እግዚአብሔር አባታችን ዘወትር እንድንጸልይ ነግሮናል። ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት መንገድ ነው። የምናምነው ሰው የመገናኛ መስመራችን ጸሎት ነው። እያንዳንዱን ልመናችንን ወደ ፈጣሪያችን እግር የምናደርስበት በጸሎት ነው። በሕይወታችን ውስጥ ምንም ነገር በማይሳካልን ጊዜ፣ ሸክም ሲከብደን፣ ሀዘን ሲሰማን የምንሄድበት ጸሎት ነው።
እግዚአብሔር ፍላጎታችንንና ድምፃችንን የሚያውቀው በጸሎት ነው። እርግጥ ከመወለዳችን በፊት ሕይወታችንን ያውቃል። ነገር ግን እሱን ማነጋገር፣ መፈለግ ይፈልጋል። ከእግዚአብሔር ጋር ያለህን ወዳጅነት፣ ቅርበትና ግንኙነት የምታጠናክርበት በጸሎት ነው። በኢየሱስ የምታምን ሰው እንደመሆንህ መጠቀም የምትችለው መሳሪያ ጸሎት ነው። ከእያንዳንዱ ውጊያ ለመከላከል የምትጠቀምበት ጋሻ ነው። ምክንያቱም በጸሎት ነው ድል የምታገኘው።
የጸሎት ኃይል ከአንተ የሚመጣ አይደለም። ኃይሉ በኢየሱስ ነው ያለው፤ እሱ ለጸሎት የሚመልስና የሰው ልጅ የማይቻለውን የሚያደርግ ነው። ከልብ ስንጸልይ የአባታችንን መጽናኛ፣ ሰላምና ፍቅር እናገኛለን። በተሰበረና በትሑት ልብ ወደ እግዚአብሔር ቅረብ፤ በፍጹም አይጥልህም። (ኤፌሶን 6:18) በመንፈስ ቅዱስ በጸሎትና በልመና ሁልጊዜ ጸልዩ። ንቁና በጸሎት በሁሉም ቅዱሳን ጸንታችሁ ኑሩ።
ስትጸልይ ምስጋና አቅርብ። ልመናህን ብቻ አታቅርብ፤ በእርሱ ፊት ዝም በል። (1ኛ ተሰሎንቄ 5:16-18) ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ዘወትር ጸልዩ፤ በሁሉም ነገር እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ይህ በክርስቶስ ኢየሱስ ለእናንተ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።
እናንተ ወደ ባሕር የምትወርዱ፣ በዚያም ያላችሁ ሁሉ፣ ደሴቶችና በዚያ የምትኖሩ በሙሉ፣ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣ ከምድር ዳርቻም ምስጋናውን ዘምሩ።
ከዚያም በሰማይና በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር፣ በእነርሱ ውስጥ ያሉ ፍጥረታትም ሁሉ እንዲህ ብለው ሲዘምሩ ሰማሁ፤ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኀይል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን።”
በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቷል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል።
እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።”
በዚህ ጊዜ በዙሪያዬ ባሉ ጠላቶቼ ላይ፣ ራሴ ከፍ ከፍ ይላል፤ በድንኳኑም ውስጥ የእልልታ መሥዋዕት እሠዋለሁ፤ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፤ እዘምርለታለሁም።
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም አወድሳለሁ፤ አስቀድሞ የታሰበውን፣ ድንቅ ነገር፣ በፍጹም ታማኝነት አድርገሃልና።
“የመዳናችን አምላክ ሆይ አድነን፤ ለቅዱስ ስምህ ምስጋና እንድናቀርብ፣ በምስጋናህም እንድንከብር ሰብስበን፤ ከአሕዛብም መካከል ታደገን” ብላችሁ ጩኹ።
