Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘዳግም 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ገዳዩ ያልታወቀ የግድያ ወንጀል

1 “እግዚአብሔር እንድትወርሳት በሚሰጥህ ምድር በሜዳ ላይ ማን እንደ ገደለው ሳይታወቅ አንድ ሰው ተገድሎ ቢገኝ፤

2 በዚያን ጊዜ መሪዎችህና ዳኞችህ ሄደው አስከሬኑ ወድቆ ከተገኘበት ስፍራ አንሥተው ባቅራቢያ እስከምትገኘው እስከያንዳንዱ ከተማ ድረስ ርቀቱን ይለኩት፤

3 ከዚያም በኋላ አስከሬኑ ወድቆ ለተገኘበት ስፍራ ቅርብ ሆና የምትገኘው ከተማ መሪዎች ለሥራ ያልደረሰች፥ በጫንቃዋም ላይ ቀንበር ያልተጫነባት አንዲት ጊደር ይምረጡ፤

4 እርስዋንም ጨርሶ ወዳልታረሰና ምንም ተክል ወዳልተተከለበት፥ ወንዙም ወደማይደርቅበት ሸለቆ ይዘዋት ወርደው በዚያ አንገትዋን በመቈልመም ይስበሩት፤

5 እርሱን እንዲያገለግሉት፥ በእርሱ ስም እንዲባርኩ፥ የክርክርና የወንጀል ጉዳይ በእነርሱ እንዲወሰን አምላክህ እግዚአብሔር ካህናቱን የሌዊን ልጆች ስለ መረጣቸው ወደ አስከሬኑ ይቅረቡ።

6 ከዚህም በኋላ የተገደለው ሰው አስከሬን ወድቆ ለተገኘበት ስፍራ አቅራቢያ የሆነችው የዚያች ከተማ መሪዎች በጊደርዋ ላይ እጃቸውን ይታጠቡ፤

7 እንዲህም ብለው መግለጫ ይስጡ፦ ‘እኛ ይህን ሰው አልገደልንም፤ ማን እንደ ገደለውም አላየንም፤

8 እግዚአብሔር ሆይ፥ ከግብጽ ምድር ዋጅተህ ያወጣሃቸውን ሕዝብህን እስራኤልን ይቅር በል፤ እኛንም ይቅር በለን፤ ስለዚህም ስለ ፈሰሰው የንጹሕ ሰው ደም በኀላፊነት ተጠያቂዎች አታድርገን።’

9 በእግዚአብሔር ፊት ትክክለኛውን ነገር ስለምታደርግ ስለ ንጹሑ ሰው ግድያ ወንጀል ተጠያቂ አትሆንም።


የጦር ምርኮኞች ስለ ሆኑ ሴቶች የተሰጠ መመሪያ

10 “ጠላቶችህን ለመዋጋት ወጥተህ፥ እግዚአብሔር አምላክህ እነርሱን አሳልፎ ሲሰጥህና ስትማርካቸው

11 በእነርሱ መካከል ለጋብቻ የምትፈልጋት ውበት ያላት ሴት ታይ ይሆናል፤

12 ይህም ከሆነ፥ እርስዋን ወደ ቤትህ ወስደህ፥ ራስዋን ተላጭታ፥ ጥፍርዋን ተቈርጣ፥

13 ልብስዋን ትለውጥ፤ እርስዋም ከአንተ ጋር በቤትህ ተቀምጣ እስከ አንድ ወር ድረስ በጦርነት ስለሞቱት ወላጆችዋ ታልቅስ፤ ከዚያም በኋላ ሚስት አድርገህ ታገባታለህ።

14 በኋላ ግን የማትፈልጋት ከሆንህ ነጻ ልትለቃት ትችላለህ፤ ከአንተ ጋር የጋብቻ ግንኙነት እንድትፈጽም ያስገደድሃት ስለ ሆንክ ባሪያ አድርገህ ልትሸጣት አይገባም።


የበኲር ልጅ ሕጋዊ የመውረስ መብት

15 “አንድ ሰው ሁለት ሚስቶችን አግብቶ አንደኛይቱን አፍቅሮ ሌላይቱን ባያፈቅርና ሁለቱም ወንዶች ልጆችን ቢወልዱለት፥ ምናልባት የመጀመሪያው ልጅ የተወለደው ከማይወዳት ሚስቱ ቢሆን፥

16 ታዲያ፥ ያ ሰው ሀብቱንና ንብረቱን ለልጆቹ በሚያካፍልበት ጊዜ ለበኲር ልጁ ሊሰጥ የሚገባውን ድርሻ በተለይ ከሚያፈቅራት ሚስቱ ለተወለደው ልጁ በመስጠት አድልዎ ማድረግ አይገባውም፤

17 ከማያፈቅራት ሚስቱ የተወለደ ቢሆንም እንኳ ለበኲር ልጁ የሚሰጠው ድርሻ ከሌሎቹ የነፍስ ወከፍ ድርሻ በእጥፍ ከፍ ያለ መሆን አለበት፤ ስለዚህም ያ ሰው ልጁ በመጀመሪያ በመወለዱ በኲር መሆኑን ተረድቶ የብኲርና ድርሻውን ሊሰጠው ይገባል።


ለወላጆቹ ስለማይታዘዝ ልጅ የተሰጠ መመሪያ

18 “አንድ ሰው ምንም ቢቀጡት የማይመለስ እልኸኛና ዐመፀኛ ሆኖ፥ ለወላጆቹ የማይታዘዝ ልጅ ይኖረው ይሆናል፤

19 ይህም ከሆነ ወላጆቹ በሚኖሩባት ከተማ አደባባይ ወዳሉት መሪዎች ዘንድ አምጥተው ለፍርድ ያቁሙት፤

20 በሚያስፈርዱበትም ጊዜ እንዲህ ይበሉ፥ ‘እነሆ፥ ይህ ልጃችን እልኸኛና ዐመፀኛ ነው፤ ለእኛ መታዘዝን እምቢ ብሎአል፤ ሰካራምና ገንዘብ አባካኝ ሆኖብናል፤’

21 የከተማይቱም ሰዎች ሁሉ በድንጋይ ወግረው ይግደሉት፤ በዚህም ዐይነት ይህን ክፉ ነገር ታስወግዳላችሁ፤ በእስራኤልም የሚኖር ሁሉ ይህን ሁኔታ ሰምቶ ይፈራል።


ልዩ ልዩ ሕጎች

22 “አንድ ሰው በሠራው ከባድ ወንጀል ምክንያት በእንጨት በስቅላት ቢቀጣ፥

23 በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር የተረገመ ስለ ሆነ አስከሬኑ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ አይደር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በርስትነት የሚሰጥህን ምድር እንዳታረክስ አስከሬኑን በዚያኑ ዕለት ቅበረው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos