ዘፍጥረት 2:7 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ከመሬት ዐፈር ወስዶ፥ ሰውን ከዐፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም ሕይወትን የሚሰጥ እስትንፋስ “እፍ” አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ፍጡር ሆነ። አዲሱ መደበኛ ትርጒም እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ከዚህ በኋላ ጌታ እግዚአብሔር ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፥ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፥ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) እግዚአብሔር አምላክም ሰውንም ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። |
እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በውስጣችሁ እስትንፋስ በማስገባት እንደገና በሕይወት እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ።
ጅማትና ሥጋ በመስጠት ቆዳ አለብሳችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አስገብቼ እንደገና በሕይወት እንድትኖሩ አደርጋችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ”
ሙሴና አሮን በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው እንዲህ አሉ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነህ፤ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ በመላው ማኅበር ላይ ትቈጣለህን?”
“ለሰው ሁሉ ሕይወትን የምትሰጥ፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ሕዝብህ እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ እንዳይሆን፥ ሕዝብህን የሚመራ አንድ ሰው ምረጥ።”
ነገር ግን ይህ ከሁሉ የሚበልጠው ኀይል የእግዚአብሔር እንጂ የእኛ አለመሆኑ እንዲታወቅ ይህን ክቡር ነገር እንደ ሸክላ ዕቃ ሆነን ይዘነዋል።
ይህ እንደ ድንኳን ጊዜያዊ የሆነው ምድራዊው ሥጋችን ሲፈርስ በሰው እጅ ሳይሆን በእግዚአብሔር የታነጸ ዘለዓለማዊ መኖሪያ በሰማይ እንዳለን እናውቃለን።
ከዚህም በቀር እኛ ሁላችን የሚቀጡን የሥጋ አባቶች ነበሩን፤ እናከብራቸውም ነበር፤ ታዲያ፥ በሕይወት ለመኖር ለመንፈሳዊ አባታችን በይበልጥ መታዘዝ እንዴት አይገባንም!