እርሾ ያለበትን እንጀራ የምስጋና መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን አሳውቁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች የምትወድዱት ይህን ነውና፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የክርስቶስ ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በጥበብ ሁሉ ተማማሩ፤ ተመካከሩ፤ በመዝሙርና በማሕሌት፣ በመንፈሳዊም ቅኔ በማመስገን በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።
መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም።
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ፤ ስለ ድንቅ ሥራዎችህም ሁሉ እናገራለሁ።
ስምህን የሚያውቁ ይታመኑብሃል፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ የሚሹህን አትተዋቸውምና።
በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ሥራውንም በሕዝቦች መካከል በግልጽ አውሩ፤
ደም ተበቃዩ ዐስቧቸዋልና፤ የጭቍኖችንም ጩኸት አልዘነጋም።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶቼ የሚያደርሱብኝን መከራ ተመልከት፤ አይተህም ራራልኝ፤ ከሞት ደጅም አንሥተህ መልሰኝ፤
ይህን ስታደርግልኝ፣ በጽዮን ሴት ልጅ ደጅ፣ ምስጋናህን ዐውጃለሁ፤ በማዳንህም ሐሤት አደርጋለሁ።
አሕዛብ በቈፈሩት ጕድጓድ ገቡ፤ እግራቸውም ራሳቸው በስውር ባስቀመጡት ወጥመድ ተያዘ።
እግዚአብሔር በትክክለኛ ፍርዱ የታወቀ ነው፤ ክፉዎችም በእጃቸው ሥራ ተጠመዱ። ሒጋዮን ሴላ
ክፉዎች ተመልሰው ወደ ሲኦል ይወርዳሉ፤ እግዚአብሔርን የሚዘነጉ ሕዝቦችም ሁሉ እንደዚሁ።
ድኾችን ግን መቼም ቢሆን አይረሱም፤ የችግረኞችንም ተስፋ ለዘላለም መና ሆኖ አይቀርም።
እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ፤ ሰውም አያይል፤ አሕዛብም በፊትህ ይፈረድባቸው።
በአንተ ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፤ ስምህን በመዝሙር እወድሳለሁ።
በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።
ጌታ መንፈስ ነው፤ የጌታም መንፈስ ባለበት በዚያ ነጻነት አለ።
እኛም ሁላችን ባልተሸፈነ ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያንጸባረቅን፣ የርሱን መልክ እንድንመስል ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን፤ ይህም የሚሆነው መንፈስ ከሆነ ጌታ ነው።
እግዚአብሔር ይነሣ፤ ጠላቶቹ ይበተኑ፤ የሚጠሉትም ከፊቱ ይሽሹ።
መንጋህ መኖሪያው አደረጋት፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ ከበረከትህ ለድኾች ሰጠህ።
ጌታ እንዲህ ሲል ቃሉን አስተላለፈ፤ ትእዛዙን የሚያውጁትም ብዙ ሰራዊት ናቸው፤
“የሰራዊት ነገሥታት ፈጥነው ይሸሻሉ፤ በሰፈር የዋሉ ሴቶችም ምርኮን ተካፈሉ።
በበጎች በረት መካከል ብትገኙ እንኳ፣ ከብር እንደ ተሠሩ የርግብ ክንፎች፣ በቅጠልያ ወርቅ እንደ ተለበጡ ላባዎች ናችሁ።”
ሁሉን ቻዩ በዚያ የነበሩትን ነገሥታት በበተነ ጊዜ፣ በሰልሞን እንደሚወርድ በረዶ አደረጋቸው።
አንተ ብርቱ ተራራ፣ የባሳን ተራራ ሆይ፤ አንተ ባለብዙ ጫፍ ተራራ፣ የባሳን ተራራ፤
እናንተ ባለብዙ ጫፍ ተራሮች ሆይ፤ እግዚአብሔር ሊኖርበት የመረጠውን ተራራ፣ በርግጥ እግዚአብሔር ለዘላለም የሚኖርበትን ተራራ ለምን በቅናት ዐይን ታያላችሁ?
የእግዚአብሔር ሠረገላዎች እልፍ አእላፍ ናቸው፤ ሺሕ ጊዜም ሺሕ ናቸው፤ ጌታ ከሲና ወደ መቅደሱ ገባ።
ወደ ላይ ዐረግህ፤ ምርኮ አጋበስህ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ አንተ በዚያ ትኖር ዘንድ፣ ከዐመፀኞችም ሳይቀር፣ ከሰዎች ስጦታን ተቀበልህ።
ሸክማችንን በየዕለቱ የሚሸከምልን፣ አዳኝ አምላካችን፣ ጌታ ይባረክ። ሴላ
ጢስ እንደሚበንን፣ እንዲሁ አብንናቸው። ሰም በእሳት ፊት እንደሚቀልጥ፣ ክፉዎችም እንዲሁ ከእግዚአብሔር ፊት ይጥፉ።
አምላካችን የሚያድን አምላክ ነው፤ ከሞት ማምለጥ የሚቻለውም በጌታ በእግዚአብሔር ነው።
በርግጥ እግዚአብሔር የጠላቶቹን ራስ፣ በኀጢአታቸውም የሚጸኑትን ሰዎች ጠጕራም ዐናት ይፈነካክታል።
ጌታ እንዲህ ይላል፤ “ከባሳን መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ ከባሕርም ጥልቀት አውጥቼ አመጣቸዋለሁ፤
እግርህ በጠላትህ ደም ውስጥ እንዲጠልቅ፣ የውሻህም ምላስ ከጠላትህ ድርሻውን እንዲያገኝ ነው።”
አምላክ ሆይ፤ የክብር አካሄድህ ታየ፤ ይህም አምላኬና ንጉሤ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያደርገው የክብር አካሄድ ነው።
መዘምራን ከፊት፣ መሣሪያ የሚጫወቱ ከኋላ ሆነው ሲሄዱ፣ ከበሮ የሚመቱ ቈነጃጅትም በመካከላቸው ነበሩ።
እግዚአብሔርን በጉባኤ አመስግኑት፤ ከእስራኤል ምንጭ የተገኛችሁ እግዚአብሔርን አመስግኑ።
የሚመራቸው ትንሹ ብንያም ነው፤ በዚያ በብዙ የሚቈጠሩ የይሁዳ መሳፍንት፣ እንዲሁም የዛብሎንና የንፍታሌም መሳፍንት ይገኛሉ።
እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀይልህን እዘዝ፤ አምላክ ሆይ ቀድሞ እንዳደረግህልን አሁንም ብርታትህን አሳየን።
በኢየሩሳሌም ስላለው ቤተ መቅደስህ፣ ነገሥታት እጅ መንሻ ያመጡልሃል።
ጻድቃን ግን ደስ ይበላቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት ሐሤት ያድርጉ፤ ደስታንና ፍሥሓን የተሞሉ ይሁኑ።
ሃሌ ሉያ። ለእግዚአብሔር አዲስ ቅኔ ተቀኙ፤ ምስጋናውንም በቅዱሳን ጉባኤ ዘምሩ።
እስራኤል በፈጣሪው ደስ ይበለው፤ የጽዮንም ልጆች በንጉሣቸው ሐሤት ያድርጉ።
ስሙን በሽብሸባ ያመስግኑ፤ በከበሮና በመሰንቆ ይዘምሩለት።
ብርታትንና መጽናናትን የሚሰጥ አምላክ፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ስትከተሉ፣ በመካከላችሁ አንድ ሐሳብ ይስጣችሁ፤
ይኸውም በአንድ ልብና በአንድ አፍ ሆናችሁ፣ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክና አባት ታከብሩ ዘንድ ነው።
እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው! ክብርህ ከሰማያት በላይ፣ ከፍ ከፍ ብሏል።
ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ ሕፃናት አፍ፣ ምስጋናን አዘጋጀህ፤ ከጠላትህ የተነሣ፣ ባላንጣንና ቂመኛን ጸጥ ታሰኝ ዘንድ።
የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣
ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም።