መክብብ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለሁሉም ጊዜ አለው 1 በዚህ ዓለም ለሚፈጸም ለማናቸውም ነገር ሁሉ እግዚአብሔር የወሰነለት ዘመንና ጊዜ አለው፤ 2 ስለዚህም እግዚአብሔር በወሰነው መሠረት፥ ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀል ጊዜ አለው። 3 ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለመገንባት ጊዜ አለው፤ ለማፍረስም ጊዜ አለው። 4 ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ለሐዘን ጊዜ አለው፤ ለመጨፈርም ጊዜ አለው። 5 ድንጋይ ለመበተን ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤ ለማቀፍ ጊዜ አለው፤ ለመለያየትም ጊዜ አለው። 6 ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ የጠፋውን ላለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፤ ለመጣልም ጊዜ አለው። 7 ለመቅደድ ጊዜ አለው፤ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለንግግርም ጊዜ አለው። 8 ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሰላምም ጊዜ አለው። 9 ታዲያ፥ ሠራተኛ ከድካሙ የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው? 10 የሰው ልጆች እንዲደክሙበት እግዚአብሔር የሰጣቸውን የከባድ ሥራ ጭነት ተመለከትኩ። 11 እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነገር ጊዜ በመወሰን ሁሉን ነገር ውብ አድርጎ ሠርቶታል፤ ዘለዓለማዊነትንም በሰው ልቡና አሳድሮአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሁሉ እስከ መጨረሻ ያውቅ ዘንድ ለሰው የተሰጠው ዕውቀት ሙሉ አይደለም። 12 ስለዚህ ሰው በሕይወቱ ሳለ መልካም ነገር ከማድረግና ደስ ከሚለው በቀር ሌላ የተሻለ ነገር እንደሌለ ተረድቼአለሁ። 13 ሰው ጥሮ ግሮ ባገኘው የድካም ዋጋ በልቶና ጠጥቶ መደሰት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 14 እግዚአብሔር የሠራው ነገር ሁሉ ዘለዓለማዊነት እንዳለው ዐውቃለሁ፤ በእርሱ ላይ የሚጨመርበት ወይም ከእርሱ የሚቀነስ ነገር የለም፤ እግዚአብሔር ይህን ያደረገው ሰዎች እርሱን እንዲፈሩት ነው። 15 የሚሆነውና መሆን የሚችለው ነገር ሁሉ ያው ቀድሞ ተደርጎ የነበረው ነው፤ እግዚአብሔር ያንኑ ቀድሞ የፈጠረውን ነገር እንዲደጋገም ያደርጋል። በዓለም ስላለ የፍትሕ መጓደል 16 ደግሞም በዓለም ላይ በቅንነትና በፍትሕ ቦታ ዐመፅና ግፍ መብዛቱን አየሁ። 17 እኔም “ሁሉ ነገር የሚፈጸምበት ጊዜ ስላለው እግዚአብሔር በዐመፀኞችም ሆነ በቅኖች ላይ ይፈርዳል” ብዬ አሰብኩ። 18 እንደገናም “የሰው ልጆች ከእንስሶች ምንም የማይሻሉ መሆናቸውን እንዲረዱ፥ እግዚአብሔር ይፈትናቸዋል” ብዬ አሰብኩ። 19 በእርግጥም የሰው ልጆችና የእንስሶች ዕድል ፈንታቸው አንድ ዐይነት ነው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁለቱም የተፈጥሮ እስትንፋስ አንድ ዐይነት ነው፤ ታዲያ ሁለቱም ከንቱ ስለ ሆኑ ሰው ከእንስሳ አይሻልም። 20 ሰውም ሆነ እንስሳ ሁለቱም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ፤ ይኸውም ከዐፈር የተሠሩ በመሆናቸው ወደ ዐፈርነት ይመለሳሉ። 21 ታዲያ፥ የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣና የእንስሶች ነፍስ ደግሞ ወደ መሬት እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው? 22 የሰው ዕድል ፈንታ ይኸው ስለ ሆነ በሚሠራው ነገር ደስ ከሚለው በቀር ሌላ የሚያደርገው ምንም ነገር እንደሌለ አስተዋልኩ፤ ከሞተም በኋላ የሚሆነውን ነገር የሚያውቅ ማንም የለም። |