ዘፍጥረት 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየይስሐቅና የርብቃ ጋብቻ 1 በዚህ ጊዜ አብርሃም በጣም አርጅቶ ነበር፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሁሉም ነገር ባረከው። 2 አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ በመሆን ለረዥም ዘመን የኖረውን አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ “እጅህን በጒልበቴ ላይ አድርገህ ማልልኝ፤ 3 ይኸውም እኔ በመካከላቸው ከምኖረው ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች መካከል ለልጄ ሚስት እንዳትመርጥ በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር ስም ማልልኝ፤ 4 ነገር ግን ወደ ትውልድ አገሬ ሂድ፤ እዚያም ካሉት ወገኖቼ መካከል ለልጄ ለይስሐቅ ሚስት ምረጥለት።” 5 አገልጋዩም “ምናልባት የምመርጥለት ሴት ከእኔ ጋር ወደዚህ አገር ለመምጣት እምቢ ብትልስ? ልጅህን ቀድሞ አንተ ወደነበርክበት አገር እንዲመለስ ላድርገውን?” ብሎ ጠየቀ። 6 አብርሃም ግን እንዲህ አለው፤ “በምንም ምክንያት ቢሆን ልጄን ወደዚያ አገር መልሰህ እንዳትወስድ ተጠንቀቅ! 7 ከአባቴ ቤትና ከትውልድ አገሬ አውጥቶ ይህን ምድር ለዘሬ እንደሚሰጥ በመሐላ ቃል የገባልኝ እግዚአብሔር፥ የሰማይ አምላክ ከዚያ ለልጄ ሚስት ማግኘት እንድትችል መልአኩን በፊትህ ይልካል። 8 ልጅትዋ ከአንተ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ከዚህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ልጄን ግን በምንም ዐይነት ወደዚያ አትመልሰው።” 9 ከዚህ በኋላ አገልጋዩ እጁን በጌታው በአብርሃም ጒልበት ላይ አድርጎ አብርሃም ያዘዘውን ሁሉ እንደሚፈጽም በመሐላ ቃል ገባ። 10 የአብርሃም ንብረት ኀላፊ የነበረው መጋቢ ከጌታው ቤት ምርጥ የሆኑ የስጦታ ዕቃዎችን በዐሥር ግመሎች ጭኖ በሰሜን መስጴጦምያ ናኮር ወደሚኖርበት ከተማ ሄደ። 11 እዚያ በደረሰ ጊዜ ከከተማው ውጪ ባለ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ግመሎቹ ተንበርክከው እንዲያርፉ አደረገ፤ ሰዓቱም ሊመሽ ተቃርቦ፥ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት የሚወጡበት ጊዜ ነበር፤ 12 አገልጋዩም እንዲህ ብሎ ጸለየ፤ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ዛሬ የእኔን ሐሳብ በመፈጸም ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን ግለጥ። 13 እነሆ፥ እኔ በዚህ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማይቱም ልጃገረዶች ውሃ ሊቀዱ ወደዚህ ይመጣሉ፤ 14 ከእነርሱም አንድዋን ልጃገረድ ‘እንስራሽን ዘንበል አድርገሽ ውሃ አጠጪኝ’ እላታለሁ፤ ‘አንተም ጠጣ፤ ግመሎችህም እንዲጠጡ ውሃ ቀድቼ አመጣለሁ’ ካለችኝ ለአገልጋይህ ለይስሐቅ ሚስት እንድትሆን የመረጥካት እርስዋ ትሁን፤ በዚህም ሁኔታ ለጌታዬ ለአብርሃም ዘለዓለማዊ ፍቅርህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።” 15 ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ ርብቃ እንስራ ተሸክማ መጣች፤ የዚህችም ልጅ አባት በቱኤል ይባል ነበር፤ እርሱም የአብርሃም ወንድም ናኮር ከሚስቱ ከሚልካ የወለደው ነው። 16 ርብቃ ገና ወንድ ያልደረሰባት በጣም ቈንጆ ልጃገረድ ነበረች፤ እርስዋ ወደ ውሃው ጒድጓድ ወርዳ በእንስራዋ ውሃ ከቀዳች በኋላ ተመለሰች። 17 አገልጋዩም ወደ እርስዋ ሮጦ ሄደና “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት። 18 እርስዋም “እሺ ጌታዬ ጠጣ” አለችና እንስራዋን ከትከሻዋ አውርዳ ዘንበል አድርጋ ያዘችለት። 19 ጠጥቶም ከረካ በኋላ “ለግመሎችህም ውሃ እቀዳላቸዋለሁ፤ እስኪበቃቸውም ድረስ ይጠጡ” አለችው። 20 ወዲያውኑ በእንስራዋ የያዘችውን ውሃ ግመሎቹ በሚጠጡበት ገንዳ ላይ ገልብጣ ግመሎቹ ሁሉ ጠጥተው እስከሚረኩ ድረስ እየተጣደፈች ከጒድጓድ ውሃ መቅዳት ቀጠለች። 21 ሰውየውም እግዚአብሔር የሄደበትን ተልእኮ አቃንቶለት እንደሆን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ሁሉ ዝም ብሎ ይመለከት ነበር። 22 ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውየው አምስት ግራም ያኽል የሚመዝን የወርቅ ጒትቻ አውጥቶ በጆሮዋ ላይ አደረገላት፤ መቶ ዐሥር ግራም ያኽል የሚመዝን ሁለት የወርቅ አምባሮችንም አውጥቶ በእጆችዋ ላይ አደረገላትና፥ 23 “የማን ልጅ ነሽ? እስቲ እባክሽ ንገሪኝ፤ ለእኔና አብረውኝ ላሉት ሰዎች ማደሪያ የሚሆን ስፍራ በአባትሽ ቤት ይገኛልን?” ብሎ ጠየቃት። 24 እርስዋም “የባቱኤል ልጅ ነኝ፤ ባቱኤልም ሚልካ ለናኮር የወለደችለት ነው፤ 25 በቤታችን ብዙ ገለባና ድርቆሽ አለ፤ ለእናንተም ማደሪያ ቦታ ይገኛል” አለችው። 26 ሰውየውም በመንበርከክ ለእግዚአብሔር ሰግዶ፥ 27 “ለጌታዬ ያለውን ታማኝነትና ዘለዓለማዊ ፍቅር የጠበቀ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ በቀጥታ መርቶ ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት ያመጣኝ እርሱ ነው” አለ። 28 ልጅትዋ ወደ ቤት ሮጣ ሄደችና የሆነውን ሁሉ ለእናትዋና ከእርስዋ ጋር ላሉት ሁሉ ነገረቻቸው። 29 ርብቃ ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ እርሱ የአብርሃም አገልጋይ ወዳለበት ውሃ ጒድጓድ እየሮጠ ሄደ። 30 ላባ ወደ ሰውየው የሄደው እኅቱ በጆሮዋ ላይ ያደረገችውን ጒትቻና በእጆችዋ ላይ ያደረገቻቸውን አንባሮች ስላየና ርብቃ ሰውየው ያላትን ስትናገር ስለ ሰማም ነው። እርሱንም በውሃው ጒድጓድ አጠገብ ከግመሎቹ ጋር ቆሞ አገኘው። 31 ስለዚህ ላባ “አንተ እግዚአብሔር የባረከህ ሰው፥ ና ወደ ቤት እንሂድ፤ በውጪ የቆምከው ለምንድን ነው? በቤታችን ለአንተ ማረፊያ ስፍራ አለ፤ ለግመሎችህም ማደሪያ የተዘጋጀ ቦታ አለ” አለው። 32 ከዚህ በኋላ ሰውየው ወደ ቤት ሄደ፤ ላባም በግመሎቹ ላይ የነበረውን ጭነት አራግፎ ገለባና ድርቆሽ አቀረበላቸው፤ ቀጥሎም የአብርሃም አገልጋይና አብረውት የነበሩት ሰዎች እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አመጣላቸው። 33 ገበታ በቀረበ ጊዜ ሰውየው “የተላክሁበትን ጉዳይ ከመናገሬ በፊት እህል አልቀምስም” አለ። ላባም “ይሁን ተናገር” አለው። 34 እርሱም “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ፤ 35 እግዚአብሔር ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ ባለጸጋም አድርጎታል፤ ብዙ የበግ፥ የፍየልና የከብት መንጋ፥ ብርና ወርቅ፥ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮች ግመሎችና አህዮች ሰጥቶታል። 36 የጌታዬ ሚስት ሣራ በእርጅናዋ ዘመን ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤ ጌታዬም ያለውን ሀብት ሁሉ ለዚሁ ልጅ አውርሶታል። 37 ጌታዬም እንዲህ ሲል አስማለኝ፤ እኔ ካለሁበት አገር ከከነዓናውያን ሴቶች ለልጄ ሚስት አትምረጥ፤ 38 ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት ወደ ወገኖቼ ሄደህ ለልጄ ሚስት ምረጥ፤ 39 እኔም ጌታዬን ‘ልጅቷ ከእኔ ጋር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆንስ ምን ላድርግ?’ ብዬ ጠየቅሁት። 40 እርሱም እንዲህ አለኝ ‘ዘወትር የማገለግለው እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋር ይልካል፤ ጒዞህም የተቃና እንዲሆን ያደርጋል፤ በዚህ ሁኔታ አንተም ከአባቴ ቤተሰብና ከዘመዶቼ መካከል ለልጄ ሚስት ልታጭለት ትችላለህ፤ 41 ከመሐላህ ነጻ የምትሆነው ወደ ዘመዶቼ ሄደህ እነርሱ ልጅትዋን አንሰጥም ብለው የከለከሉህ እንደ ሆነ ብቻ ነው።’ 42 “ከዚህም በኋላ ዛሬ ወደ ውሃው ጒድጓድ ስመጣ እንዲህ ብዬ ጸለይኩ፤ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ እባክህ የመጣሁበት ጉዳይ እንዲቃና አድርግልኝ፥ 43 እነሆ፥ በዚህ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ አንዲት ልጃገረድ ውሃ ልትቀዳ ስትመጣ፥ እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ’ ብዬ እጠይቃታለሁ፤ 44 እርስዋም ‘እሺ ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ’ የምትለኝ ብትሆን፥ ለጌታዬ ልጅ ሚስት እንድትሆን አንተ የመረጥካት እርስዋ ትሁን። 45 የኅሊና ጸሎቴን ገና ሳልጨርስ ርብቃ እንስራ ተሸክማ ብቅ አለች፤ ወደ ጒድጓዱም ሄዳ ውሃ ቀዳች፤ እኔም ‘እባክሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ’ አልኳት። 46 እርስዋም እንስራዋን በፍጥነት ከትከሻዋ አወረደችና ዘንበል አድርጋ ‘እሺ ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣልሃለሁ’ አለችኝ፤ ስለዚህ እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቼንም አጠጣችልኝ። 47 እኔም ‘የማን ልጅ ነሽ?’ ብዬ ጠየቅኋት። እርስዋም ‘የባቱኤል ልጅ ነኝ፤ የባቱኤል አባት ናኮር እናቱም ሚልካ ይባላሉ’ አለችኝ። ከዚህ በኋላ ጒትቻ በጆሮዋ ላይ፥ አንባሮቹንም በእጆችዋ ላይ አደረግሁላት፤ 48 ከዚህ በኋላ ለጌታዬ ልጅ ሚስት የምትሆነዋን ሴት ወዳገኘሁበት ወደ ጌታዬ ወንድም ቤት በቀና መንገድ ለመራኝ ለእግዚአብሔር በጒልበቴ ተንበርክኬ ሰገድሁ፤ የጌታዬን የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንኩ፤ 49 እንግዲህ የጌታዬን ዐደራ በእውነት ተቀብላችሁ እርሱን ደስ ለማሰኘት የምትፈቅዱ እንደ ሆነ ንገሩኝ፤ የማትፈቅዱም እንደ ሆነ ቊርጡን ንገሩኝ፤ እኔም እግዚአብሔር ወደሚመራኝ እሄዳለሁ።” 50 ላባና ባቱኤልም “ይህ ነገር ከእግዚአብሔር የመጣ ስለ ሆነ፥ መከልከል አንችልም፤ 51 ርብቃ ይህችውልህ፤ እነሆ፥ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር ራሱ እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁን” አሉት። 52 የአብርሃም አገልጋይ ይህን በሰማ ጊዜ በጒልበቱ ተንበርክኮ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ 53 ከወርቅና ከብር የተሠሩ ጌጣጌጦችን፥ እንዲሁም ልብስ አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ለወንድምዋና ለእናትዋም በጣም ውድ የሆኑ ስጦታዎችን አውጥቶ ሰጣቸው። 54 ከዚህ በኋላ የአብርሃም አገልጋይና አብረውት የነበሩ ሰዎች በልተው ጠጥተው እዚያው ዐደሩ፤ ጠዋት በተነሡ ጊዜ የአብርሃም አገልጋይ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ ፍቀዱልኝ” አለ። 55 ነገር ግን የርብቃ ወንድምና እናትዋ “ልጅትዋ ዐሥር ቀን ያኽል ከእኛ ጋር ትቈይ፤ ከዚያ በኋላ ከአንተ ጋር ልትሄድ ትችላለች” አሉት። 56 እርሱ ግን “እባካችሁ አታቈዩኝ፤ እግዚአብሔር የመጣሁበትን ጉዳይ ስላቃናልኝ ቶሎ ብዬ ወደ ጌታዬ ልመለስ” አላቸው። 57 እነርሱም “እስቲ ልጅቷን እንጥራና እርስዋ የምትለውን እንስማ” አሉ። 58 ስለዚህ ርብቃን ጠሩና “ከዚህ ሰው ጋር መሄድ ትፈልጊያለሽን?” ብለው ጠየቅዋት። እርስዋም “አዎ እሄዳለሁ” አለች። 59 ስለዚህ ርብቃ ሞግዚትዋን አስከትላ፥ ከአብርሃም አገልጋይና ከእርሱ ሰዎች ጋር እንድትሄድ ፈቀዱላት። 60 “አንቺ እኅታችን የብዙ ሺህ ሕዝብ እናት ሁኚ፤ ዘሮችሽም የጠላቶቻቸውን ከተሞች ይውረሱ!” ብለው ርብቃን መረቁአት። 61 ከዚህ በኋላ ርብቃ ከደንገጡሮችዋ ጋር ለመሄድ ተነሣች፤ በግመሎቹ ላይ ተቀምጠው ከአብርሃም አገልጋይ ጋር ለመሄድ ተዘጋጁ። በዚህ ዐይነት የአብርሃም አገልጋይ ርብቃን ይዞ ሄደ። 62 በዚህ ጊዜ ይስሐቅ “ብኤር ላሐይ ሮኢ ወይም የሚያየኝ ሕያው አምላክ” የተባለው ኲሬ ወዳለበት በረሓ መጥቶ በኔጌብ ተቀምጦ ነበር። 63 ከዕለታት አንድ ቀን ወደ ማታ ጊዜ እያሰላሰለ በመስክ ውስጥ ሲዘዋወር ሳለ ግመሎች ሲመጡ በሩቅ አየ። 64 ርብቃ ይስሐቅን ባየች ጊዜ ከግመሏ ወረደችና፥ 65 “ያ በመስክ ውስጥ ወደ እኛ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል የአብርሃምን አገልጋይ ጠየቀችው። አገልጋዩም “እርሱ ጌታዬ ነው” አላት። ስለዚህ በፍጥነት በሻሽ ፊትዋን ሸፈነች። 66 አገልጋዩም ያደረገውን ነገር ሁሉ ለይስሐቅ ነገረው። 67 ከዚህ በኋላ ይስሐቅ እናቱ ሣራ ትኖርበት ወደነበረው ድንኳን ርብቃን ይዞአት ገባ፤ ሚስትም ሆነችው፤ ይስሐቅ ርብቃን ወደዳት፤ በእናቱ ሞት ምክንያት ከደረሰበትም ሐዘን በዚህ ሁኔታ ተጽናና። |