እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል።
ነገር ግን የሰዎችን በደል ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይልላችሁም።
እርስ በርሳችሁም ተቻቻሉ፤ ከእናንተ አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሠኘበት ነገር ቢኖር ይቅር ተባባሉ፤ ጌታ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ሌላውን ይቅር በሉ።
በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ይቅር ልበለው? እስከ ሰባት ጊዜ ነውን?” አለው።
ኢየሱስም “እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” አለው።
እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም።
ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት።
ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ።
ብፁዕ ነው፤ መተላለፉ ይቅር የተባለለት፣ ኀጢአቱም የተሸፈነለት፤
የክፉዎች ዋይታ ብዙ ነው፤ በእግዚአብሔር የሚታመን ግን፣ ምሕረት ይከብበዋል።
ጻድቃን ሆይ፤ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤትም አድርጉ፤ ቅን ልብ ያላችሁም ሁሉ እልል በሉ።
ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር ኀጢአቱን የማይቈጥርበት፣ በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት፤
በዚያም ሰዎች አንድ ሽባ ሰው በቃሬዛ ተሸክመው ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አይዞህ አንተ ልጅ፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።
እናንተ ይቅር የምትሉትን ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ በርግጥ ይቅር የምለው ነገር ካለ፣ በክርስቶስ ፊት ይቅር የምለው ስለ እናንተ ስል ነው።
ስለዚህ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። “ወንድምህ ቢበድል ገሥጸው፤ ቢጸጸት ይቅር በለው።
“የሰው ልጅ በሚገለጥበትም ቀን እንደዚሁ ይሆናል።
በዚያ ቀን በቤቱ ጣራ ላይ ያለ፣ ማንም ሰው በቤቱ ውስጥ ያለውን ንብረት ለመውሰድ አይውረድ፤ እንዲሁም በዕርሻ ቦታ ያለ ሰው ወደ ኋላው አይመለስ።
የሎጥን ሚስት አስታውሱ።
ነፍሱን ለማሰንበት የሚፈልግ ሁሉ ያጣታል፤ ነፍሱን የሚያጠፋት ግን ያቈያታል።
እላችኋለሁ፤ በዚያች ሌሊት ሁለት ሰዎች በአንድ ዐልጋ ይተኛሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።
ሁለት ሴቶች ዐብረው ይፈጫሉ፤ አንዷ ትወሰዳለች፤ ሌላዋ ትቀራለች [
ሁለት ሰዎች በዕርሻ ቦታ ዐብረው ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው ይቀራል።”]
እነርሱም መልሰው፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚወሰዱት ወዴት ነው?” አሉት። እርሱም፣ “በድን ባለበት አሞሮች ይሰበሰባሉ” አላቸው።
በቀን ሰባት ጊዜ ቢበድልህና ሰባት ጊዜ፣ ‘ተጸጽቻለሁ’ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ ይቅር በለው።”
እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ።
አምላኬ ሆይ፤ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ ቀና የሆነውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
ከፊትህ አትጣለኝ፤ ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድ።
የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፤ በእሽታ መንፈስም ደግፈህ ያዘኝ።
እኔም ለሕግ ተላላፊዎች መንገድህን አስተምራለሁ፤ ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።
የድነቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ደም ከማፍሰስ አድነኝ፤ አንደበቴም ስለ ጽድቅህ በእልልታ ይዘምራል።
ጌታ ሆይ ከንፈሮቼን ክፈት፤ አፌም ምስጋናህን ያውጃል።
መሥዋዕትን ብትወድድ ኖሮ ባቀረብሁልህ ነበር፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ደስ አያሰኝህም።
እግዚአብሔር የሚቀበለው መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ አትንቅም።
በበጎ ፈቃድህ ጽዮንን አበልጽጋት፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥሮች ሥራ።
የጽድቅ መሥዋዕት፣ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሙሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያን ጊዜ ደስ ያሰኙሃል፤ ኰርማዎች በመሠዊያህ ላይ የሚሠዉትም ያን ጊዜ ነው።
በደሌን ፈጽሞ ዕጠብልኝ፤ ከኀጢአቴም አንጻኝ።
ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው።
ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
ኀጢአቴን ለአንተ አስታወቅሁ፤ በደሌንም አልሸሸግሁም፤ ደግሞም “መተላለፌን ለእግዚአብሔር እናዘዛለሁ” አልሁ፤ አንተም የኀጢአቴን በደል፣ ይቅር አልህ። ሴላ
እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለመገረዝ ሙታን ነበራችሁ፣ እግዚአብሔር ግን ከክርስቶስ ጋራ ሕያዋን አደረጋችሁ፤ በደላችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤
ክፉ ሰው መንገዱን፣ በደለኛም ሐሳቡን ይተው። ወደ እግዚአብሔር ይመለስ፤ እርሱም ምሕረት ያደርግለታል፤ ወደ አምላካችን ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።
ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ እኛም በብርሃን ብንመላለስ፣ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።
ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው” ብሎ፣ ሽባውን፣ “ተነሣ! ቃሬዛህን ይዘህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው።
ወንድሞች ሆይ፤ አንድ ሰው በኀጢአት ውስጥ ገብቶ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ በገርነት ልትመልሱት ይገባል። ነገር ግን አንተም እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።
ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ኀጢአት መሥራትና የስድብ ቃል ሁሉ መናገር ለሰዎች ይቅር ይባልላቸዋል፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚነገር የስድብ ቃል ይቅር አይባልም።
ዳዊትም እግዚአብሔር ጽድቅን ያለ ሥራ ስለሚቈጥርለት ሰው ብፅዕና እንዲህ ብሏል፤
“መተላለፋቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኀጢአታቸው የተሰረየላቸው፣ ብፁዓን ናቸው።
ኀጢአቱን፣ ጌታ ከቶ የማይቈጥርበት ሰው ምስጉን ነው።”
ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለ ምሕረትህና ስለ ታማኝነትህ፣ ለስምህ ምስጋና አቀርባለሁ፤ ስምህንና ቃልህን፣ ከሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አድርገሃልና።
ወንድሞቼ ሆይ፤ ነጻ እንድትሆኑ ተጠርታችኋል፤ ነጻነታችሁን ግን ሥጋዊ ምኞታችሁን መፈጸሚያ አታድርጉት፤ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በፍቅር ያገልግል።