ዘኍል 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየጸሎፍሐድ ሴቶች ልጆች ጥያቄ 1 የሔፌር፥ የገለዓድ፥ የማኪር፥ የምናሴ፥ የዮሴፍ ልጅ የሆነው ጸሎፍሐድ፥ ማሕላ፥ ኖዓ፥ ሖግላ፥ ሚልካ እና ቲርጻ ተብለው የሚጠሩ ሴቶች ልጆች ነበሩት። 2 እነርሱም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሄደው መላው ማኅበርና የሕዝቡ መሪዎች ባሉበት በሙሴና በአልዓዛር ፊት ቆመው እንዲህ አሉ፤ 3 “አባታችን አንድ እንኳ ወንድ ልጅ ሳይወልድ በምድረ በዳ ሞተ፤ እርሱ በእግዚአብሔር ላይ ካመፁት ከቆሬ ተከታዮች ጋር ተባባሪ አልነበረም፤ የሞተውም በራሱ ኃጢአት ምክንያት ነው፤ 4 ታዲያ፥ ወንድ ልጅ ባለመውለዱ ብቻ የአባታችን ስም ከእስራኤል ተፍቆ መጥፋት ይገባዋልን? ስለዚህ በአባታችን ዘመዶች መካከል ለእኛ የሚገባንን የርስት ድርሻ ስጡን።” 5 ሙሴም የእነርሱን አቤቱታ ወደ እግዚአብሔር አቀረበ፤ 6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ 7 “የጸሎፍሐድ ሴቶች ልጆች የጠየቁት ትክክል ነገር ነው፤ ስለዚህ በአባታቸው ዘመዶች መካከል ርስት ስጣቸው፤ የአባታቸው ድርሻ ወደ እነርሱ ይተላለፍ፤ 8 ወንድ ልጅ ሳይወልድ የሚሞት ሰው ቢኖር ሴት ልጁ ንብረቱን መውረስ እንደሚገባት ለእስራኤል ሕዝብ አስታውቅ። 9 ሴት ልጅም ከሌለው ወንድሞቹ ንብረቱን ይውረሱ፤ 10 ወንድሞችም ከሌሉት የአባቱ ወንድሞች ይውረሱ፤ 11 ወንድሞችም ሆኑ አጐቶች ከሌሉት የቅርብ ዘመዱ የሆነ ሰው ንብረቱን ወርሶ ሊጠቀምበት ይችላል፤ እኔ እግዚአብሔር ባዘዝኩህ መሠረት የእስራኤል ሕዝብ ይህን ሕግና ሥርዓት ቋሚ መመሪያ አድርገው ይጠብቁት።” ኢያሱ በሙሴ ምትክ መመረጡ ( ዘዳ. 31፥1-8 ) 12 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ዐባሪም ተራራ ወጥተህ ለእስራኤላውያን ልሰጣቸው ያቀድኩትን ምድር ሁሉ እይ፤ 13 እርሱንም ካየህ በኋላ ወንድምህ አሮን እንደ ሞተ አንተም ትሞታለህ፤ 14 ሁለታችሁም በጺን ምድረ በዳ በትእዛዜ ላይ ዐምፃችሁ ነበር፤ መላው ማኅበር በመሪባ ውሃ ዘንድ ሳሉ በእኔ ላይ በዐመፁ ጊዜ የተቀደሰውን ኀይሌን በእነርሱ ፊት መግለጥ እምቢ ብላችኋል፤” (መሪባ በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ የሚገኝ ምንጭ ነው።) 15 ሙሴም ወደ ጌታ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ 16-17 “ለሰው ሁሉ ሕይወትን የምትሰጥ፥ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፥ ሕዝብህ እረኛ እንደሌለው የበግ መንጋ እንዳይሆን፥ ሕዝብህን የሚመራ አንድ ሰው ምረጥ።” 18 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በመንፈስ ጠንካራ የሆነውን የነዌን ልጅ ኢያሱን ውሰድና እጆችህን በራሱ ላይ ጫን፤ 19 በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበር ፊት እንዲቆም አድርገው፤ በእነርሱም ሁሉ ፊት የአንተ ተተኪ መሆኑን አስታውቅ። 20 መላው የእስራኤል ማኅበር እርሱን ይታዘዙት ዘንድ የሥልጣንህ ተካፋይ አድርገው። 21 ካህኑ አልዓዛር በኡሪም አማካይነት ፈቃዴን የሚያውቅ ስለ ሆነ ኢያሱ በአልዓዛር ይደገፋል፤ በዚህም ዐይነት አልዓዛር ኢያሱንና መላውን የእስራኤል ማኅበር በተግባር አፈጻጸማቸው ሁሉ ይመራቸዋል።” 22 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በመላው ማኅበር ፊት እንዲቆም አደረገው፤ 23 እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሙሴ እጆቹን በኢያሱ ራስ ላይ ጭኖ ከዚያ በኋላ የእርሱ ተተኪ መሆኑን በግልጥ አስታወቀ። |