Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 22 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)


የአብርሃም መሥዋዕት

1 ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ “አብርሃም!” ብሎ ጠራው፤ አብርሃምም፥ “እነሆ፥ አለሁኝ!” ብሎ መለሰ።

2 እግዚአብሔርም፥ “የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሕቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፥ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋልኝ” አለው።

3 በማግስቱም ጠዋት አብርሃም በማለዳ ተነሥቶ ለመሥዋዕት የሚሆን ዕንጨትን ቈረጠና በአህያው ላይ ጫነው፥ ከእርሱም ጋር ሁለቱን አገልጋዮቹን እና ልጁን ይስሕቅን ይዞ፥ እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ተነሥቶ ጉዞ ጀመረ።

4 በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት ቦታውን በሩቅ አየ።

5 ከዚህ በኋላ አብርሃምም አገልጋዮቹን፥ “አህያውን ይዛችሁ በዚህ ቈዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ተራራ ሄደን እንሰግዳለን፤ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን” አላቸው።

6 አብርሃምም የመሥዋዕቱን ማቃጠያ እንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፥ እርሱም እሳቱንና ቢላዋውን በእጁ ያዘ፥ ከዚያም ሁለቱ አብረው ሄዱ።

7 ይስሐቅ አብርሃምን “አባቴ ሆይ!” አለው፤ አብርሃምም “እነሆ፥ አለሁ ልጄ!” አለው። ይስሐቅም “እነሆ፥ እሳትና እንጨት ይዘናል፤ ነገር ግን ለመሥዋዕት የሚሆነው በግ የት አለ?” በማለት ጠየቀው።

8 አብርሃምም “ልጄ ሆይ፥ ለመሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ራሱ ያዘጋጃል” አለው፤ ከዚያም ሁለቱ አብረው ሄዱ።

9 እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ በደረሱ ጊዜ አብርሃም መሠዊያ ሠራና እንጨቱን በላዩ ላይ ረበረበው፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ላይ፥ ከእንጨቱ በላይ አጋደመው።

10 እጁንም ዘርግቶ፥ ልጁን ለማረድ አብርሃም ቢላዋ አነሣ።

11 ነገር ግን የጌታ መልአክ “አብርሃም! አብርሃም!” ሲል ከሰማይ ተጣራ። አብርሃምም “እነሆ፥ አለሁኝ!” አለ።

12 እርሱም “በልጁ ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ ምንም ዓይነት ጉዳት አታድርስበት፤ አንድ ልጅህን እንኳ ለእኔ ለመስጠት እንዳልሳሳህ እነሆ አየሁ፥ እኔን እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን አውቄአለሁ” አለ።

13 አብርሃምም ዓይኑን አንስቶ ሲመለከት፥ ከኋላው እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዛፍ ቊጥቋጦ ተይዞ አየ፥ አብርሃምም ሄዶ በጉን አመጣና፥ በልጁ ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው።

14 ስለዚህም አብርሃም ያንን ቦታ “ጌታ ያዘጋጃል (ያህዌ ይርኤ)” ብሎ ሰየመው፤ ዛሬም ቢሆን ሰዎች “ጌታ በተራራው ላይ ያዘጋጃል” ይላሉ።

15 የጌታ መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፥

16 እንዲህም አለው፦ “ጌታ፥ በራሴ እምላለሁ፥ ይላል፤ ምክንያቱም ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልከኝምና፤

17 በእውነት መባረክን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት እና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘሮችህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳሉ፥

18 ቃሌን ሰምተሃልና፥ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ።”

19 ከዚህ በኋላ አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፥ ተነሥተውም ወደ ቤርሳቤህ አብረው ሄዱ፥ አብርሃምም በቤርሳቤህ ተቀመጠ።


የናኮር ዘሮች

20 ይህም ከሆነ በኋላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረ፦ “እነሆ፥ ሚልካ ደግሞ ለወንድምህ ለናኮር ልጆችን ወለደች፤

21 እነርሱም የመጀመሪያው ዑፅ፥ ወንድሙም ቡዝ፥ የአራም አባት ቀሙኤል፤

22 ኬሠድ፥ ሐዞ፥ ፊልዳሽ፥ ይድላፍና በቱኤል ናቸው።”

23 በቱኤል ርብቃን ወለደ፤ ሚልካ እነዚህን ስምንት ልጆች ለአብርሃም ወንድም ለናኮር ወለደችለት።

24 እንዲሁም፥ ረኡማ የተባለችው የናኮር ቊባት ደግሞ ጤባሕን፥ ገሐምን፥ ተሐሽንና፥ ማዕካን ወለደችለት።

Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos