Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ቆሮንቶስ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ይህ እንደ ድንኳን ጊዜያዊ የሆነው ምድራዊው ሥጋችን ሲፈርስ በሰው እጅ ሳይሆን በእግዚአብሔር የታነጸ ዘለዓለማዊ መኖሪያ በሰማይ እንዳለን እናውቃለን።

2 ሰማያዊ አካልን ለመልበስ በመናፈቅ እንጥራለን።

3 እርሱንም ስንለብስ ራቁታችንን ሆነን አንገኝም።

4 በዚህ እንደ ምድራዊ ድንኳን በሆነው ሥጋችን ውስጥ ስንኖር ከብደን እንቃትታለን፤ የምንቃትተውም ሞት በሕይወት እንዲለወጥ ሰማያዊውን አካል በበለጠ እንድንለብስ ነው እንጂ ከዚህ ከምድራዊ ሥጋችን ለመለየት በመፈለግ አይደለም።

5 ለዚህም ነገር ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ ከዚያም በላይ ለሚሰጠን ነገር ሁሉ ዋስትና እንዲሆን መንፈሱን የሰጠንም እርሱ ነው።

6 በምድራዊ ሰውነታችን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ከጌታ የራቅን መሆናችንን ብናውቅም እንኳ ሁልጊዜ በእርሱ እንተማመናለን።

7 እኛ የምንኖረውም ጌታን በማመን እንጂ እርሱን በማየት አይደለም።

8 ከዚህ እንደ መኖሪያችን ከሆነው ሥጋችን ተለይተን ከጌታ ጋር ለመሆን እንመኛለን፤ ስለዚህ በመተማመን እንኖራለን።

9 ከዚህ ከሥጋችን ጋር ብንሆንም ወይም ከእርሱ ብንለይም ዓላማችን ጌታን ማስደሰት ነው።

10 እያንዳንዱ በምድራዊ ሕይወቱ ላደረገው ክፉም ሆነ ደግ ነገር እንደየሥራው ዋጋውን ለመቀበል ሁላችንም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት መቅረብ አለብን።

11 ጌታን መፍራት ምን መሆኑን ስለምናውቅ ሰዎችን እናስረዳለን፤ እኛ ምን መሆናችንንም እግዚአብሔር ያውቃል፤ እናንተም በልቡናችሁ ምን መሆናችንን እንደምታውቁ ተስፋ አደርጋለሁ።

12 በልብ ባለው ሳይሆን በሚታየው ለሚመኩ መልስ ለመስጠት እንድትችሉ በእኛ ትመኩ ዘንድ ዕድል እንሰጣችኋለን እንጂ እንደገና እኛ ለእናንተ ራሳችንን አናመሰግንም።

13 እብዶች ብንሆን ለእግዚአብሔር ስንል ነው፤ ባለ አእምሮዎች ብንሆንም ለእናንተ ስንል ነው።

14 አንድ ጊዜ ክርስቶስ ለሁሉም መሞቱንና ሁሉም የእርሱ ሞት ተካፋዮች መሆናቸውን ስለ ተረዳን የክርስቶስ ፍቅር ለሥራ ያስገድደናል።

15 በሕይወት ያሉት ሁሉ ለእነርሱ ለሞተውና ከሞትም ለተነሣው እንዲኖሩ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ ለራሳቸው ሲሉ እንዳይኖሩ ክርስቶስ ለሁሉም ሞተ።

16 ከእንግዲህ ወዲህ እኛ ማንንም ሰው በሥጋዊ አመለካከት አንመለከትም፤ ከዚህ በፊት ክርስቶስንም የተመለከትነው እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋዊ አመለካከት ከሆነ ለወደፊቱ ግን ይህን አናደርግም።

17 ስለዚህ ማንም ሰው የክርስቶስ ወገን ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ፍጥረት አልፎአል፤ በእርሱም ስፍራ አዲስ ፍጥረት ተተክቶአል።

18 ይህም ሁሉ የሆነው እኛን ከራሱ ጋር በክርስቶስ አማካይነት ባስታረቀንና የማስታረቅንም አገልግሎት በሰጠን በእግዚአብሔር ነው።

19 ይህም እግዚአብሔር በክርስቶስ የዓለምን ሰዎች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ ማለት ነው፤ በደላቸውንም አልቈጠረባቸውም፤ ለእኛም ሰውን ከጌታ ጋር የምናስታርቅበትን ቃል ሰጠን።

20 እግዚአብሔር ሰዎችን በእኛ አማካይነት ስለሚጠራ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ ስለዚህ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ!” ብለን በክርስቶስ ስም እንለምናችኋለን።

21 እኛ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተካፋዮች እንድንሆን እግዚአብሔር ኃጢአት የሌለበትን ክርስቶስን የእኛን ኃጢአት እንዲሸከም አደረገው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos