ዘዳግም 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 “ ከመካከልህ ነቢይ ወይም ሕልም አላሚ ተነሥቶ ‘ተአምር ወይም አስደናቂ ነገር አደርጋለሁ’ ይል ይሆናል። 2 አደርጋለሁ ብሎ የተናገረውን ተአምርና ድንቅ ነገር ቢያደርግም እንኳ፥ አንተ የማታውቃቸውን ሌሎች አማልክት እንከተል፤ እናምልካቸውም ቢልህ፥ 3 እግዚአብሔር አምላካችሁ በፍጹም ልባችሁ ትወዱት እንደ ሆነ ለማወቅ ፈልጎ ልኮት ይሆናልና ያን ነቢይ ወይም አላሚ አትስሙት። 4 አምላካችሁን እግዚአብሔርን ተከተሉት፤ እርሱን ብቻ ፍሩ፤ ትእዛዞቹንም ጠብቁ፤ ቃሉንም ስሙ፤ እርሱንም አምልኩ፤ ከእርሱም ጋር ያላችሁ አንድነት የጠበቀ ይሁን። 5 በባርነት ከኖራችሁባት ከግብጽ ምድር ነጻ በማውጣት በአዳናችሁ በእግዚአብሔር ላይ እንድታምፁ የሚያደርጋችሁን ሕልም አላሚ ወይም ነቢይ ነኝ ባዩን ሁሉ ግደሉ፤ እንደዚህ ያለው ሰው ጸንታችሁ እንድትኖሩበት እግዚአብሔር አምላካችሁ ካዘዛችሁ መንገድ ሊለያችሁ ያቀደ ነው፤ ስለዚህ እናንተ ይህን ክፉ ነገር ከመካከላችሁ አስወግዱ። 6-7 “በቅርብም ሆነ በሩቅ ካሉት፥ ከአንዱ የምድር ዳርቻ በአካባቢህ ካሉ ከአሕዛብ አማልክት አንተ ወይም አባቶችህ የማታውቁትን አንዱን እናምልክ በማለት ሌላ እንኳ ቀርቶ የአባትህ፥ ወይም የእናትህ ልጅ ወንድምህ፥ ወንድ ልጅህ፥ ወይም ሴት ልጅህ ወይም የምትወዳት ሚስትህ ወይም የቅርብ ወዳጅህ በምሥጢር ይገፋፋህ ይሆናል። 8 ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለውን ሰው ያግባባህ ዘንድ አትፍቀድለት፤ የሚናገረውን እንኳ አታድምጥ፤ ምሕረትም ሆነ ርኅራኄ በማድረግ ሕይወቱን ለማዳን አትሞክር። 9 ያለ ማመንታት እንዲሞት አድርግ፤ ይልቁንም በእርሱ ላይ ድንጋይ በመወርወር የመጀመሪያ ሁን፤ ሌላውም ሁሉ ተባብሮ በድንጋይ ወግሮ ይግደለው። 10 በባርነት ከኖርክበት ከግብጽ ምድር ነጻ ካወጣህ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ሊያርቅህ ስለ ሞከረ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ውገረው፤ 11 ከዚህም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የሆነውን ነገር ሰምተው ይፈራሉ፤ ስለዚህም ያንን ዐይነት ክፉ ነገር እንደገና የሚያደርግ አይኖርም። 12-13 “እግዚአብሔር አምላክህ እንድትኖርባቸው ከሰጠህ ከተሞች በአንደኛዋ ውስጥ አንዳንድ ወራዶች ሰዎች ከመካከልህ ተነሥተው ነዋሪዎቹን ወደማታውቃቸው ወደ ሌሎች አማልክት ‘እንሂድና እናምልክ’ ብለው ወደ ጥፋት መንገድ መርተው መውሰዳቸውን ትሰማ ይሆናል፤ 14 ይህን በምትሰማበት ጊዜ ስለ ጉዳዩ ጠይቀህ ጠለቅ አድርገህ መርምር፤ ይህ አስከፊ የሆነው ጉዳይ በመካከላችሁ መደረጉ በእውነት ከተረጋገጠ፥ 15 በዚያች ከተማ የሚኖሩትን ሰዎች ከከብቶቻቸው ሁሉ ጋር በሙሉ ግደል፤ ያቺንም ከተማ በፍጹም ደምስስ። 16 የዚያችን ከተማ ሰዎች ሀብት በሙሉ ሰብስበህ በማምጣት በከተማይቱ አደባባይ እንዲከመር አድርግ፤ ከዚያም በኋላ ከተማይቱንና ሀብቱን ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገህ በእሳት አቃጥለው፤ ዳግመኛም እንዳትሠራ ለዘለዓለም ፍርስራሽ ሆና ትቅር። 17 እግዚአብሔር ከአስፈሪ ቊጣው ተመልሶ ምሕረት ያደርግልህ ዘንድ እንዲወድም ከተወሰነው ሀብት አንዳችም ለራስህ አታስቀር፤ ይህን ብታደርግ ለአባቶችህ በመሐላ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ቊጥርህን ያበዛዋል። 18 ዛሬ እኔ የሰጠሁህን ትእዛዞች ብትጠብቅና እርሱ ከአንተ የሚፈልገውንም ሁሉ ብታደርግ ይህ ተስፋ በእርግጥ ይፈጸምልሃል። |