ምሳሌ 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ወይን ጠጅ ፌዘኛ፥ ጠንካራ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋሉ፤ በእነርሱ ሱስ የተጠመደ ጥበበኛ ሊሆን አይችልም። 2 የንጉሥ ቊጣ እንደሚያገሣው አንበሳ ያስፈራል፤ የእርሱንም ቊጣ የሚያነሣሣ በራሱ ላይ የሞት ፍርድ እንደ ፈረደ ይቈጠራል። 3 ማንኛውም ሞኝ ተቈጥቶ ጠብ ማነሣሣት ይችላል፤ ሰውን የሚያስከብረው ግን ከክርክር መራቅ ነው። 4 መሬቱን በወቅቱ የማያርስ ሰነፍ ገበሬ በመከር ጊዜ የሚሰበስበው ምርት አይኖረውም። 5 የሰው ሐሳብ በጥልቅ ጒድጓድ ውስጥ እንዳለ ውሃ ነው፤ ይሁን እንጂ ማስተዋል ያለው ሰው ይቀዳዋል። 6 ሰው ሁሉ ስለ ራሱ ደግነት ያወራል፤ ነገር ግን በእውነት ታማኝ የሆነውን ሰው ማን ሊያገኝ ይችላል! 7 ጻድቅ ሰው በቅንነት ይኖራል፤ የእርሱ ልጆችም የተባረኩ ናቸው። 8 በፍርድ ዙፋን ላይ የተቀመጠ ንጉሥ ክፉ የሆነውን ነገር ሁሉ አበጥሮ የሚያውቅ ዐይን አለው። 9 “ኅሊናዬ ንጹሕ ነው፤ ኃጢአትም የለብኝም” ማለት የሚችል ሰው ይኖራልን? 10 እግዚአብሔር በሐሰተኛ ሚዛንና ትክክል ባልሆነ መስፈሪያ የሚጠቀሙ ሰዎችን ይጠላል። 11 ሕፃን እንኳ ደግና ቅን መሆኑ በሚያደርገው ነገር ይታወቃል። 12 የሚሰማ ጆሮንና የሚያይ ዐይንን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው። 13 ጊዜህን በእንቅልፍ ብትጨርስ ትደኸያለህ፤ ተግተህ ብትሠራ ግን በቂ ምግብ ይኖርሃል። 14 ገዢ ዘወትር መጥፎ ነው እያለ ዕቃን ያራክሳል፤ ገዝቶ ከሄደ በኋላ ግን “በርካሽ ገዛሁ” እያለ ይመካል። 15 ዕውቀት የተሞላበት ንግግር፥ ከወርቅና ከከበረ ዕንቊ ይበልጥ የተወደደ ነው። 16 ማንም ሰው ለእንግዳ ሰው ከተዋሰ፥ ልብሱን ውሰድ፤ ለማይታወቀው ሰው መያዣ እንዲሆን አንተ ዘንድ አስቀምጠው። 17 በማጭበርበር የምታገኘው ነገር እንደ ጣፋጭ ምግብ ሊያስደስትህ ይችላል፤ ነገር ግን ውሎ ሲያድር በአፍ ውስጥ እንደ አሸዋ ይሆናል። 18 መልካም ምክርን ብትቀበል ሁሉ ነገር ይሳካልሃል፤ ስለዚህ መልካም ምክር ሳትቀበል ወደ ጦርነት አትሂድ። 19 ሐሜተኛ ሰው ምሥጢር አይደብቅም፤ ስለዚህ በከንቱ ከሚለፈልፉ ሰዎች ራቅ። 20 አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ሕይወቱ በድቅድቅ ጨለማ ጊዜ እንደሚጠፋ መብራት ይሆናል። 21 በመጀመሪያ ያለ ድካም በቀላሉ የሚገኝ ሀብት በመጨረሻ አይባረክም። 22 ክፉ ያደረገብህን ሰው አንተም መልሰህ ክፉ አታድርግበት፤ በእግዚአብሔር ታመን፤ እርሱም ይታደግሃል። 23 እግዚአብሔር ያልተስተካከለ መስፈሪያና ሐሰተኛ ሚዛን ይጸየፋል። 24 እግዚአብሔር የምንራመድበትን መንገድ ወስኖአል፤ ታዲያ፥ ሰው ሕይወቱ ወዴት አቅጣጫ እንደሚያመራ እንዴት ሊያውቅ ይችላል? 25 በኋላ እንዳትጸጸት ለእግዚአብሔር ከመሳልህ በፊት ተጠንቅቀህ አስብ። 26 ብልኅ ንጉሥ ዐመፀኞችን ለይቶ ያውቃቸዋል፤ ያለ ምሕረትም ይቀጣቸዋል። 27 የሰው መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ስለ ሆነ የሰውን ውስጣዊ ሰውነት ሁሉ ይመረምራል። 28 ቸርነትና ታማኝነት ንጉሥን ይጠብቁታል፤ መንግሥቱም በእውነተኛነት ላይ ጸንቶ ይኖራል። 29 የወጣቶች መመኪያ ብርታታቸው ነው፤ የሽማግሌዎችም መከበሪያ ሽበታቸው ነው። 30 የሚያቈስል ቅጣት ክፉ ነገርን ያስወግዳል፤ ግርፋትም የሰውን ውስጣዊ ሁኔታ ያነጻል። |