መዝሙር 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 8 ለመዘምራን አለቃ፤ በጊጊት የሚዜም፤ የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው! ክብርህ ከሰማያት በላይ፣ ከፍ ከፍ ብሏል። 2 ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ ሕፃናት አፍ፣ ምስጋናን አዘጋጀህ፤ ከጠላትህ የተነሣ፣ ባላንጣንና ቂመኛን ጸጥ ታሰኝ ዘንድ። 3 የጣቶችህን ሥራ፣ ሰማያትህን ስመለከት፣ በስፍራቸው ያኖርሃቸውን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ሳይ፣ 4 በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው? 5 ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው፤ ክብርንና ግርማን አጐናጸፍኸው። 6 በእጆችህ ሥራ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉንም ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፤ 7 በጎችንና ላሞችን ሁሉ፣ የዱር አራዊትንም፣ 8 የሰማይ ወፎችንና የባሕር ዓሦችን፣ በባሕር ውስጥ የሚርመሰመሱትንም ሁሉ አስገዛህለት። 9 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ምንኛ ግርማዊ ነው! |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.