Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሰቈቃወ 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በኢየሩሳሌም ላይ ስለሚደርሰው ቅጣት

1 ቤተ መቅደስ የታነጸባቸው ድንጋዮች በየመንገዱ ተበታተኑ። ወርቁ እንዴት ደበዘዘ! ንጹሑስ ወርቅ እንዴት ተለወጠ!

2 የከበሩ የጽዮን ልጆች እንደ ንጹሕ ወርቅ ያኽል ውድ ነበሩ፤ እንዴት አሁን የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው እንደ ሸክላ ዕቃ ተቈጠሩ!

3 ቀበሮዎች እንኳን የወለዱአቸውን ከጡታቸው ይመግባሉ፤ ሕዝቤ ግን እንደ ምድረ በዳ ሰጎኖች ጨካኞች ሆነዋል።

4 በውሃ ጥም ምክንያት የሕፃናት ምላስ ከትናጋቸው ጋር ተጣበቀ፤ ልጆቻቸው ምግብ ይለምናሉ፤ ነገር ግን ምንም ነገር የሚሰጣቸው ሰው የለም።

5 ቀደም ብለው ምርጥ ምግብ ይመገቡ የነበሩት፥ አሁን በመንገድ ላይ ወድቀዋል። ሐምራዊ ልብስ ለብሰው ያደጉት አሁን በዐመድ ክምር ላይ ተጋደሙ።

6 በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት የማንም እጅ ሳያርፍበት በቅጽበት ከተገለበጠችው ከሰዶም ቅጣት የበለጠ ነው።

7 ልዑላን መሳፍንታችን ርኲሰት የማይገኝባቸው፥ ከበረዶ ይልቅ የጠሩ፥ ከወተትም ይልቅ የነጡ ነበሩ፤ መልካቸውም እንደ ሰንፔር ያማረ ነበር፤

8 አሁን ግን ፊታቸው እንደ ጥላሸት ስለ ጠቈረ፥ በየመንገዱ ወድቀው ሲገኙ የሚያውቃቸው የለም፤ እንደ እንጨት የደረቀ ቆዳቸው በአጥንታቸው ላይ ተጣብቆአል።

9 የምድር ምርትን በማጣት ቀስ በቀስ በራብ ከመሞት ይልቅ በጦርነት የሚሞቱት የተሻሉ ነበሩ።

10 የርኅሩኅ ሴቶች እጆች የገዛ ልጆቻቸውን ቀቀሉ፤ ከተማዋ በተደመሰሰች ጊዜ እነዚያ የተቀቀሉ ልጆች ለሰዎች ምግብ ሆኑ።

11 እግዚአብሔር ኀይለኛ ቊጣውን ገለጠ፤ የጽዮንን መሠረት የሚያጠፋ፥ የተቀጣጠለ እሳት የመሰለ መዓቱን አወረደ።

12 የምድር ነገሥታትም ሆኑ የዓለም ሕዝቦች በኢየሩሳሌም የቅጽር በሮች ጠላት ይገባል ብለው አላመኑም።

13 ይህም የሆነው በመካከልዋ የንጹሓንን ደም ባፈሰሱት በካህናትዋ በደልና በነቢያትዋ ኃጢአት ምክንያት ነው።

14 እነርሱ በደም የረከሱ ስለ ሆኑ ሰው ልብሳቸውን እንኳ ለመንካት አይደፍርም፤ እነርሱ ግን እንደ ዕውሮች በመንገድ ላይ ይንከራተታሉ።

15 ስለዚህም ሕዝቡ “ወዲያ ሂዱ! ስለ ረከሳችሁም አትንኩን!” እያሉ ይጮኹባቸዋል። ስለዚህ እነርሱ ስደተኞችና ተንከራታቾች ሆኑ ሕዝቦችም “ከእንግዲህ በመካከላችን አይቈዩም” አሉ።

16 እግዚአብሔር ራሱ የበተናቸው ስለ ሆነ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ እነርሱ አያስብም፤ ለካህናቱ ክብር አይሰጣቸውም፤ ሽማግሌዎችም ልዩ አስተያየት አይደረግላቸውም።

17 በከንቱ ረዳት በመጠበቅ ዐይናችን ደከመ ሊታደግ ከማይችል ሕዝብ በጒጒት ርዳታ ጠበቅን።

18 ጠላትም በየመንገዱ መዘዋወር እንዳንችል በዐይነ ቊራኛ ይጠባበቀን ነበር፤ ዘመናችን ቀርቦአል፤ ዘመናችን አልቆአል፤ ፍጻሜውም ደርሶአል።

19 አሳዳጆቻችን በሰማይ ከሚበርሩ ንስሮች የፈጠኑ ነበሩ፤ በተራሮች ላይ አሳደዱን፤ በበረሓም ሸመቁብን።

20 በሕዝቦች መካከል በእርሱ ጥላ ሥር እንኖራለን ብለን ያሰብነውን እግዚአብሔር የቀባውን የሕይወት እስትንፋሳችን አጠመዱብን።

21 እናንተ በዑፅ ምድር የምትኖሩ የኤዶም ሕዝብ ሆይ ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ! ይሁን እንጂ የእናንተም ጽዋ ተራውን ጠብቆ በመምጣት ላይ ነው፤ እናንተም ሰክራችሁ ትራቈታላችሁ።

22 የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ! የበደላችሁ ቅጣት አብቅቶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ በስደት እንድትኖሩ አያደርጋችሁም፤ ነገር ግን የኤዶም ሕዝብ ሆይ! የእናንተን በደል ይቀጣል፤ ኃጢአታችሁንም ያጋልጣል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos