Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ቆሬ፥ ዳታንና አቤሮን የፈጸሙት ዐመፅ

1 ከሌዊ ነገድ የሆነው የቀዓት ጐሣ የይስዓር ልጅ ቆሬ፥ ከሮቤል ነገድ የሆኑት የኤልያብ ልጆች ዳታንና አቤሮን፥ የፋሌትም ልጅ ኦን ዐመፁ፤

2 ከእነርሱም ጋር በእስራኤላውያን ዘንድ ዝናቸው የታወቀና ለሕዝብ መሪነት የተመረጡ ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎችን ወስደው በሙሴ ላይ ተነሡ፤

3 እነርሱም በሙሴና በአሮን ፊት ተሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ “እናንተ ከልክ አልፋችኋል! የዚህ ጉባኤ አባላት የሆኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለዩ ናቸው፤ እግዚአብሔርም ከእኛ ሁሉ ጋር ነው፤ ታዲያ በእግዚአብሔር ጉባኤ ላይ ራሳችሁን ከፍ ከፍ የምታደርጉት ስለምንድን ነው?”

4 ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ በግንባሩ ወድቆ ጸለየ፤

5 ቆሬንና ተከታዮቹን እንዲህ አላቸው፦ “ነገ ጠዋት እግዚአብሔር ለእርሱ የተለየ ማን እንደ ሆነ ለይቶ ያሳየናል፤ ይኸውም የእርሱ የሆነውንና የመረጠውን በመሠዊያው ላይ ያገለግለው ዘንድ ወደ እርሱ እንዲቀርብ ይፈቅድለታል።

6 ነገ ጠዋት አንተና ተባባሪዎችህ ሁሉ ጥናዎችን ይዛችሁ ኑ!

7 በእነርሱም ላይ የከሰል ፍምና ዕጣን አድርጋችሁ ወደ መሠዊያው አቅርቡአቸው፤ ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ማንኛችንን መርጦ ለራሱ እንደ ለየ እናያለን፤ ከልክ ያለፋችሁትስ እናንተ ሌዋውያኑ ናችሁ።”

8 ሙሴ ከቆሬ ጋር መነጋገሩን እንዲህ ሲል ቀጠለ፦ “እናንተ ሌዋውያን አድምጡ!

9 ወደ እርሱ ቀርባችሁ በማደሪያው ድንኳን አገልግሎታችሁን እንድትፈጽሙና በፊታቸውም ቆማችሁ የእስራኤልን ጉባኤ እንድታገለግሉ የእስራኤል አምላክ ከሌላው የእስራኤል ማኅበር መካከል መርጦ እናንተ የተለያችሁ እንድትሆኑ ማድረጉን እንደ ቀላል ነገር ታዩታላችሁን?

10 እርሱ እናንተና ሌሎቹም ሌዋውያን ይህ ክብር እንዲኖራችሁ አድርጎአል፤ አሁን ደግሞ የካህናቱን ቦታ ለመያዝ ፈልጋችኋል፤

11 ስለዚህ አንተና ተባባሪዎችህ የተሰበሰባችሁት በእግዚአብሔር ላይ ነው፤ በአሮን ላይ የምታጒረመርሙት እርሱ ማን ነው?”

12 ከዚህ በኋላ ሙሴ የኤልያብ ልጆች የሆኑትን ዳታንንና አቤሮንን ልኮ አስጠራ፤ እነርሱ ግን “አንመጣም!” አሉ።

13 “በምድረ በዳ እንድንሞት በማርና በወተት ከበለጸገችው ምድር ያስወጣኸን አንሶ አሁን ደግሞ በእኛ ላይ አለቃ ልትሆን ትፈልጋለህን?

14 ለም ወደሆነችው ምድር እንዳላመጣኸን ወይም የእርሻና የወይን ተክል ቦታ እንዳላወረስከን የተረጋገጠ ነው፤ አሁን ደግሞ ልታታልለን ትፈልጋለህ፤ እንግዲህስ ወደ አንተ አንመጣም!”

