Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘፍጥረት 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር ከአብራም ጋር የገባው ቃል ኪዳን

1 ከዚህ በኋላ አብራም ራእይ አየ፤ እግዚአብሔርም “አብራም፥ አትፍራ፤ እንደ ጋሻ ሆኜ ከአደጋ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ታላቅ በረከትም እሰጥሃለሁ” ሲል ሰማው።

2 አብራምም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ጌታ አምላክ ሆይ፥ ምንም ልጅ ስለሌለኝ የምትሰጠኝ በረከት ምን ያደርግልኛል? ሀብቴን የሚወርሰው የደማስቆ ሰው የሆነው ኤሊዔዘር ነው።

3 ምንም ዘር ስላልሰጠኸኝ ሀብቴን የሚወርሰው በቤቴ የተወለደ አገልጋይ ነው።”

4 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል “ይህ ኤሊዔዘር የተባለው አገልጋይ የአንተን ሀብት አይወርስም፤ ከአንተ የሚወለደው ልጅ ወራሽህ ይሆናል” ብሎ ሲነግረው ሰማ።

5 ቀጥሎም እግዚአብሔር አብራምን ወደ ውጪ አወጣውና “ወደ ሰማይ ተመልከት፤ ከዋክብትን መቊጠር ትችል እንደሆን ሞክር፤ እንግዲህ የአንተም ዘሮች እንደዚህ ይበዛሉ” አለው።

6 አብራም በእግዚአብሔር አመነ፤ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት።

7 ደግሞም እግዚአብሔር አብራምን “ይህችን አገር በውርስ ለአንተ እንድሰጥህ ዑር ከምትባለው ከከለዳውያን ምድር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” አለው።

8 አብራም ግን “ጌታ አምላክ ሆይ፥ ይህች ምድር የእኔ እንደምትሆን እንዴት ለማወቅ እችላለሁ?” ሲል ጠየቀ።

9 እግዚአብሔርም “ሦስት፥ ሦስት ዓመት የሆናቸው አንድ ጊደር፥ አንድ ፍየልና፥ አንድ በግ፥ እንዲሁም ዋኖስና ርግብ አምጣልኝ” አለው።

10 አብራምም እነዚህን ሁሉ ወደ እግዚአብሔር አምጥቶ እያንዳንዱን እየቈረጠ በሁለት ከፈለው፤ የተከፈሉትንም ትይዩ አድርጎ በሁለት መስመር አስቀመጣቸው። ወፎቹን ግን ቈርጦ አልከፈላቸውም።

11 አሞራዎች የተቈራረጠውን ሥጋ ለመብላት ሲመጡ አብራም አባረራቸው።

12 የፀሐይ መጥለቂያ ሰዓት እየተቃረበ ሲሄድ አብራምን ከባድ እንቅልፍ ያዘው፤ እነሆ፥ ድንጋጤና ታላቅ ጨለማ መጣበት።

13 እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፦ “የልጅ ልጆችህ በባዕድ አገር ስደተኞች እንደሚሆኑ ዕወቅ፤ እዚያም በባርነትና በጭቈና ለአራት መቶ ዓመት ያስጨንቁአቸዋል፤

14 በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እቀጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ ብዙ ሀብት ይዘው ከዚያ አገር ይወጣሉ።

15 አንተ ግን ብዙ ዘመን ኖረህ በሰላም ትሞታለህ፤ በሰላምም ትቀበራለህ።

16 የልጅ ልጆችህ ወደዚህ ተመልሰው የሚመጡት በአራተኛው ትውልድ ነው፤ እስከዚያ የሚቈዩበትም ምክንያት የአሞራውያን ኃጢአት ገና ስላልተፈጸመ ነው።”

17 ፀሐይ ጠልቃ በጨለመ ጊዜ የምድጃ እሳት ጢስና ነበልባል ታየ፤ በተቈራረጠውም ሥጋ መካከል አለፈ።

18 በዚያን ዕለት እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ በማለት ቃል ኪዳን ገባለት፦ “ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ሁሉ ለዘሮችህ እሰጣለሁ፤

19 እንዲሁም የቄናውያንን፥ የቀኒዛውያንን፥ የቃድሞናውያንን፥

20 የሒታውያንን፥ የፈሪዛውያንን፥ የረፋያውያንን፥

21 የአሞራውያንን፥ የከነዓናውያንን፥ የጌርጌሳውያንን፥ የኢያቡሳውያንን ምድር እሰጣለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos