Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 32 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያሉት ነገዶች
( ዘዳ. 3፥12-22 )

1 የሮቤልና የጋድ ነገዶች እጅግ ብዙ የከብት መንጋ ነበራቸው፤ የያዕዜርና የገለዓድ ምድር ለከብት ተስማሚ መሆኑን ባዩ ጊዜ፥

2 ወደ ሙሴና አልዓዛር እንዲሁም ወደ ሌሎቹ የማኅበሩ መሪዎች ሄደው እንዲህ አሉ፤

3-4 “ይህ እስራኤላውያን እንዲወርሱት እግዚአብሔር የረዳቸው የዐጣሮት፥ የዲቦን፥ የያዕዜር፥ የኒምራ፥ የሐሴቦን፥ የኤልዓሌ፥ የሲብማ፥ የነቦና የበዖን ከተሞች የሚገኙበት ምድር ለከብት ተስማሚ ነው፥ እኛ ደግሞ ብዙ ከብት አለን፤”

5 ንግግራቸውንም በመቀጠል፦ “በፊታችሁ ሞገስን አግኝተን ከሆነ ይህን ምድር ለእኛ ለአገልጋዮቻችሁ በርስትነት እንዲሰጠን አድርጉ እንጂ ዮርዳኖስን እንድንሻገር አታድርጉ።”

6 ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወገኖቻችሁ እስራኤላውያን ወደ ጦርነት ሲሄዱ እናንተ እዚህ መቅረት ትፈልጋላችሁን?

7 የእስራኤል ሕዝብ ዮርዳኖስን ተሻግረው እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ የምታስቈርጡት ለምንድን ነው?

8 ምድሪቱን ያጠኑ ዘንድ ወደ ቃዴስ በርኔ በላክኋቸው ጊዜ አባቶቻችሁ ያደረጉት ይህንኑ ነበር፤

9 እስከ ኤሽኮል ሸለቆ ሄደው ምድሪቱን ተመለከቱ፤ ነገር ግን ከዚያ በተመለሱ ጊዜ ሕዝቡ እግዚአብሔር ወደ ሰጣቸው ምድር እንዳይገቡ ተስፋ አስቈረጡ፤

10-11 በዚያን ቀን እግዚአብሔር እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለ፤ ‘በእኔ በመተማመን ስላልጸኑ፥ ከግብጽ ምድር ከወጡት ዕድሜአቸው ኻያ ዓመት የሞላቸውና ከዚያም በላይ የሆኑ ሁሉ ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ልሰጣቸው ቃል ወደገባሁላቸው ምድር ከቶ እንደማይገቡ ምዬአለሁ።’

12 ይህም የእግዚአብሔር ውሳኔ እግዚአብሔርን በሙሉ ልባቸው ከታዘዙት ከቀኒዛዊው ከየፉኔ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር ማንኛውንም ሰው የሚያጠቃልል ነው። ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው የተገኙት እነርሱ ብቻ ናቸው።

13 እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ተቈጥቶ ስለ ነበር፥ እነዚያ ያሳዘኑት ትውልዶች በሙሉ እስከሚያልቁ ድረስ ለአርባ ዓመት በምድረ በዳ እንዲንከራተቱ አደረጋቸው፤

14 አሁን ደግሞ እናንተ በአባቶቻችሁ ስፍራ ተተክታችኋል፤ የእግዚአብሔርንም ቊጣ በእስራኤል ላይ ለማምጣት የተዘጋጀ አዲስ ኃጢአተኛ ትውልድ ሆናችኋል።

15 እናንተ የሮቤልና የጋድ ሰዎች አሁን እግዚአብሔርን ለመከተል እምቢ ብትሉ፥ እርሱም ይህን ሕዝብ እንደገና በምድረ በዳ ይተወዋል፤ በእነርሱም ላይ በሚደርሰው ጥፋት እናንተ ኀላፊዎች ትሆናላችሁ።”

16 እነርሱም ወደ ሙሴ ቀርበው እንዲህ አሉ፦ “በመጀመሪያ በዚህ ለእንስሶቻችን በረቶች፥ ለልጆቻችንም ከተሞችን እንድንሠራ ፍቀድልን፤

17 ከዚያም በኋላ ከወገኖቻችን ከእስራኤላውያን ጋር ወደ ጦርነት ለመሄድና የራሳቸው ወደሆነችው ምድር ገብተው እስኪሰፍሩ ድረስ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈን ለመዋጋት ዝግጁዎች እንሆናለን፤ እኛም ይህን ግዳጅ ፈጽመን እስከምንመለስ ልጆቻችን በእነዚህ በተመሸጉ ከተሞች ይኖራሉ፤ በዚህች ምድር ከሚኖሩትም ሰዎች ወገን ጒዳት አይደርስባቸውም።

18 ሌሎቹ እስራኤላውያን ሁሉ ለእነርሱ የተመደበላቸውን ርስት እስኪያገኙ ድረስ ወደ ቤታችን አንመለስም፤

19 እኛ የራሳችንን ድርሻ እዚህ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ስለ ወሰድን ከዮርዳኖስ ማዶ ለእነርሱ ከተመደበው ርስት ምንም አንወስድም።”

20 ሙሴም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ይህ የተናገራችሁት ሁሉ እውነት ከሆነ እዚህ በእግዚአብሔር ፊት ወደ ጦርነት ለመሄድ ተዘጋጁ።

21-22 የጦር ሰዎቻችሁ ሁሉ ዮርዳኖስን መሻገር፥ በእግዚአብሔር አዛዥነት በጠላቶቻችን ላይ መዝመት፥ እግዚአብሔር ድል አድርጎ፥ ምድራቸውን እስኪወስድ ድረስ መዋጋት አለባቸው፤ ይህን ካደረጋችሁ በኋላ መመለስ ትችላላችሁ፤ በዚያን ጊዜ ለእግዚአብሔርም ሆነ ለወገኖቻችሁ ለእስራኤላውያን ያለባችሁን ግዴታ ትወጣላችሁ፤ ከዚያ በኋላ ይህ ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያለው ምድር የእናንተ ርስት መሆኑን እግዚአብሔር ያረጋግጥላችኋል።

23 ቃላችሁን ባትጠብቁ ግን እግዚአብሔርን የምታሳዝኑ ሆናችሁ እንዳትገኙ አስጠነቅቃችኋለሁ፤ ሰለ ኃጢአታችሁም ቅጣት የሚደርስባችሁ መሆኑንም አትዘንጉ።

24 ስለዚህ ከተሞቻችሁንና ለእንስሶቻችሁ የሚሆኑትን በረቶች ሥሩ፤ ነገር ግን የገባችሁትንም የተስፋ ቃል ፈጽሙ።”

25 የጋድና የሮቤል ወገኖች እንዲህ አሉ፤ “እኛ አገልጋዮችህ፥ አንተ ጌታችን እንዳዘዝከው እናደርጋለን።

26 ሚስቶቻችንና ልጆቻችን፥ ከብቶቻችንና በጎቻችን፥ በዚህ በገለዓድ ከተሞች ይቈያሉ፤

27 ነገር ግን እኛ አገልጋዮችህ ለጦርነት የታጠቅን ሁሉ በእግዚአብሔር መሪነት ለመዋጋት ልክ አንተ ጌታችን እንደምታዘን ወደ ማዶ እንሻገራለን።”

28 ስለዚህም ሙሴ ስለ እነርሱ ለካህኑ ለአልዓዛር፥ ለነዌ ልጅ ለኢያሱና ለእስራኤል ሕዝብ የነገድ አለቆች ሁሉ ይህን ትእዛዝ አስተላለፈ።

29 “የጋድና የሮቤል ሰዎች ዮርዳኖስን ተሻግረው በእግዚአብሔር መሪነት ለጦርነት የሚዘጋጁ ከሆነና በእነርሱም ርዳታ ምድሪቱን የምትወርሱ ከሆነ የገለዓድን ምድር ለእነርሱ ርስት አድርጋችሁ ስጡአቸው።

30 ዮርዳኖስን ተሻግረው ከእናንተ ጋር ወደ ጦርነት የማይሄዱ ከሆነ ግን ልክ እንደ እናንተው በከነዓን ምድር የራሳቸው ድርሻ የሆነ ርስት ይሰጣቸው።”

31 የጋድና የሮቤል ሰዎችም እንዲህ ሲሉ መልስ ሰጡ፤ “እግዚአብሔር ያዘዘንን ሁሉ እናደርጋለን፤

32 በእርሱም መሪነት ወደ ከነዓን ምድር እንሻገራለን፤ በዚህ በዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን የርስት ድርሻችንን ለራሳችን ለማስቀረት ወደ ጦርነት እንሄዳለን።”

33 ስለዚህ ሙሴ የአሞራውያንን ንጉሥ የሲሖንንና የባሳንን ንጉሥ የዖግን ግዛት በዙሪያቸው ያሉትን ከተሞችና አገሮች ጭምር ለጋድና ለሮቤል ነገዶች እንዲሁም ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠ፤

34 የጋድ ነገድ የተመሸጉትን የዲቦንን፥ የዐጣሮትን፥ የዓሮዔርን፥

35 የዓጥሮት ሶፋንን፥ የያዕዜርን፥ የዮግበሃን፥

36 የቤትኒምራንና የቤትሃራንን ከተሞች በማደስ ለከብቶቹም በረቶችን ሠራ።

37 የሮቤል ነገድ የሐሴቦንን፥ የኤልዓሌን፥ የቂርያታይምን፥

38 የነቦን፥ በኋላ ስሙ የተለወጠው የባዓልመዖንንና የሲብማን ከተሞች አደሰ፤ እነርሱም ላደሱአቸው ከተሞች ሁሉ አዲስ ስም አወጡላቸው።

39 የምናሴ ልጅ የማኪር ቤተሰብ የገለዓድን ምድር በመውረር ወረሰ፤ በዚያም ይኖሩ የነበሩትን አሞራውያንን አባረረ።

40 ስለዚህም ሙሴ የገለዓድን ምድር ለማኪር ቤተሰብ ሰጣቸው፤ እነርሱም በዚያ ኖሩ።

41 ከምናሴ ነገድ የሆነው ያኢር በአንዳንድ መንደሮች ላይ አደጋ ጥሎ ወሰዳቸው፤ “የያኢር መንደሮች” ብሎም ሰየማቸው።

42 ኖባሕ ደግሞ በቄናትና በመንደሮችዋ ላይ አደጋ በመጣል ወሰዳቸው፤ በራሱም ስም “ኖባሕ” ብሎ ሰየማቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos