Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ሮሜ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እንደ መረጠ

1 በክርስቶስ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው ኅሊናዬም እንደማልዋሽ ይመሰክርልኛል።

2 ትልቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ጭንቀት በልቤ አለ፤

3 በሥጋ ዘመዶቼ ስለ ሆኑት ወገኖቼ ስል እኔ ከክርስቶስ ተለይቼ የእግዚአብሔር ርግማን ቢደርስብኝ በወደድኩ ነበር።

4 እነርሱ እስራኤላውያን ናቸው፤ እግዚአብሔርም እነርሱን ልጆቹ አደረጋቸው፤ ክብሩን ገለጠላቸው፤ ቃል ኪዳን ገባላቸው፤ ሕግን ሰጣቸው፤ እውነተኛውን የአምልኮ ሥርዓት አሳያቸው፤ የተስፋውንም ቃል ሰጣቸው።

5 እነርሱ በትውልዳቸው ከነገድ አባቶች የመጡ ናቸው፤ ክርስቶስም በሥጋ የመጣው ከእነርሱ ዘር ነው፤ እርሱ ከሁሉ በላይ ነው፤ ለዘለዓለምም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን!

6 ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ተሽሮአል ማለት አይደለም፤ የእስራኤል ዘር በሙሉ እውነተኞች እስራኤላውያን አይደሉም።

7 እንዲሁም የአብርሃም ዘር ሁሉ የአብርሃም ልጆች ናቸው ማለት አይደለም። እግዚአብሔር አብርሃምን “ዘር የሚወጣልህ በይስሐቅ ነው” ስላለው ነው፤

8 ስለዚህ በሥጋ የተወለዱት የእግዚአብሔር ልጆች አይደሉም፤ ነገር ግን ዘር ሆነው የሚቈጠሩት የተስፋው ቃል ልጆች ብቻ ናቸው።

9 ይህም እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ እመጣለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” የሚል ነበር።

10 ይህም ብቻ ሳይሆን ርብቃ የነገድ አባታችን ከሆነው ከይስሐቅ መንታ ልጆችን በፀነሰች ጊዜ፥

11 የእግዚአብሔር ምርጫ በሥራ ሳይሆን በጥሪ መሆኑን ለመግለጥ ሁለቱ ልጆች ከመወለዳቸውና ክፉም ሆነ ደግ ከማድረጋቸው በፊት

12 እግዚአብሔር ርብቃን “ታላቁ ለታናሹ ተገዢ ይሆናል” አላት።

13 ይህም “ያዕቆብን ወደድኩ ዔሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

14 እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያዳላል ማለት እንችላለን? እግዚአብሔር ያዳላል ማለትስ ከቶ አንችልም!

15 እግዚአብሔር ሙሴን “ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፥ ልራራለት የምፈልገውንም እራራለታለሁ” ብሎታል።

16 ስለዚህ የእግዚአብሔር ምርጫ የሚገኘው በሰው ፈቃድና በሰው ሥራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ምሕረት ነው።

17 በዚህ ምክንያት በቅዱስ መጽሐፍ ስለ ግብጽ ንጉሥ “በአንተ ኀይሌን ለማሳየትና ስሜም በዓለም ሁሉ ላይ እንዲታወቅ ለማድረግ አንተን አንግሼሃለሁ” የሚል ቃል ተጽፎአል።

18 ስለዚህ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ይምረዋል፤ የሚፈልገውንም እልኸኛ ያደርገዋል።


የእግዚአብሔር ቊጣና ምሕረት

19 ስለዚህ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመቃወም ማንም አይችልም፤ ታዲያ፥ እርሱ ሰዎችን በክፉ ሥራቸው ለምን ይወቅሳቸዋል” ብለህ ትጠይቀኝ ይሆናል።

20 አንተ ሰው! ከእግዚአብሔር ጋር ለመከራከር ምን መብት አለህ? የሸክላ ዕቃ ሠሪውን “ለምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?” ሊለው ይችላልን?

21 ሸክላ ሠሪ ከአንድ ዐይነት የሸክላ ጭቃ አንዱን ዕቃ ለክብር፥ ሌላውን ለተራ አገልግሎት አድርጎ ለመሥራት ሥልጣን የለውምን?

22 እግዚአብሔር ቊጣውን ለማሳየትና ኀይሉንም ለመግለጥ ፈልጎ ለጥፋት የተዘጋጁትን የቊጣ ዕቃዎች ብዙ ታግሦአቸውስ እንደ ሆነ ምን ታውቃለህ?

23 ይህንንም ያደረገው አስቀድሞ ለክብር ላዘጋጃቸው ለምሕረት ዕቃዎች የክብሩን ብዛት ለመግለጥ ነው።

24 እኛን የምሕረት ዕቃዎቹንም ከአይሁድ ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብም ጠርቶናል።

25 ይህም በነቢዩ በሆሴዕ እንዲህ እንደ ተባለ ነው፦ “የእኔ ሕዝብ ያልነበረውን ‘ሕዝቤ!’ ብዬ እጠራዋለሁ፤ ያልተወደደውንም ሕዝብ ‘የተወደደ!’ ብዬ እጠራዋለሁ፤

26 እነርሱ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ በተባሉበት ስፍራ ‘የሕያው እግዚአብሔር ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ።”

27 ኢሳይያስም ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፤ “የእስራኤል ልጆች ቊጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢበዛ እንኳ ከእነርሱ የሚድኑት ጥቂቶች ብቻ ናቸው።

28 ጌታ ሳይዘገይ በፍጥነት በዓለም ላይ ፍርዱን ይሰጣል።”

29 እንዲሁም ኢሳይያስ “የሠራዊት ጌታ ዘር ባያስቀርልን ኖሮ የሰዶምና የገሞራ ከተሞች እንደ ጠፉ እኛም በጠፋን ነበር” ሲል አስቀድሞ ተናግሮአል።

30 እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅን ያልተከተሉት አሕዛብ ጽድቅን አገኙ፤ ይህም ጽድቅ ከእምነት የሚገኘው ነው።

31 ነገር ግን ጽድቅ የሚያስገኘውን ሕግ ይከተሉ የነበሩት እስራኤላውያን ሕግን ለመፈጸም ባለመቻላቸው ወደ ጽድቅ አልደረሱም።

32 “ስለምን ወደ ጽድቅ አልደረሱም?” ቢባል እነርሱ ጽድቅን ለማግኘት የፈለጉት በእምነት ሳይሆን በሥራ ስለ ሆነ ነው፤ ስለዚህ በማሰናከያ ድንጋይ ተሰናከሉ፤

33 ይህም፦ “እነሆ፥ ሰዎችን የሚያሰናክል ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ፤ ይህም ድንጋይ ሰዎችን በማሰናከል የሚጥል አለት ነው፤ በእርሱ የሚያምን ግን አያፍርም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos