ዮሐንስ 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሱስ ከሞት መነሣት ( ማቴ. 28፥1-8 ፤ ማር. 16፥1-8 ፤ ሉቃ. 24፥1-12 ) 1 እሑድ ጠዋት በማለዳ፥ ገና ጎሕ ሳይቀድ፥ መግደላዊት ማርያም ወደ ኢየሱስ መቃብር ሄደች፤ እዚያም እንደ ደረሰች መቃብሩ ተዘግቶበት የነበረው ድንጋይ ከመቃብሩ በር ላይ ተነሥቶ አየች። 2 ስለዚህ እርስዋ ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ወደሚወደው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር እየሮጠች ሄደችና “ጌታን ከመቃብሩ አውጥተው ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩት አናውቅም” አለቻቸው። 3 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጡና ወደ መቃብሩ ሄዱ። 4 ሁለቱም አብረው ይሮጡ ነበር፤ ነገር ግን ሌላው ደቀ መዝሙር ከጴጥሮስ ይበልጥ ፈጥኖ ሮጠና ቀድሞ ወደ መቃብሩ ደረሰ። 5 ጐንበስ ብሎም ወደ መቃብሩ ቢመለከት የከፈኑ ጨርቅ እዚያ ተቀምጦ አየ፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ አልገባም። 6 ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣና ወደ መቃብሩ ውስጥ ገባ፤ እርሱም የከፈኑን ጨርቅ እዚያ ተቀምጦ አየ፤ 7 የኢየሱስ ራስ ተጠምጥሞ የነበረበት ጨርቅ ከከፈኑ ጨርቅ ጋር ሳይሆን ለብቻው በሌላ ስፍራ ተጠቅሎ እንደ ተቀመጠ አየ። 8 ቀጥሎም ያ ቀድሞ የደረሰው ደቀ መዝሙር ወደ መቃብሩ ውስጥ ገብቶ አየና አመነ። 9 “ከሞት መነሣት ይገባዋል” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ቃል ገና አልተገነዘቡም ነበር። 10 ከዚህ በኋላ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ተመልሰው ወደ ቤታቸው ሄዱ። የኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም መገለጥ ( ማቴ. 28፥9-10 ፤ ማር. 16፥9-11 ) 11 መግደላዊት ማርያም እያለቀሰች፥ ከመቃብሩ በስተውጭ ቆማ ነበር፤ እያለቀሰችም ጐንበስ ብላ ወደ መቃብሩ ውስጥ ተመለከተች። 12 የኢየሱስ አስከሬን በነበረበት ስፍራ ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አንዱ በራስጌ፥ አንዱ በግርጌ ተቀምጠው አየች። 13 እነርሱም ማርያምን፥ “አንቺ ሴት! ለምን ታለቅሻለሽ?” አሉአት። እርስዋም “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” አለች። 14 ይህንንም ብላ ወደ ኋላዋ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስ መሆኑን ግን አላወቀችም። 15 ኢየሱስ፥ “አንቺ ሴት ስለ ምን ታለቅሺአለሽ፤ ማንንስ ትፈልጊአለሽ?” አላት። እርስዋም አትክልተኛው መስሎአት፥ “ጌታ ሆይ! አንተ ወስደኸው እንደ ሆነ የት እንዳኖርከው እባክህ ንገረኝ፤ እኔ እወስደዋለሁ” አለችው። 16 ኢየሱስም “ማርያም!” አላት። እርስዋም ወደ እርሱ ዞር ብላ በዕብራይስጥ ቋንቋ “ረቡኒ!” አለችው፤ ትርጓሜውም “መምህር ሆይ!” ማለት ነው። 17 ኢየሱስ “ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሂጂና ‘እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፥ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ ብሎአል’ ብለሽ ንገሪያቸው” አላት። 18 ስለዚህ መግደላዊት ማርያም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሄዳ ጌታን እንዳየችና እርሱም ምን እንዳላት ነገረቻቸው። የኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ መገለጥ ( ማቴ. 28፥16-20 ፤ ማር. 16፥14-18 ፤ ሉቃ. 24፥36-49 ) 19 በዚያው በሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እሑድ ማታ ደቀ መዛሙርቱ የአይሁድን ባለሥልጣኖች በመፍራት፥ በራፎቹን ዘግተው፥ በቤት ውስጥ ተሰብስበው ነበር፤ በሮቹ ተዘግተው ሳለ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ተሰበሰቡበት ቤት ገባ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። 20 ይህንንም ብሎ እጆቹንና ጐኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 21 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ እንደገና “ሰላም ለእናንተ ይሁን! አብ እኔን እንደ ላከኝ እኔም እናንተን እልካችኋለሁ” አላቸው። 22 ይህን ብሎ እፍ አለባቸውና “መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ፤ 23 እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ብትሉ ይቅር ይባልላቸዋል፤ እናንተ የሰዎችን ኃጢአት ይቅር ባትሉ ግን፥ ይቅር አይባልላቸውም” አላቸው። ኢየሱስና ቶማስ 24 ኢየሱስ ወደ ደቀ መዛሙርቱ በመጣ ጊዜ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ፥ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም። 25 ስለዚህ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ቶማስን “ጌታን አየነው” አሉት። እርሱ ግን “በምስማር የተወጉትን እጆቹን ካላየሁና ጣቴን በምስማር በተወጋው ውስጥ ካላገባሁ፥ እጄንም በጐኑ ቊስል ካላገባሁ አላምንም” አላቸው። 26 ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንደገና በቤት ውስጥ ነበሩ፤ ቶማስም አብሮአቸው ነበር፤ በሮቹ ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። 27 ከዚህ በኋላ ቶማስን፥ “ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና በጐኔ ውስጥ አግባው፤ እመን እንጂ እምነተ ቢስ አትሁን” አለው። 28 ቶማስም “ጌታዬ! አምላኬም!” ሲል መለሰለት። 29 ኢየሱስም ቶማስን፥ “አንተስ ስለ አየኸኝ አመንክ፤ ሳያዩኝ የሚያምኑ ግን የተመሰገኑ ናቸው” አለው። የዚህ መጽሐፍ ዓላማ 30 ኢየሱስ በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ብዙ ተአምር በደቀ መዛሙርቱ ፊት አድርጓል፤ 31 ነገር ግን ኢየሱስ መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንድታምኑና፥ አምናችሁም በእርሱ ስም የዘለዓለም ሕይወትን እንድታገኙ ይህ ተጽፎአል። |