ስለዚህ ከቶ የማይናወጥ መንግሥት ስለምንቀበል እግዚአብሔርን እናመስግን፤ ደግሞም ደስ በሚያሠኘው መንገድ በአክብሮትና በፍርሀት እናምልከው፤
“አምላካችን የሚባላ እሳት ነውና።”
አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣
መልካም እንዲሆንልህና ዛሬ እኔ የምሰጥህን ትእዛዞችና የእግዚአብሔር ሥርዐቶች እንድትጠብቅ አይደለምን?
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው።
አሁንም እስራኤል ሆይ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? አምላክህን እግዚአብሔርን እንድትፈራው፣ በመንገዶቹ ሁሉ እንድትሄድ፣ እንድትወድደው፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ እንድታገለግለው፣
ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣
ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።
እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን? እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?” ይላል እግዚአብሔር። “ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።
የምታደርጉትን ሁሉ ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉት ቈጥራችሁ በሙሉ ልባችሁ አድርጉት፤
ከጌታ ዘንድ እንደ ብድራት የምትቀበሉት ርስት እንዳለ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስን ነው።
ከሕዝቦች መካከል ባወጣኋችሁ ጊዜ፣ ከተበተናችሁባቸውም አገሮች በሰበሰብኋችሁ ጊዜ፣ መልካም መዐዛ እንዳለው ዕጣን እቀበላችኋለሁ፤ በእናንተም መካከል ቅዱስ መሆኔን በአሕዛብ ፊት እገልጣለሁ።
እርሱ በፈረስ ኀይል አይደሰትም፤ በሯጭም ብርታት ላይ ደስታውን አያደርግም።
ነገር ግን እግዚአብሔር በሚፈሩት፣ በምሕረቱ በሚታመኑትም ይደሰታል።
ታዲያ ለእነርሱም ሆነ ለልጆቻቸው ለዘላለም መልካም እንዲሆንላቸው፣ እኔን እንዲፈሩና ሁልጊዜ ትእዛዞቼን ሁሉ እንዲጠብቁ እንደዚህ ያለ ልብ ቢኖራቸው ምናለ!
ከፍ ከፍ ያለውና ልዕልና ያለው እርሱ፣ ስሙም ቅዱስ የሆነው፣ ለዘላለም የሚኖረው እንዲህ ይላል፤ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት፣ ከፍ ባለውና በቅዱሱ ስፍራ እኖራለሁ፤ የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋራ እሆናለሁ።
ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የባሪያውንም ቃል የሚሰማ ማን ነው? ያ ሰው በጨለማ የሚሄድ ከሆነና፣ ብርሃንም ከሌለው፣ በእግዚአብሔር ስም ይታመን፤ በአምላኩም ይደገፍ።
ብልቶቻችሁን የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኀጢአት አታቅርቡ፤ ይልቁንስ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።
ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ።
እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።
እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
እግዚአብሔርን የምትፈሩና የምታመልኩ፣ የምትታዘዙትና በትእዛዞቹ ላይ የማታምፁ ከሆነ፣ እንዲሁም እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ከተከተላችሁ መልካም ይሆንላችኋል።