ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ሲራክ 43 - መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ)ፀሐይ 1 የተራሮች መኩሪያ፥ የጠራች የሰማይ ድባብ፥ የከዋክብት ውበት፥ ሞገስ ያላትም ትዕይንት ናት። 2 ፀሐይ ብቅ ስትል፥ ጮራዋንም ስትፈነጥቅ፥ የልዑል እግዚአብሔር ሥራ ምንኛ ድንቅ ነው! በማለት ታበስራለች። 3 ቀትር ላይ መሬትን ታደርቃለች፤ ሙቀቷንስ የሚቋቋም ማነው? 4 ሙቀትንም ለማግኘት ወናፍን መንፋት አለብን፤ ፀሐይ ግን ተራሮቹን ሦስት እጥፍ ጊዜ ታነዳቸዋለች፤ እስትንፋሷ የእሳት ነበልባል፥ ጮራዋም አንጸባራቂና ዓይንን የሚያጥበረብር ነው። 5 እርሷን የፈጠረ መንገዷንም በቃሉ የሚያፈጥን፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው። ጨረቃ 6 ጨረቃ ቀጠሮ አክባሪ ናት፤ ጊዜያትንም ለዘለዓለም ታመለክታለች። 7 በዓላትን የምታበስር፥ ከሞላች በኋላ የምትሟሟ አንጸባራቂ አካል ጨረቃ ናት። 8 ወር ስሙን ከእርሷ ወረሰ፤ ወቅቷንም ጠብቃ ድንቅ መለዋወጥን ታሳያለች፤ በደመና ያሉ አእላፋት ዓርማ፤ በሰማያት ቅስትም ላይ ሆና የምታበራ ናት። ለከዋክብት 9 የከዋክብት ግርማ፥ የሰማይ ውበት፥ የልዑል እግዚአብሔርም አንጸባራቂ ጌጥ ነው። 10 በቅዱስ አምላክ ቃል፥ በትእዛዙ ይጸናሉ፤ በቃፊርነታቸውም ፈጽመው አይደክሙም። ቀስተ ደመና 11 እጅግ ማራኪውን የቀስተ ደመናን ውበት ተመልከት፤ ፈጣሪውንም አመስግን። 12 በልዑል እግዚአብሔር እጅ በሰማይ ላይ የተነደፈ አንጸባራቂ ቀስት ነው። የተፈጥሮ ውበት 13 በትእዛዙ በረዶ ይወርደል፤ መብረቁንም እንዲወነጨፍ ያደርጋል። 14 ግምጃ ቤቱም ሲከፈት፥ ደመናት እንደ ወፎች ይበራሉ። 15 በታላቅ ኃይሉ ደመናትን ያጠጥራል፤ ፈረካክሶም በረዶ ያደርጋቸዋል። ነጐድጓዱም በተሰማ ጊዜ ምድር ታምጣለች። 16 እርሱን ባዩ ጊዜ ተራሮች ይንቀጠቀጣሉ፤ በትእዛዙም የደቡብ ነፍስ ይነፍሳል። 17 የሰሜኑ ማዕበልና ዓውሎ ነፋስም እንዲሁ ናቸው። 18 ለማረፍ እንደሚዘጋጅ ወፎች፥ እንዲሁ በረዶውን ያርከፈክፋል፥ እንደ አንበጣ መንጋም ያወርደዋል፤ ንጣቱ የዐይን እይታን ይማርካል፥ አወራረዱም አእምሮን ያስደምማል። 19 በመሬት ላይ እንደ ጨው ሁሉ፥ የነጣ ውርጭ ያፈሳል፤ እርሱም በቀዘቀዘ ጊዜ እንደ እሾህ ይቆማል። 20 ቀዝቃዛ ነፋስ ከሰሜን ይነፍሳል፤ ውሃም በረዶ ይዝላል። የረጋውንም ውሃ እንደ ጋሻ ይሸፈነዋል። 21 ነፋሱ ተራሮችን ይውጣል፤ በረሃውንም ያነዳል፤ ተክሎችንም እንደ እሳት ይፈጃል። 22 ደመናዎች ግን ፈጣን ፈውስን ያመጣሉ፤ ደስታን ይሰጣል። 23 ጥልቁን ጉድጓድ በጥበብ ገራው፤ ደሴቶችንም ተከለበት። 24 በባሕር የሚጓዙ አስፈሪነቱን ይናገራሉ፤ ትረካዎቻቸውም ጆሮዎቻችንን በአድናቆት ይሞላሉ፤ 25 ያልተለመደና አስደናቂ ሥራዎች፥ ታላላቅ ፍጥረታትና እንስሳት በሙሉ በዚያም ይገኛሉና። 26 እግዚአብሔር ይመስገን መልእክተኛው ከጠረፍ ይደርሳል፤ በቃሉም መሠረት ሁሉም ይፈጸማል። 27 ከዚህም በበለጠ ማየት ይቻላል፤ ይሁን እንጂ በቂ አይሆንም፤ እንዲያው ባጭሩ፥ እርሱ ሁሉንም ነው። 28 የእርሱን ክብር ለመግለጽ በቂ ኃይል የምናገኘው ከየት ነው? እርሱ ከሥራዎቹ ሁሉ የበለጠ ታላቅ፥ 29 በጣም አስደንጋጭ እጅግ ግዙፍ፥ ኃይሉም አስደናቂ ነውና። 30 በምስጋናችሁ ጌታን አወድሱት፤ የምትችሉትንም ያህል ከፍ አድርጉት፤ እርሱ ግን ከዚያም የመጠቀ ነው። በምስጋና ወቅት ኃይላችሁን ሁሉ ተጠቀሙ፤ ሰውነታችሁ አይዛል፤ ከፍጻሜው ግን ከቶውንም አትደርሱም። 31 እርሱን ለመግለጽ ከቶ ያየው ይኖራልን? የሚገባውንስ ያህል ሊያከብረው የሚችለው ይኖራልን? 32 ከሥራዎቹም ያየነው ጥቂቶቹን ነው፤ ከነኚህም የላቀ በርካታ ምሥጢራት አልቀረቡም። 33 ሁሉን የፈጠረ ጌታ ነውና፤ ለደጋጐችም ጥበብን የሰጠ እርሱ ነውና። |