ዘፍጥረት 22:17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም እኔም ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብትና እንደ ባሕር ዳር አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘሮችህም ጠላቶቻቸውን ድል ነሥተው ከተሞቻቸውን ይይዛሉ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) በእውነት መባረክን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት እና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘሮችህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳሉ፥ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ፈጽሞ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላት ሀገሮችን ይወርሳሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፦ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር እንዳል አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤ |
ቀጥሎም እግዚአብሔር አብራምን ወደ ውጪ አወጣውና “ወደ ሰማይ ተመልከት፤ ከዋክብትን መቊጠር ትችል እንደሆን ሞክር፤ እንግዲህ የአንተም ዘሮች እንደዚህ ይበዛሉ” አለው።
አብርሃም ከሞተ በኋላ ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር ባረከው፤ ይስሐቅም “ብኤርላሐይ ሮኢ ወይም የሚያየኝ ሕያው አምላክ” ተብሎ በሚጠራው ኲሬ አጠገብ ይኖር ነበር።
በዚያን ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ እኔ ከአንተ ጋር ስለ ሆንኩ አትፍራ፤ ለአገልጋዬ ለአብርሃም በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ” አለው።
አብርሃምን እንደ ባረከ አንተንና ዘርህን ይባርክ! ይህንንም ለአብርሃም ሰጥቶት የነበረውንና አንተም ስደተኛ ሆነህ የኖርክበትን ምድር ርስት አድርጎ ይስጥህ!”
ስለዚህ እኔ የምመክርህ፥ ከአገሪቱ አራት ማእዘኖች ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉትንና ብዛታቸው እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የሆነው እስራኤላውያን ሁሉ በአንድነት ሰብስበህ አንተው ራስህ አዛዥ በመሆን ወደ ጦርነቱ እንድትመራቸው ነው።
እግዚአብሔር “የእስራኤልን ሕዝብ እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ” ሲል በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ንጉሥ ዳዊት ዕድሜአቸው ከኻያ ዓመት በታች የሆኑትን በሕዝብ ቈጠራ ውስጥ አላስገባቸውም ነበር፤
እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! ለአባቴ የሰጠኸው የተስፋ ቃል እንዲፈጸም አድርግ፤ እነሆ ከብዛቱ የተነሣ ሊቈጠር በማይችል ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛል፤
ብዛታቸው እንደ ሰማይ ከዋክብት የሆኑ ልጆችን ሰጠሃቸው፥ ለቀድሞ አባቶቻቸው ትሰጣቸው ዘንድ ቃል የገባህላቸውን ምድር፥ በድል አድራጊነት እንዲይዙ ፈቀድክላቸው።
አገልጋዮችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ፤ ዘራቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት ልታበዛውና የተስፋይቱንም ምድር ርስት ለዘለዓለም አድርገህ ልትሰጣቸው በመሐላ የገባህላቸውንም ቃል ኪዳን አስብ።”
ስለዚህ የአገልጋዬን የዳዊትን ዘርና ከሌዊ ወገን የሆኑትን ካህናት ቊጥር አበዛለሁ፤ ብዛታቸውም ሊቈጠር እንደማይችል እንደ ባሕር አሸዋና እንደ ሰማይ ከዋክብት ይሆናል።”
የእስራኤል ሕዝብ ብዛት ሊቈጠር ወይም ሊለካ እንደማይቻል የባሕር አሸዋ ይሆናል፤ አሁን እግዚአብሔር “ሕዝቤ አይደላችሁም” ቢላቸው በዚሁ ስፍራ “የሕያው እግዚአብሔር ልጆች!” ተብለው የሚጠሩበት ጊዜ ይመጣል፤
የሰማርያ ቊስል ሊፈወስ የሚችል አይደለም፤ ይህም ሥቃይ ወደ ይሁዳ ደርሶአል፤ ሕዝቤ ወደሚሰበሰቡበት ወደ ኢየሩሳሌም አደባባይም ተዛምቶአል።”
ኢሳይያስም ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፤ “የእስራኤል ልጆች ቊጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢበዛ እንኳ ከእነርሱ የሚድኑት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።
የቀድሞ አባቶችህ ወደ ግብጽ በወረዱ ጊዜ ብዛታቸው ሰባ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር አምላክህ የአንተን ቊጥር ብዛት እንደ ሰማይ ከዋክብት አድርጎታል።
እግዚአብሔር ከአስፈሪ ቊጣው ተመልሶ ምሕረት ያደርግልህ ዘንድ እንዲወድም ከተወሰነው ሀብት አንዳችም ለራስህ አታስቀር፤ ይህን ብታደርግ ለአባቶችህ በመሐላ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ቊጥርህን ያበዛዋል።
ሰባተኛውም መልአክ እምቢልታውን ነፋ፤ በሰማይም “የዓለም መንግሥት የጌታ የአምላካችንና የመሲሑ ሆናለች፤ እርሱ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣል፤” የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ተሰሙ።