Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ራእይ 5 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ጥቅልል መጽሐፉና በጉ

1 በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው በውስጥና በውጭ በኩል የተጻፈበት፣ በሰባት ማኅተም የታሸገ ጥቅልል መጽሐፍ በቀኝ እጁ ይዞ አየሁ።

2 አንድ ብርቱ መልአክ በታላቅ ድምፅ፣ “ማኅተሞቹን ለመፍታትና መጽሐፉን ለመክፈት የተገባው ማን ነው?” ብሎ ሲያውጅ አየሁ።

3 ነገር ግን በሰማይም ሆነ በምድር፣ ከምድርም በታች መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ መመልከት የሚችል ማንም አልነበረም።

4 እኔም መጽሐፉን ለመክፈት ወይም ገልጦ ለመመልከት የተገባው ማንም ባለመኖሩ እጅግ አለቀስሁ።

5 ከዚያም ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ “አታልቅስ፤ እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ የዳዊት ሥር ድል ነሥቷል፤ እርሱ መጽሐፉን ሊከፍትና ሰባቱንም ማኅተሞች ሊፈታ ይችላል” አለኝ።

6 ከዚያም በዙፋኑና በአራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ በሽማግሌዎቹም መካከል የታረደ የሚመስል በግ ቆሞ አየሁ፤ በጉም ሰባት ቀንዶችና ሰባት ዐይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩት ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።

7 እርሱም መጥቶ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ቀኝ እጅ መጽሐፉን ወሰደ።

8 መጽሐፉን በወሰደ ጊዜ አራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችም በበጉ ፊት በግንባራቸው ተደፉ፤ እያንዳንዳቸውም የቅዱሳን ጸሎት የሆኑትን በገናና ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ሙዳይ ይዘው ነበር።

9 እንዲህም እያሉ አዲስ መዝሙር ዘመሩ፤ “መጽሐፉን ልትወስድ፣ ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ታርደሃል፤ በደምህም ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋ ሁሉ፣ ከወገን ሁሉ፣ ከሕዝብ ሁሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃል።

10 ለአምላካችንም መንግሥትና ካህናት አድርገሃቸዋል፤ እነርሱም በምድር ላይ ይነግሣሉ።”

11 ከዚያም ተመለከትሁ፤ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም ሺሕ ጊዜ ሺሕና እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ። እነርሱም በዙፋኑና በሕያዋን ፍጡራኑ፣ በሽማግሌዎቹም ዙሪያ ከብበው ነበር፤

12 በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ዘመሩ፤ “የታረደው በግ ኀይልና ባለጠግነት፣ ጥበብና ብርታት፣ ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣ ሊቀበል ይገባዋል።”

13 ከዚያም በሰማይና በምድር፣ ከምድር በታችና በባሕር፣ በእነርሱ ውስጥ ያሉ ፍጥረታትም ሁሉ እንዲህ ብለው ሲዘምሩ ሰማሁ፤ “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኀይል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን።”

14 አራቱ ሕያዋን ፍጡራንም፣ “አሜን!” አሉ፤ ሽማግሌዎቹም በግምባራቸው ተደፍተው ሰገዱ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች