት ልጆቻቸው አይራራም፤ ሁሉም እያንዳንዱ ከሐዲና ክፉ አድራጊ ሆኖአል፤ ከእያንዳንዱም ሰው አንደበት የሚነገረው ቃል ተንኰል የሞላበት ነው፤ ይህም ሁሉ ሆኖ የእግዚአብሔር ቊጣ ገና አልበረደም፤ ስለዚህ እነርሱን ለመቅጣት እጁ እንደ ተቃጣ ነው። 18 የሕዝቡ ክፋት ኲርንችቱንና እሾኹን እንደሚያቃጥል እሳት ነው፤ እንደ በረሓ እሳት ደኑን በሚያቃጥልበት ጊዜ ጢሱ ተትጐልጒሎ ሲወጣ ቀጥ ብሎ የቆመ ዐምድ ይመስላል። 19 የሠራዊት አምላክ ተቈጥቶአል፤ የቅጣቱም ፍርድ በአገሪቱ በሞላ እንደ እሳት ይነዳል፤ ሕዝቡም እንደ ማገዶ ይሆናል፤ ወንድም ለወንድሙ አይራራም። 20 በአንድ በኩል ሆዳቸው እስኪሞላ ይበላሉ፤ ነገር ግን እንደ ተራቡ ናቸው፤ እንዲሁም በሌላ በኩል አግበስብሰው ይውጣሉ፤ ነገር ግን አይጠግቡም፤ የልጆቻቸውን ሥጋ እንኳ እስከ መብላት ይደርሳሉ። 21 ይኸውም ምናሴ ኤፍሬምን፥ ኤፍሬምም ምናሴን ይወረዋል፤ ሁለቱም ነገዶች ተባብረው በይሁዳ ላይ ይዘምታሉ፤ ይህም ሁሉ ሆኖ የእግዚአብሔር ቊጣ ገና አልበረደም፤ ስለዚህ እነርሱን ለመቅጣት እጁ እንደ ተሰነዘረ ነው። |