15 ሙሴም እጅግ ተቈጥቶ እግዚአብሔርን እንዲህ አለ፦ “እነዚህ ሰዎች የሚያቀርቡልህን መባ አትቀበል፤ እኔ ከእነርሱ አንዱን እንኳ አልበደልኩም፤ ሌላው ቀርቶ ከአህዮቻቸው አንዱን እንኳ አልወሰድኩም።”

16 ሙሴ ቆሬን እንዲህ አለው፦ “ነገ አንተና ሁለት መቶ ኀምሳ ተባባሪዎችህ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን እንድትመጡ፤ አሮንም እዚያው ይገኛል።

17 እያንዳንዳችሁ ጥናችሁን ይዛችሁ ኑ፤ በውስጡም ዕጣን ጨምሩበት፤ ከሁለት መቶ ኀምሳ ጥናዎች ጋር ወደ እግዚአብሔር ፊት ዕጣናችሁን ታቀርባላችሁ፤ አንተና አሮንም ዕጣናችሁን ታቀርባላችሁ።”

18 ስለዚህም እያንዳንዳቸው ጥናቸውን ይዘው የእሳት ፍምና ዕጣን በመጨመር በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሙሴና ከአሮን ጋር ቆሙ፤

19 ከዚያም በኋላ ቆሬ መላውን ማኅበር በአንድነት ሰበሰበ፤ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ መጥተው በሙሴና በአሮን ፊት ለፊት ቆሙ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለመላው ማኅበር በድንገት ታየ።

20 እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

21 “ከእነዚህ ሕዝብ ራቅ ብላችሁ ቁሙ፤ እኔም እነርሱን በአንድ ጊዜ እደመስሳቸዋለሁ።”

22 ሙሴና አሮን በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው እንዲህ አሉ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነህ፤ አንድ ሰው ኃጢአት ቢሠራ በመላው ማኅበር ላይ ትቈጣለህን?”

23-24 እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “ከቆሬ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች እንዲርቁ ለሕዝቡ ንገር” አለው።

25 ከዚህ በኋላ ሙሴ የእስራኤልን መሪዎች አስከትሎ ወደ ዳታንና አቤሮን ሄደ፤

26 ሕዝቡንም እንዲህ አለ፦ “ከእነዚህ ዐመፀኞች ሰዎች ድንኳኖች ርቃችሁ ቁሙ፤ የእነርሱ ንብረት የሆነውን ማናቸውንም ዕቃ አትንኩ፤ አለበለዚያ በእነርሱ ኃጢአት ምክንያት ሁላችሁም ከእነርሱ ጋር ተጠራርጋችሁ ትጠፋላችሁ።”

27 ስለዚህ ሕዝቡ ከቆሬ፥ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች ፈቀቅ አሉ። ዳታንና አቤሮንም ወጥተው ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በድንኳናቸው ደጃፍ ቆመው ነበር።

28 በዚያን ጊዜ ሙሴ ለሕዝቡ እንዲህ አለ፦ “ይህን ሁሉ ሥራ እንዳከናውን እግዚአብሔር እኔን የላከኝ መሆኑን የምታውቁትና እኔ ይህን ሁሉ ሥራ የማከናውነው በራሴ ፈቃድ እንዳልሆነ የምትገነዘቡት በዚህ ነው፤

29 እነዚህ ሰዎች ከእግዚአብሔር ቅጣት ሳይደርስባቸው እንደማንኛውም ሰው ከሞቱ፥ እኔን እግዚአብሔር አላከኝም፤

30 ነገር ግን እግዚአብሔር ተሰምቶ የማይታወቅ አዲስ ነገር በመፍጠር በሕይወታቸው ሳሉ ወደ ሙታን ዓለም ይወርዱ ዘንድ ምድር ተከፍታ እነርሱንና የእነርሱ የሆነውን ሁሉ ብትውጥ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን የተቃወሙ መሆናቸውን ታውቃላችሁ።”

31 ሙሴ ይህን ተናግሮ እንዳበቃ፥ ዳታንና አቤሮን የቆሙበት ምድር ተከፍታ

32 እነርሱንና ቤተሰቦቻቸውን፥ የቆሬን ተከታዮችና ያላቸውን ንብረት ሁሉ ዋጠች።

33 ስለዚህ በሕይወት ሳሉ ከነንብረታቸው ወደ ሙታን ዓለም ወረዱ፤ ምድርም በላያቸው ተከድና ጠፉ።

34 በዚያ የነበሩት የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የእነዚያን ሰዎች ጩኸት በሰሙ ጊዜ ሸሹ፤ “ምድር እኛንም ልትውጠን ስለምትችል እንሩጥ!” እያሉም ጮኹ።

35 ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር እሳት ልኮ ዕጣን ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ ኀምሳ ሰዎች አቃጠለ።

36 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

37 “የአሮን ልጅ አልዓዛር ከነሐስ የተሠሩትን ጥናዎች ከተቃጠሉት ሰዎች ዘንድ እንዲወስድና ጥናዎቹ የተቀደሱ ስለ ሆኑ በውስጣቸው ያለውን ፍም ወደ ሌላ ስፍራ እንዲያፈስ ንገረው፤

38 ጥናዎቹም የተቀደሱት ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ በቀረቡ ጊዜ ነው፤ ስለዚህ በኃጢአታቸው የተገደሉትን የእነዚህን ሰዎች ጥናዎች ውሰድና በመቀጥቀጥ እንዲሳሱ አድርግ፤ ለመሠዊያውም መክደኛ እንዲሆኑ አድርገህ ሥራቸው፤ ለእስራኤል ሕዝብ የመቀጣጫ ማስጠንቀቂያ ይሆናል።”

39 ስለዚህ አልዓዛር ጥናዎቹን ወስዶ ለመሠዊያው ክዳን ይሆኑ ዘንድ በስሱ ቀጠቀጣቸው።

40 ይህም ሁኔታ የአሮን ዘር ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ዕጣን ያጥን ዘንድ ወደ መሠዊያው መቅረብ እንደማይገባው ለእስራኤላውያን ሁሉ ማስጠንቀቂያ ይሆናል፤ ይህ ካልሆነ ግን እንዲህ የሚያደርግ ሰው ሁሉ እንደ ቆሬና እንደ ተከታዮቹ ይጠፋል፤ ይህም ሁሉ የተፈጸመው እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ነበር።


አሮን ሕዝቡን ማዳኑ

41 በማግስቱ መላው የእስራኤል ማኅበር “የእግዚአብሔር ወገኖች የሆኑትን ሕዝብ ገድላችኋል” በማለት በሙሴና በአሮን ላይ አጒረመረሙ።

42 ሙሴንና አሮንን ለመቃወም ሁሉም በአንድነት ከተሰበሰቡ በኋላ ወደ መገናኛው ድንኳን ዞር ብለው ሲመለከቱ ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፍኖት የእግዚአብሔር ክብር ተገለጠ።

43 ሙሴና አሮንም መጥተው በመገናኛው በድንኳን ፊት ለፊት ቆሙ።

44 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦

45 “ከእነዚህ ሰዎች ርቃችሁ ቁሙ፤ እኔ እነርሱን በአንድ ጊዜ እደመስሳቸዋለሁ!” ሁለቱም በግንባራቸው ወደ መሬት ተደፉ፤

46 ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፦ “የአንተን ጥና ወስደህ ከመሠዊያው የእሳት ፍም ጨምርበት፤ በፍሙም ላይ ዕጣን አድርግበት፤ ከዚያም ወደ ሕዝቡ በፍጥነት በመሄድ አስተስርይላቸው፤ ፍጠን! እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቊጣ ከመገለጡ የተነሣ በሕዝቡ መካከል መቅሠፍት ጀምሮአል።”

47 አሮንም በመታዘዝ ጥናውን ይዞ ወደ ተሰበሰበው ሕዝብ መካከል ፈጥኖ ሄደ፤ መቅሠፍቱ እንደ ጀመረ በተመለከተ ጊዜ ዕጣኑን በፍሙ ላይ አድርጎ ለሕዝቡ አስተሰረየላቸው፤

48 በዚህም መቅሠፍቱ እንዲቆም አደረገ፤ አሮንም በሞቱትና በሕይወት ባሉት መካከል ቆሞ ነበር።

49 በዚያን ጊዜ የሞቱት ሰዎች ቊጥር ከቆሬ ጋር ዐምፀው ያለቁትን ሳይጨምር ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበር፤

50 ቸነፈሩም በቆመ ጊዜ አሮን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደነበረው ወደ ሙሴ ተመለሰ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos