ሚልክያስ 1:4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) ኤዶምያስ፦ እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፣ በሰዎችም ዘንድ፦ የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ይባላል። አዲሱ መደበኛ ትርጒም ኤዶምያስ፣ “ብንደመሰስም እንኳ የፈረሰውን መልሰን እንሠራዋለን” ይል ይሆናል። የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤ “እነርሱ ይሠሩ ይሆናል፤ እኔ ግን አፈርስባቸዋለሁ፤ ክፉ ምድር፣ እግዚአብሔርም ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ተብለው ይጠራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) ኤዶም፦ “እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን” ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ የክፋት አገር፥ ጌታ ለዘለዓለም የተቆጣው ሕዝብ ብለው ይጠሩአቸዋል።” አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም ኤዶማውያን የተባሉ የዔሳው ተወላጆች “ከተሞቻችን ፈራርሰዋል፤ ነገር ግን መልሰን እንሠራቸዋለን” ቢሉ የሠራዊት አምላክ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ይሠራሉ፤ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ ሕዝቡም ሁሉ አገሪቱን ‘የክፋት ምድር’ ኗሪዎቹንም ‘እግዚአብሔር ለዘለዓለም የተቈጣው ሕዝብ’ ብለው ይጠሯቸዋል።” መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) ኤዶምያስ፦ እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፥ በሰዎችም ዘንድ፦ የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ ይባላል። |
በሐሣር እንዳትወድቁ፥ ክብራችሁን ወዴት ትተዉታላችሁ? በዚህም ሁሉ እንኳ ቍጣው አልተመለሰችም፤ ነገር ግን እጁ ገና ተዘርግታ ትኖራለች።
በባሕርም በኩል በፍልስጥኤማውያን መርከቦች ላይ እየበረሩ ይወርዳሉ፤ የምሥራቅ ሰዎችንና ኤዶምያስን በአንድነት ይዘርፋሉ፤ በሞዓብ ላይ ቀድመው እጃቸውን ይዘረጋሉ፤ የአሞንም ልጆች ቀድመው ለእነርሱ ይታዘዛሉ።
ስለዚህ እግዚአብሔር በኤዶምያስ ላይ የመከረባትን ምክር፥ በቴማንም በሚኖሩ ስዎች ላይ ያሰባትን ዐሳብ ስሙ፤ ትንንሾች በጎችን ዘርፈው ይወስዷቸዋል፤ የሚኖሩባትንም ማደሪያቸውን ባድማ ያደርጉባቸዋል።
ስለ ኤዶምያስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በውኑ በቴማን ጥበብ የለምን? ከብልሃተኞችስ ምክር ጠፍቶአልን? ጥበባቸውስ አልቆአልን?
እናንተ በድዳን የምትኖሩ ሆይ! የዔሳውን ጥፋት፥ የምጐበኝበትን ጊዜ አመጣበታለሁና ሽሹ፤ ወደ ኋላም ተመለሱ፤ በጥልቅም ጕድጓድ ውስጥ ተቀመጡ።
መከርህንና እንጀራህን ይበላሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህንም ይበሉአቸዋል፤ በጎችህንና ላሞችህንም ይበላሉ፤ ወይንህንና በለስህንም፥ ዘይትህንም ይበላሉ፤ የምትታመናቸውን የተመሸጉ ከተሞችህንም በሰይፍ ያጠፋሉ።”
በሰይፍ ትወድቃላችሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች እፈርድባችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እጄን በኤዶምያስ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከእርስዋም ዘንድ ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ ባድማም አደርጋታለሁ፤ ከቴማንና ከድዳንም ያመለጡ በሰይፍ ይወድቃሉ።
በሕዝቤ በእስራኤል እጅ ኤዶምያስን እበቀላለሁ፤ እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴም መጠን በኤዶምያስ ያደርጋሉ፤ በቀሌንም ያውቃሉ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
እንደ ተራቈተ ድንጋይ አደርግሻለሁ፤ የመረብም ማስጫ ትሆኛለሽ፤ ከእንግዲህ ወዲህ አትሠሪም፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁና፥” ይላል እግዚአብሔር።
ለዘለዓለምም ባድማ አደርግሃለሁ፤ ከተሞችህም ሰው የማይኖርባቸው ይሆናሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃለህ።
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦“ወንድሙን በሰይፍ አሳድዶታልና፥ በምድር ላይም ማኅፀንን አርክሶአልና፥ የሚዘልፈውንና የሚያስደነግጠውን በርብሮአልና፥ መዓቱንም ለዘለዓለም ጠብቆአልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የኤዶምያስ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም።
የክረምቱንና የበጋዉን ቤት እመታለሁ፤ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፤ ሌሎችም ታላላቆች ቤቶች ይፈርሳሉ” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
ድሃውንም ደብድባችኋልና፤ መማለጃንም ከእርሱ ወስዳችኋልና፤ ያማሩ ቤቶችንም መርጣችሁ ሠርታችኋልና፥ ነገር ግን አትኖሩባቸውም፤ ያማሩ የወይን ቦታዎችም ተክላችኋል፤ ነገር ግን ወይንን አትጠጡም።
የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ወደ ካልኔ ተሻግራችሁ ተመልከቱ፤ ከዚያም ወደ ኤማትራባ እለፉ፤ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፤ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይበረታሉ፤ ድንበራቸውም ከድንበራቸው ይሰፋልና።
የአብድዩ ራእይ። ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኤዶምያስ እንዲህ ይላል፦ ከእግዚአብሔር ዘንድ መስማትን ሰማሁ፤ ከባቢን ወደ አሕዛብ ልኮ፥ “ተነሡ፤ በላይዋም እንነሣና እንውጋት።