Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ሆሴዕ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የሆሴዕ ሚስትና ልጆች ምሳሌነት

1 ዖዝያን፥ ኢዮአታም፥ አካዝና ሕዝቅያስ በይሁዳ ተከታትለው በነገሡባቸው ዘመናት፤ እንዲሁም የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም የእስራኤል ንጉሥ በነበረበት ዘመን፥ እግዚአብሔር ለብኤር ልጅ ለሆሴዕ የገለጠለት የትንቢት ቃል ይህ ነው።

2 እግዚአብሔር በሆሴዕ አማካይነት ለእስራኤል ሕዝብ ቃሉን ማስተላለፍ ሲጀምር ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቤ ከእኔ ተለይቶ አጸያፊ የሆነ የዝሙት ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፤ እንግዲህ አንተም ሂድና ዘማዊት ሴት አግባ፤ ከእርስዋም የዝሙት ልጆችን ውለድ።”

3 ስለዚህ ሆሴዕ ሄዶ የዲብላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፤ እርስዋም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደችለት።

4 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ “ኢዩና ዘሮቹ በኢይዝራኤል በገደሉአቸው ሰዎች ምክንያት የኢዩን ቤተሰብ የምቀጣበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፤ የእስራኤልም መንግሥት እንዲያከትም አደርጋለሁ፤

5 በዚያን ጊዜ በኢይዝራኤል ሸለቆ የእስራኤልን ጦር እደመስሳለሁ፤ ስለዚህ የልጅህን ስም ‘ኢይዝራኤል’ ብለህ ጥራው።”

6 ጎሜር ዳግመኛ ፀንሳ ሴት ልጅ ወለደች፤ እግዚአብሔርም ሆሴዕን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሕዝብ ከእንግዲህ ወዲህ ፍቅር አላሳያቸውም፤ ይቅርታም አላደርግላቸውም፤ ስለዚህ የልጅህን ስም ‘ሎሩሐማ’ ብለህ ጥራት።

7 ለይሁዳ ሕዝቦች ግን ፍቅር አሳያቸዋለሁ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር አድናቸዋለሁ፤ የማድናቸውም በጦርነት ኀይል አይደለም፤ በሰይፍ፥ በቀስትና በፍላጻ ወይም በፈረስና በፈረሰኛ አይደለም።”

8 ጎሜር ሎሩሐማን ጡት ካስጣለች በኋላ እንደገና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች።

9 እግዚአብሔርም ሆሴዕን “ከእንግዲህ ወዲህ የእስራኤል ሕዝብ ወገኖቼ አይደሉም፤ እኔም የእነርሱ አምላክ አይደለሁም፤ ስለዚህ የልጅህን ስም ‘ሎዓሚ’ ብለህ ጥራው አለው።”


ለእስራኤል ሕዝብ የተነገረ የተስፋ ቃል

10 የእስራኤል ሕዝብ ብዛት ሊቈጠር ወይም ሊለካ እንደማይቻል የባሕር አሸዋ ይሆናል፤ አሁን እግዚአብሔር “ሕዝቤ አይደላችሁም” ቢላቸው በዚሁ ስፍራ “የሕያው እግዚአብሔር ልጆች!” ተብለው የሚጠሩበት ጊዜ ይመጣል፤

11 በዚያን ጊዜ የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ አንድ ይሆናሉ፤ ሁለቱንም የሚያስተዳድር አንድ መሪ ይመርጣሉ፤ እንደገናም በገዛ ምድራቸው ላይ በዕድገትና በብልጽግና ይኖራሉ፤ የኢይዝራኤልም ቀን ታላቅ ይሆናል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos