Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ሳሙኤል 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የሑሻይ አቤሴሎምን ማዘናጋት

1 ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቈይ አኪጦፌል አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “ዛሬ ማታ ዳዊትን አሳድጄ ለመያዝ እችል ዘንድ ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች እንድመርጥ ፍቀድልኝ፤

2 ደክሞት ተስፋ በመቊረጥ ላይ ሳለ ድንገተኛ አደጋ እጥልበታለሁ፤ በዚያን ጊዜ እርሱ ድንጋጤ ላይ ይወድቃል፤ ተከታዮቹም ጥለውት ይሸሻሉ ንጉሡንም ለብቻው አግኝቼ እገድለዋለሁ፤

3 ሙሽራ ወደ ባልዋ እንደምትመለስ ተከታዮቹ በሙሉ ወደ አንተ ተመልሰው እንዲመጡ አደርጋለሁ፤ እንግዲህ አንተ የምትፈልገው አንድ ሰው ብቻ መግደልን ነው፤ የቀረው ሌላው ሕዝብ ግን በሰላም ይኖራል።”

4 ይህም ለአቤሴሎምና ለእስራኤል መሪዎች ሁሉ ጥሩ ምክር መስሎ ታያቸው።

5 አቤሴሎምም “አሁን ደግሞ አርካዊውን ሑሻይን ጥሩትና እርሱ የሚለውን እንስማ” አለ።

6 ሑሻይም በደረሰ ጊዜ አቤሴሎም “አኪጦፌል የሰጠን ምክር ይህ ነው፤ ይህንኑ ምክር እንከተል ወይስ ምን ማድረግ እንደሚገባን አንተም የምትነግረን አለ ይሆን?” ሲል ጠየቀው።

7 ሑሻይም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በአሁኑ ሰዓት አኪጦፌል የሰጣችሁ ምክር ጥሩ አይደለም፤

8 አባትህ ዳዊትና ተከታዮቹ ብርቱ ጦረኞች እንደሆኑና ግልገሎችዋ እንደ ተነጠቁባትም ድብ አስፈሪዎች መሆናቸውን ታውቃለህ፤ አባትህ በጦር ልምድ የተፈተነ ወታደር በመሆኑ ሌሊቱን ከሠራዊቱ ጋር አያድርም፤

9 ምናልባት አሁን እንኳ በዋሻ ውስጥ ወይም በሌላ ስፍራ ተሸሽጎ ሊሆን ይችላል፤ ዳዊት በአንተ ሠራዊት ላይ አደጋ እንደ ጣለባቸው የሚሰማ ሰው ሁሉ ወዲያውኑ ወታደሮችህ እንደ ተሸነፉ አድርጎ ያወራል።

10 አባትህ ታላቅ ጦረኛ መሆኑንና የእርሱም ተከታዮች ብርቱ ተዋጊዎች መሆናቸውን በእስራኤል የሚኖር ሁሉ ስለሚያውቅ እንደ አንበሳ ደፋሮች የሆኑት ወታደሮችህ እንኳ ልባቸው በፍርሃት ሊቀልጥ ይችላል።

11 ስለዚህ እኔ የምመክርህ፥ ከአገሪቱ አራት ማእዘኖች ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያሉትንና ብዛታቸው እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የሆነው እስራኤላውያን ሁሉ በአንድነት ሰብስበህ አንተው ራስህ አዛዥ በመሆን ወደ ጦርነቱ እንድትመራቸው ነው።

12 የትም ስፍራ ቢደበቅ ዳዊትን ፈልገን እናገኘዋለን፤ በረዶ በምድር ላይ እንደሚወርድ እንወርድበታለን፤ እርሱም ሆነ ከተከታዮቹ አንድ ሰው እንኳ በሕይወት የሚተርፍ አይኖርም።

13 ሸሽቶ ወደ ከተማም ቢገባ ሕዝባችን በሙሉ ገመድ አምጥተው ከተማይቱን በመሳብ በእርስዋ ሥር ወደሚገኘው ሸለቆ አሽቀንጥረው ይጥሉአታል፤ በኮረብታውም ላይ አንድ ድንጋይ እንኳ አይቀርም።”

14 አቤሴሎምና እስራኤላውያን በሙሉ “ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የሑሻይ ምክር ይበልጣል” አሉ፤ በአቤሴሎም ላይ ጥፋት ይመጣበት ዘንድ እግዚአብሔር የአኪጦፌል መልካም ምክር ተቀባይ እንዳይኖረው አደረገ።


የዳዊት ማምለጥ

15 ከዚህ በኋላ እርሱና አኪጦፌል ለአቤሴሎምና ለእስራኤላውያን መሪዎች የሰጡትን ምክር ሑሻይ ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ነገራቸው፤

16 ከዚህም ጋር “እንግዲህ ዛሬ ሌሊት በበረሓ ውስጥ በሚገኘው በወንዙ መሻገሪያ ላይ እንዳያድር በፍጥነት መልእክተኛ ልካችሁ ለዳዊት ንገሩት! ነገር ግን እርሱና ተከታዮቹ ተይዘው እንዳይገደሉ በፍጥነት የዮርዳኖስን ወንዝ ይሻገሩ!” አላቸው።

17 የአብያታር ልጅ ዮናታንና የሳዶቅ ልጅ አሒማዓጽ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ማንም እንዳያያቸው ስለ ፈሩ፥ ከኢየሩሳሌም አካባቢ ባለችው በዔንሮጌል ምንጭ አጠገብ ይጠባበቁ ነበር፤ አንዲት ልጃገረድ አገልጋይም ዘወትር ወደዚያ እየሄደች የሚሆነውን ነገር ሁሉ ትነግራቸው ነበር፤ ከዚያም በኋላ እነርሱ ሄደው ለንጉሥ ዳዊት ይነግሩት ነበር።

18 ነገር ግን አንድ ቀን አንድ ልጅ እነርሱን ስላያቸው ሄዶ ለአቤሴሎም ነገረው፤ ስለዚህ እነርሱ በባሑሪም በሚገኘው በአንድ ሰው ቤት ለመሸሸግ ሮጠው ሄዱ፤ ሰውየው በቤቱ አጠገብ የውሃ ጒድጓድ ስለ ነበረው ወደዚያ ውስጥ ገቡ።

19 የዚያም ሰው ሚስት ጒድጓዱን ሸፍና በላዩ ላይ ማንም ሰው እንዳይጠረጥር እህል አሰጣችበት።

20 የአቤሴሎም ባለሟሎች ወደዚያ ቤት መጥተው ሴቲቱን “አሒማዓጽና ዮናታን የት ናቸው?” ሲሉ ጠየቁአት። እርስዋም “ወንዙን ተሻግረው ሄደዋል” ስትል መለሰች። ሰዎቹም ፈልገው ሊያገኙአቸው ስላልቻሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

21 እነርሱም ከሄዱ በኋላ አሒማዓጽና ዮናታን በፍጥነት ከጒድጓዱ ወጥተው በመሄድ የሆነውን ሁሉ ለንጉሥ ዳዊት ነገሩት፤ አኪጦፌል በእነርሱ ላይ ዐቅዶት የነበረውን ካስረዱት በኋላም “ፈጥነህ ወንዙን ተሻገር!” አሉት።

22 ስለዚህም ዳዊትና ተከታዮቹ የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር ጀመሩ፤ እስኪነጋም ድረስ ሁሉም ወንዙን ተሻግረው ነበር።

23 አኪጦፌል የሰጠው ምክር ተቀባይነት እንዳላገኘ በተረዳ ጊዜ አህያውን ጭኖ ወደ መኖሪያ ከተማው ተመልሶ ሄደ፤ ሁሉን ነገር መልክ በማስያዝ ካስተካከለም በኋላ ተሰቅሎ ሞተ፤ በቤተሰቡም መቃብር ተቀበረ።

24 አቤሴሎምና እስራኤላውያን ሁሉ የዮርዳኖስን ወንዝ በተሻገሩ ጊዜ ዳዊት ማሕናይም ተብላ ወደምትጠራው ትንሽ ከተማ ደርሶ ነበር፤

25 አቤሴሎም በኢዮአብ ምትክ ዐማሣ ተብሎ የሚጠራውን ሰው የጦር አዛዥ አድርጎ ሾመ፤ ዐማሣ የእስራኤላዊው የዬቴር ልጅ ነበር፤ እናቱም አቢጌል ተብላ የምትጠራ የናሐሽ ልጅ ስትሆን ለኢዮአብ እናት ለጸሩያ እኅት ነበረች። ዜና መ. 2፥17

26 አቤሴሎምና ሠራዊቱም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ።

27 ዳዊት ማሕናይም በደረሰ ጊዜ በዐሞን ግዛት ራባ ተብላ ከምትጠራው ከተማ የመጣውን የናዖስን ልጅ ሾቢን፥ ከሎደባር ከተማ የመጣውን የዓሚኤልን ልጅ ማኪርንና ከገለዓድ ግዛት ሮገሊም ተብላ ከምትጠራው ከተማ የመጣውን ባርዚላይን አገኘ።

28-29 እነርሱም ምንቸቶችንና የሸክላ ማሰሮዎችን፥ የመኝታ አልጋዎችንም ይዘው መጡ፤ እንዲሁም ለዳዊትና ለተከታዮቹ የሚሆን ስንዴ፥ ገብስ፥ ዱቄት፥ የተጠበሰ እሸት፥ ባቄላ፥ አተር፥ ማር፥ አይብ፥ እርጎና በጎችን አመጡ፤ ይህንንም ያደረጉበት ምክንያት ዳዊትና ተከታዮቹ በበረሓ ኑሮ እንደሚርባቸው፥ እንደሚጠማቸውና እንደሚደክማቸው በማሰብ ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos