Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


1 ጢሞቴዎስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የቤተ ክርስቲያን ጸሎት

1 እግዚአብሔርን በማምለክና ክብር በተመላ ሕይወት ልመና፥ ጸሎት፥ ምልጃና ምስጋና ለሰዎች ሁሉ እንዲደረግ እመክራለሁ።

2 እግዚአብሔርን በመፍራትና በመልካም ጠባይ እየተመራን በሰላምና በጸጥታ እንድንኖር በተለይ ለነገሥታትና በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ላሉ ሁሉ ጸልዩ።

3 ይህም በአዳኛችን በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው።

4 የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን እንዲያውቁ ነው።

5 እግዚአብሔር አንድ ነው፤ በመካከል ሆኖ እግዚአብሔርንና ሰውን የሚያስታርቀውም አንድ ነው፤ እርሱም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

6 ሰዎችን ሁሉ ከኃጢአት ለመዋጀት ራሱን ቤዛ አድርጎ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይህም ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ የሚያስረዳ ምስክርነት ነው።

7 እኔም እምነትንና እውነትን ለማብሠር ሐዋርያና አስተማሪ ሆኜ ወደ አሕዛብ የተላክሁት በዚህ ምክንያት ነው፤ ይህንንም ስል እውነት እናገራለሁ እንጂ አልዋሽም።

8 እንግዲህ በየስፍራው ያሉ ወንዶች ቊጣንና ጥልን አስወግደው የተቀደሱ እጆቻቸውን ወደ ላይ በማንሣት እንዲጸልዩ እፈልጋለሁ።

9 እንዲሁም ሴቶች ጠጒርን በማሳመር ወይም በወርቅ ወይም በዕንቊ ወይም ውድ በሆነ ልብስ በማጌጥ ሳይሆን በማፈርና በትሕትና ተገቢ የሆነ የጨዋ ልብስ ይልበሱ።

10 እግዚአብሔርን እናመልካለን የሚሉ ሴቶች ማድረግ በሚገባቸው ዐይነት በመልካም ሥራ ያጊጡ።

11 ሴት በጸጥታና በመታዘዝ ትማር፤

12 ሴት ወንድን እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም፤ እርስዋ ዝም ማለት ይገባታል።

13 በመጀመሪያ የተፈጠረ አዳም ነው፤ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች።

14 ደግሞም የተታለለችውና የእግዚአብሔርን ሕግ ያፈረሰችው ሴት ናት እንጂ የተታለለው አዳም አይደለም።

15 ነገር ግን ሴት በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ብትጽናና ራስን በመቈጣጠር ብትኖር ልጅ በመውለድ ትድናለች።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos