Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የአብራም መጠራት

1 እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “አገርህን ትተህ፥ ከዘመዶችህና ከአባትህ ቤተሰብ ተለይተህ፥ እኔ ወደማሳይህ አገር ሂድ፤

2 ዘርህን አበዛዋለሁ፤ ታላቅ ሕዝብም ይሆናል፤ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎችም በረከት ትሆናለህ።

3 የሚመርቁህን እመርቃለሁ፤ የሚረግሙህንም እረግማቸዋለሁ፤ በአንተም አማካይነት ሕዝቦች ሁሉ ይባረካሉ።”

4 አብራም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ከካራን ወጥቶ ሄደ፤ በዚያን ጊዜ ዕድሜው ሰባ አምስት ዓመት ነበር፤ ሎጥም አብሮት ሄደ።

5 አብራም፥ ሚስቱ ሣራይና የወንድሙ ልጅ ሎጥ፥ በካራን ሳሉ ያገኙትን ሀብትና አገልጋዮቻቸውን ሁሉ ይዘው ወደ ከነዓን ምድር ሄዱ። ከነዓን በደረሱ ጊዜ፥

6 አብራም በሴኬም ወደሚገኘው ቅዱስ ስፍራ ወደ ሞሬ ዛፍ እስኪደርስ ድረስ ተጓዘ፤ በዚያን ጊዜ ከነዓናውያን በዚያች ምድር ይኖሩ ነበረ።

7 እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና “ለዘርህ የምሰጠው ምድር ይህ ነው” አለው፤ ከዚህ በኋላ አብራም ለተገለጠለት አምላክ በዚያ ቦታ መሠዊያ ሠራ።

8 ቀጥሎም ከቤትኤል በስተምሥራቅ ወዳለው ተራራማ አገር ወጣ፤ ቤትኤልን በስተምዕራብ፥ ዐይን በስተምሥራቅ አድርጎ ድንኳኑን ተከለ፤ በዚያም መሠዊያ ሠራና ለእግዚአብሔር ሰገደ፤

9 ከቦታ ወደ ቦታ እየተዘዋወረም ወደ ኔጌብ መጣ።


አብራም በግብጽ አገር

10 በከነዓን ምድር ራብ ገባ፤ ራብም እየበረታ በመሄዱ አብራም የራቡን ጊዜ ለማሳለፍ በስተደቡብ ርቆ ወደ ግብጽ አገር ሄደ።

11 አብራም ወደ ግብጽ ምድር ለመግባት በተቃረበ ጊዜ ሚስቱን ሣራይን እንዲህ አላት፤ “አንቺ በጣም ቈንጆ ሴት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤

12 ግብጻውያን አንቺን በሚያዩበት ጊዜ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ በማለት እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺን ግን በሕይወት እንድትኖሪ ይተዉሻል።

13 ስለዚህ ‘እኅቱ ነኝ’ በያቸው፤ በዚህ ዐይነት በአንቺ ምክንያት በሕይወት እንድኖር ይተዉኛል፤ በደኅና ዐይንም ይመለከቱኛል።”

14 ወደ ግብጽ በገቡ ጊዜ በእርግጥም ግብጻውያን የአብራም ሚስት በጣም ቈንጆ እንደ ሆነች አዩ።

15 እንዲሁም አንዳንድ የፈርዖን ባለሟሎች ባዩአት ጊዜ ስለ ቁንጅናዋ ለፈርዖን ተናገሩ፤ ስለዚህ ወደ ቤተ መንግሥት ተወሰደች።

16 በእርስዋ ምክንያት ንጉሡ አብራምን በደኅና ዐይን ተመለከተው፤ በጎች፥ ከብቶች፥ አህዮች፥ ግመሎች፥ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን ሰጠው።

17 ነገር ግን በአብርሃም ሚስት በሣራይ ምክንያት እግዚአብሔር በእርሱና በባለሟሎቹ ሁሉ ላይ አሠቃቂ በሽታዎች አመጣባቸው።

18 ከዚህ በኋላ ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ ሲል ጠየቀው “ይህ ያደረግኽብኝ ነገር ምንድን ነው? ሣራይ ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልነገርከኝም?

19 ‘እኅቴ ነች’ ብለህ በሚስትነት እንድወስዳት ለምን አደረግህ? ይህችውና ሚስትህ፥ ይዘሃት ውጣ፤”

20 ንጉሡ ባዘዛቸው መሠረት ባለሟሎቹ አብራምንና ሚስቱን ካለው ሀብት ሁሉ ጋር ከአገር አስወጡአቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos